1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

  የኮሪያ ልሳነ ምድር ዉጥረት

ነጋሽ መሐመድ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 17 2009

የሁለቱ ሐገራት የሐብት፤የቆዳ ስፋት፤ የሕዝብ ብዛት እና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ልዩነት በዝሆንና ዲምቢጥ የሚመሰል ነዉ።በጦር ኃይል  ለመጠፋፋት ግን በ190መቶዎቹ መጀመሪያ ለጥቂት ዓመታት ከማረፋቸዉ በስተቀር ያልተዘጋጁ፤ያልፎከሩ፤ ያልተቆራቆሱበት ዘመን የለም።

https://p.dw.com/p/2ibaK
Kim Jong Un, Donald Trump
ምስል picture alliance/AP Photo

የኮሪያ ልሳነ ምድር ዉጥረት

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሲግማር ጋብሬል ባለፈዉ ሳምንት ጠየቁ «ዓለም ሥንት ቀዉስ» ታስተናግዳለች» ብለዉ።ዓለም በቦምብ-ፈንጂ፤ በሚሳዬል-መኪና ይሸበራል።ከአፍቃኒስታን እስከ ሶማሊያ፤ ከሶሪያ እስከ ደቡብ ሱዳን፤ ከዩክሬይን እስከ የመን በጦርነት፤ በሽታ ረሐብ የሚያልቀዉን  ይቆጥራል።አስከሬን ይቀብራልም።ሰሞኑን ደግሞ ከፕዮንግዮንግ፤ ከዋሽግተን፤ ከቶኪዮ እና ሶል በሚሰማዉ የጦርነት ዛቻ፤ ፉከራ ይሸመቃቀል።በኑክሌር ቦምብ ለመደባደብ የሚዛዛቱት መንግሥታት ከየመሪዎቻቸዉ ፉከራ ወደ ወታደሮቻቸዉ የጦር ልምምድ አድጓል።ቀጥሎስ? 
                                     
ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን በይፋ ያወጁት በገቢር ከወሰኑት ጋር መጣጣሙ ለሩቁ ታዛቢ ግራ አጋቢ ነበር።ጦርነት እንጠላለን አሉ ግን በሰሜን ኮሪያ ላይ ይፋ ጦርነት አወጁ።ሰኔ 27 1950 ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።
                             
«ጦርነት እንጠላልለን።ሰዉ እንወዳለን።ግን ሲያጠፉ ዝም ብለን አናይም።»ከኢትዮጵያ እስከ ቱርክ፤ ከአዉሮጳ እስከ ደቡብ አሜሪካ ያሉ ሐገራትን ጦር ያስከተለችዉ ዩናይትድ ስቴትስ እና በሶቭየት ሕብረትና በቻይና የምትደገፈዉ ሰሜን ኮሪያ ሶስት ዓመት ተዋጉ።ሚሊዮኖች አለቁ፤ ብዙ ሚሊዮኖች ተሰደዱ፤ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሐብት ንብረት ጠፋ።ኮሪያም ለሁለት እንደተከፈለች ቀረች።

Südkorea Gemeinsame Militärübung mit der USA
ምስል Getty Images/AFP/Jung Yeon-Je

የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ካደረሰበት እልቂት ጥፋት በቅጡ ያላገገመዉ ዓለም የኮሪያ ልሳነ-ምድርን በሌላ ጦርነት ማንደዱ ያነሰ ይመስል ለመጪዉ ለትዉል የሚቀጥል ቂም፤በቀል፤ንትርክ፤ፍጥጫን አዳፈነ።ዋነኛ ተዋጊዎች በ1953 የተፈራረሙት የተኩስ አቁም ዉል ዘላቂ ሠላም ለማዉረድም፤ ዳግም ዉጊያ ለመግጠምም፤ እንደ ተፋጠጡ ለመቀጠልም በር የሚከፍት ነዉ።ተፈራራሚዎች ሰላማዊዉን መንገድ እንዲመርጡ በጦርነቱ ዘመድ-ወዳጁ ያለቀበት፤ ሐገሩ እሁለት የተገመሰበት፤ ተሳቅቆ እንዲኖር የተፈረደበት ሕዝብ፤ ተፈራራሚዎች እና ተኪዎቻቸዉ የመጀመሪያዉን አማራጭ ገቢር እንዲያደርጉ ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ መጠየቁ አልቀረም።ዛሬም ባደባባይ ሰልፍ ይሰለፋል።ሠላም እንዲወርድ ይጠይቃል።
                              
