1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮትዲቯር ቀውስ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 21 2003

ሁለተኛ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ካደረገች አንድ ወር ያለፋት የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኮትዲቯር አሁንም ቀውስ ውስጥ ናት።የምዕራብ አፍሪካ የምጣኔ ሀብት ማህበረሰብ ግባግቦን ከሆነ በሰላም አልያም በኃይል ስልጣን እንዲያስረክቡ ለማድረግ እየተነጋገረ ነው።

https://p.dw.com/p/QlTd
ሎረን ግባግቦምስል AP

ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ በኮትዲቯር የተደረገው ፕሬዝዳንታዊ በእርግጥ ሰላም ያወርዳል፤ አንድነትንም ያመጣል የሚል እምነት ብዙዎች ዘንድ ነበር። የታሰበው የተጠበቀው ሳይሆን ቀረና ሀገሪቱ በውጥረት ታመሰች። የምርጫ ኮሚሽኑ አሸናፊነታቸውን ያወጀላቸው የተቃዋሚው ዕጩ አላሳኔ ዋታራ ከአቢጃን ቤተመንግስት መግባት አልቻሉም። ሎረን ግባግቦ አሻፈረኝ እንዳሉ፤ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰቡም ጥሪ ጆሮ እንደነፈጉ አሉ። የሁለቱ ተቀናቃኞች ፍጥጫ ደጋፊዎቻቸውን አደባባይ አስወጥቶ ማጋጨት ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል። በመሃሉ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭትም ከ170 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ወደ 20 ሺህ የሚጠጉት ኮትዲቮራውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። አሸናፊ የተባሉት አላሳኔ ዋታራ ከተሸሸጉበት ሆነው ሚኒስትሮችንና አምባሳደሮችን እየሾሙ ናቸው። በዚህ መሃል ውጥረቱ ያሳሰበው ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በሎረን ግባግቦ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ማሳረፍ ጀምሯል። የመንግስታቱ ድርጅትም ግባግቦ ስልጣን እንዲለቁ አሳስቧል። በግብግቦ የተላኩትን ትቶ በዋታራ የተሾሙትን የኮትዲቯር አምባሳደርንም የሹመት ድብዳቤ ተቀብሏል። ጫናው የበረታባቸው ግባግቦ በእርግጥ ስለስልጣን መልቀቅ ፍንጭ እንኳን አላሳዩም። እንደውም ይዞታቸውን ለማጠናከር መፍጨርጨሩን ቀጥለዋል። የምዕራብ አፍሪካ የምጣኔ ሀብት ማህበረሰብ ኢኳዋስ የሰላሙ ጥረት ካልተሳካ በወታደራዊ እርምጃ ግብግቦን ከቤተመንግስት ፈንቅሎ ለማስወጣት መሪዎቹ መነጋገር ጀምረዋል። የአፍሪካ የደህንነት ጥናት ተቋም የሰላም ተልዕኮዎች ፕሮግራም ሃላፊ ሄነሪ ቦሾፍ ወታደራዊ አማራጩ የመጨረሻው ሊሆን ይችላል ይላሉ።

«ኢኳዋስ ለመሸምገልና ውጥረቱ በሰላማዊ መንገድ አንዲረግብ ማንኛውንም አማራጭ እየተጠቀመ ያለ ይመስለኛል። እናም ወታደራዊ አማራጭ ብቻ እስኪቀር ድረስ ሁሉንም ጥረቶች እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ይህ ማለት ወታደራዊ አማራጩ የግድ መዘግየት አለበት ማለት አይደለም። ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው።»

ከትላንት በስቲያ ሶስት የምዕራብ አፍሪካ ሸገራት መሪዎች በኢኳዋስ ስም በሰጡት መግለጪያ ግብግቦ ስልጣኑን በሰላም የማያስረክቡ ከሆነ ሰራዊት እንደሚዘምቱባቸው ዝተዋል። ይህ የምዕራብ አፍሪካ ምጣኔ ሀብት ማሀበረሰብ ማስፈራሪያ ወደ ተግባር መለወጡ እንደማይቀር ታዛቢዎች ይናገራሉ። በተለይ በአሸናፊው አላሳኔ ዋታራ የተሾሙት በመንግስታቱ ድርጅት የኮትዲቯር አምባሳደር ዩሱፉ ባምባ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በአፋጣኝ አንዳች እርምጃ ካልወሰደ ሀገራቸው ወደዘር ፍጅት ውስጥ ልትገባ ትችላለች ሲሉ ገልጸዋል። በእርግጥ አሁን ላይ ሁኔታዎች ወታደራዊ አማራጩን የሚፈልጉበት ምዕራፍ ላይ እንደደረሱ አመላክተዋል። በተለይ የግባግቦ ደጋፊዎች በመንግስታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ላይም ጥቃት መሰንዘር መጀመራቸው የቀጠናው ሀገራት የኃይል አማራጩን እንዲወስዱት የሚያደርጋቸው ነው ተብሏል። የአፍሪካ የደህንነት ጥናት ተቋም የሰላም ተልዕኮዎች ፕሮግራም ሃላፊ ሄነሪ ቦሾፍ፤ ወታደራዊ አማራጩ በርካታ ፈተናዎች የተደቀኑበት ነው ይላሉ።