«የደቡብ ኮሪያ እና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ዛሬ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ጀምረዋል።ማድረግ የሚገባዉ ተገቢዉ ነገር ልምምዱን መቀነስ ወይም ጨርሶ ማቆም ነዉ።ምክንያቱም ዉጥረት ባየለበት ባሁኑ ወቅት የሚደረገዉ ልምምድ ሰሜን ኮሪያ ለጠብ የሚጋብዝ ነዉ።»
ቢል ክሊተን የዋሽግተንን፤ ኪም ዴ ጁንግ የሶልን፤ ኪም ጆንግ ኢል የፒዮንግዮንግን አብያተ መንግሥታት በተቆጣጠሩበት በ1990ዎቹ መጀመሪያ የየሕዝባቸዉን ጥያቄ እና ፍላጎት ያደመጡ መስለዉ ነበር።ሰወስቱ መሪዎች ያደረጉት ድርድር፤ዉይይት፤ሥምምነት በተቀረዉ ዓለም ዘንድም የሠላም ተስፋ  ፈንጥቆ ነበር።ሁሉም ባፍታ ተዳፍኖ ከዚያ በፊት የነበረዉ ብሶ ቀጠለ።
ክሊንተንን የተኩት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ የለኮሱት ጦርነት ዛሬም ድረስ መቶ ሺዎችን እያረገፈ ነዉ።የቡሽን አስተምሕሮ የተከተሉት የፈረንሳይና የብሪታንያ መሪዎች፤ ቡሽን የተኩትን ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማን አስከትለዉ ሊቢያ ላይ የከፈቱት ጦርነት ዳፋዉ ለምዕራብና ሰሜን አፍሪቃ ተርፏል።ሶሪያ ከጥንታዊ ታሪካዊ ሐገርነት ወደ ከስል አመድ ክምርነት እየተለወጠች ነዉ።
ከአፍሪቃ ሐገራት ከሶማሊያ እስከ ኮንጎ፤ ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር እስከ ደቡብ ሱዳን፤ከማሊ እስከ ናጄሪያ በዉጊያ ጦርነት፤ ግጭት ፍጥጫ እየተንቀረቀቡ ነዉ።ከየመን እስከ ዩክሬን  ከጦርነት፤ ረሐብ በሽታ ሌላ ሌላ ነገር የለም።የሞስኮ ዋሽግተን-ብራስልሶች ሽኩቻም ወደ ቀዝቃዛዉ ዘመን ፍጥጫ እየናረ ነዉ።በዚሕ ሰሞን ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች አያት-አባቶቻቸዉ ያዳፈኑትን እሳት መገላለጥ ጀመሩ። 
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ።-------------------የፒዮግዮንጎች አፀፋ።

Trump: Nordkorea würde Angriff auf Guam bereuen
ምስል Reuters/J. Ernst

የሁለቱ ሐገራት የሐብት፤የቆዳ ስፋት፤ የሕዝብ ብዛት እና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ልዩነት በዝሆንና ዲምቢጥ የሚመሰል ነዉ።በጦር ኃይል  ለመጠፋፋት ግን በ190መቶዎቹ መጀመሪያ ለጥቂት ዓመታት ከማረፋቸዉ በስተቀር ያልተዘጋጁ፤ያልፎከሩ፤ ያልተቆራቆሱበት ዘመን የለም።ጦርነቱ በቆመበት ዘመን በመቶ የሚቆጠሩ የኑክሌር አረሮች የነበሯት ዩናይትድ ስቴትስ ዛሬ 7200 የኑክሌር ቦምብ አከማችታለች።ያኔ ምንም ያልነበራት ሰሜን ኮሪያ ዛሬ በትንሽ ግምት አስር የኑክሌር ቦምብ አምርታለች።
ሁለቱ ሐገራት አንዳቸዉ ሌላቸዉን በኑክሌር ቦምብ መትተዉ ከብቅላዉ አፀፋ አይተርፉም።ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን ወይም ጃፓንን በኑክሌር ቦምብ ከመታች ደግሞ አጻፋዉ ሳይደርስ ብዙ ዜጎችዋ በመርዛማዉ ጢስጠለስ ብቻ ማለቃቸዉ አይቀርም።
ዩናይትድ ስቴትስ ከአንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺሕ በላይ እግረኛ ጦር አላት።ከሰሜን ኮሪያ ጋር ጦርነት የምትገጥም ከሆነ የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ ጦርም ከአሜሪካ የሚቆጠር ነዉ።የሰሜን ኮሪያ እግረኛ ጦር ከአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺሕ በላይ ነዉ።ከሐገሪቱ ዜጋ ስድስት ሚሊዮን የሚሆነዉ ግን ወታደር ለመሆን ጠመንጃ ማንገብ እንጂ አዲስ ሥልጠና አያስፈልገዉም።
ሰሜን ኮሪያ በረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል፤ በባሕር ሰርጓጅ ጀልባና መርከቦች ብዛትና ጥራትም ከአሜሪካኖች አትወዳደርም።የአሜሪካን የቅርብ ታማኞች  ደቡብ ኮሪያን ወይም ጃፓንን ለመምታት ግን አንዱም በቂ ነዉ።
እርግጥ ነዉ ዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ ኮሪያ፤ጉዋም፤ ሰላማዊ ዉቅያኖስ ላይ እና ጃፓን የተከለችዉ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል ከሰሜን ኮሪያ የሚወነጨፈዉን ሚሳዬል አየር ላይ መቅለብ ይችላል።ማንም ግን እርግጠኛ መሆን አይችልም።የጃፓን ባለሥልጣናትን ለማረጋጋት ባለፈዉ ሳምንት ቶኪዮን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትሱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች አዛዥ ጄኔራል ጆሴፍ ዳንፎርድ እንኳ ጦራቸዉ በሰሜን ኮሪያ አጎራባች  ግዛቶች የተከለዉ  ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል የጠላቱን ሚሳዬል ቀልቦ እንደሚያቀር ዋስትና ለመስጠት አልደፈሩም።ሐገራቸዉ ታማኞችዋን ከጥቃት እንደምትከላከል ግን ቃል ገብተዋል።«ጠቅላይ ሚንስትር አቤ የጋራ ግንኙነታችንን፤ በተለይ በወታደራዊ ደረጃ ያለዉን በግልፅ ልነግረዎት እችላለሁ።ከአለት የጠጠረ ነዉ።»
የሁለቱ ሐገራት የመከላከያ እና የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮችም ከአለት የጠጠረዉን ወዳጅነት ያረጋግጣል ባሉት ሥልት ላይ ባለፈዉ ሳምንት ተወያይተዋል።ፕሬዝደንት ትራምፕም ጦራቸዉ የሐገራቸዉን ወዳጆች ከጥቃት እንዲሚከላከል ደጋግመዉ አስታዉቀዋል።
                                    