«በኮትዲቯር የሚሆነው ነገር በጎረቤት ሀገራት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ለዚህም ነው ችግሩን በሰላም መፍታት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተካሄደ ያለው። ሌላው የወታደራዊ አማራጩ ፈተና የሚሰማራው ሰራዊት የሚገኝበት መንገድ ነው። አሁን የመንግስታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ይገኛል። ይህ ግባግቦን ለማስወገድ የሚሰማራው ሰራዊት በአፍሪካ ህብረት ወይስ በኢኳዋስ የሚዘምት ነው? ይህ ራሱ ትልቅ ፈተና ነው። ጋናና ሴኔጋል ቡዙውን ሰራዊት ያሰማራሉ ተብሎ ይገመታል። ናይጄሪያም እንዲሁ። ይህ የሚዋጣውን ሰራዊት በአንድ ዕዝ ስር ማንቀሳቀሱም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሌላው የገንዘብ ጉዳይ ነው። ዋናው ግን የሚመስለኝ የሰራዊቱ ሃላፊነትና ስልጣን ነው። እንዴት ነው የምታደርገው? ያ ነው ቁልፉ ጉዳይ።»

በእርግጥ እንደ ሄነሪ ቦሾፍ እምነት ግባግቦን በኃይል ለማስወገድ ከተወሰነ የሚጠብቀው ፈተና እነዚህ ብቻ አይደሉም። የግባግቦ ደጋፊዎች የሚፈጥሩት መሰናክል በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

Dossierbild Elfenbeinküste 2
አላሳኔ ዋታራምስል AP

«48 በመቶ አከባቢ የሚሆነው ህዝብ አሁንም ፕሬዝዳንት ግባግቦን ይደግፋል። እናም ግባግቦን በኃይል ማስወገድ ሀገሪቱን ለበለጠ ውስጣዊ ብጥብጥ መዳረጉ የማይቀር ነው። የኢኳዋስ ሰራዊት ላይ የግባግቦ ደጋፊዎች ጥቃት መሰንዘራቸው እርግጥ ነው። ይህንንም ለምሳሌ በሶማሊያ የኢትዮዽያ ሰራዊት ላይ የሶማሊያ ህዝብ የወሰደውን እርምጃ ማስታወስ ይቻላል። ህዝቡ እንደ ጠላት ያያቸውና ለጥቃትም ኢላማ ሊሆኑ ችለዋል።»

ኢኳዋስ ጦሩን ወደ አቢጃን አሰማርቶ ግባግቦን ከስልጣን የሚያስወግድ ከሆነ ትልቁን ሚና ልትጫወት ትችላለች ተብላ የምትጠበቀው ናይጄሪያ ናት። በእርግጥ ናይጄሪያ በተለያዩ ውስጣዊ ችግሮች ብትወጠርም የኮቲዲቯሩን ቀውስ በቀላሉ የምታየው አይደለም። የአፍሪካ የደህንነት ጥናት ተቋም የሰላም ተልዕኮዎች ፕሮግራም ሃላፊ ሄነሪ ቦሾፍም ይህን ያጠናክራሉ።

«ናይጄሪያም በተወሰኑ ችግሮች የተወጠረች ናት። ምርጫ ከምታካሂድበት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። በሀገሪቱ ዳግም የሃይማኖት ግጭት ተቀስቅሷል። በጣም አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች ችግሮችም ተደቅነውባታል። እናም ያልተረጋጋች ናት ናይጄሪያም። ሆኖም ናይጄሪያ የቀጠናውን የሃይል ሚዛን የጨበጠች ናት። የመሪነቱን ሚና እንደያዘች ትገኛለች። ስለዚህ ማንኛም ነገር ቢከሰት ቁልፍ ሚና የሚኖራት ናይጄሪያ ናት።»

መሳይ መኮንን

ነጋሽ መሐመድ