«ሰሜን ኮሪያ እኛ የምንወደዉን፤የምንወክለዉን፤ ወዳጃችንን ወይም እኛን ለማጥቃት አይደለም ለማጥቃት እንኳን ካሰቡ አቅላቸዉን ይሳታሉ።እዉነቴን ነዉ የምላችሁ ጭራሽ የሚይዙ-የሚጨብጡትን ነዉ የሚያጡት።ምክንያቱም የሚደርስባቸዉ ነገር ይሆናል ብለዉ ጨርሶ ያላሰቡት ነዉ።የሐገራችን ሕዝብ፤ተባባሪዎቻችን፤ ጥቃት አይደርስባቸዉም።የሚከተለዉን እነግራችኃለሁ፤ ሰሜን ኮሪያዎች የሚያደርጉትን በጥሞና ቢያስቡት ይሻላል፤ አለበለዚያ በዚች ዓለም ጥቂት ሐገራት ብቻ የደረሰባቸዉን ዓይነት መከራ ይደርስባቸዋል።»
ሰሜን ኮሪያዎችም ለዛቻ ፉከራ ፕሮፓጋንዳዉ አልሰነፉም።የሐገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበዉ ታላቁ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጦራቸዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሠፈር የሚገኝበትን ጉዋምን በሚሳዬል ለመምታት የነደፈዉን ሥልት ከጦሩ ጠቅላይ እዝ ቢሮ ተገኝተዉ ሲያጠኑ ዉለዋል።ሥለ ሥልቱ አፈፃፀም የጦር ሐይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ኪም ራክ ግዮም ያደረጉላቸዉን ገለፃና ማብራሪያ አድምጠዋል።ታላቁ መሪ ጉብኝታቸዉን ሲያጠናቅቁ አሜሪካኖች አስጠነቀቁ።«ታፍራላችሁ» እያሉ 

Nordkorea Rackete
ምስል picture alliance/AP Photo
Nordkorea Kim Jong Un Armee Offiziere
ምስል Reuters/KCNA

«የተከበሩት የበላይ መሪያችን፤ አሜሪካኖች ትዕግስታችንን ከተፈታተኑና በኮሪያ ልሳነ-ምድር አካባቢ በጣም አደገኛና ወራዳ እርምጃ ከወሰዱ ከዚሕ በፊት እንዳልነዉ አስፈላጊዉን እንወስናለን።አሜሪካኖች በቅጡ ማሰብ እና ትክክለኛ ዉሳኔ ማድረግ አለባቸዉ።አለበለዚያ በኛ ጥቃት ሐፍረት ይከናነባሉ።»
የሁለቱ ሐገራት ጠብ ፍጥጫቸዉን በድርድር እንዲያስወግዱት የተለያዩ መንግሥታት ጠይቀዋል።ሌሎቹ መክረዋል።ያስጠነቀቁም አሉ።ቀዳሚዋ ሩሲያ ናት።የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛኻሮቫ ባለፈዉ ሐሙስ እንዳሉት ማናቸዉም ወታደራዊ እርምጃ የሚያደርሰዉ ጥፋት በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
                                
«የኮሪያ ልሳነ ምድርን ችግር በጦር ኃይል ለመፍታት የሚደረግ ማናቸዉም ሙከራ ከፍተኛ ድቀት ያስከትላል።በሁሉም ተፋላሚ ኃይላት ላይ ከፍተኛ ጥፋት ያደርሳል።በሰዉ፤በምጣኔ ሐብት እና በተፈጥሮ ሐብት ላይ የሚያደርሰዉ ጥፋት አደገኛ ይሆናል።»
ለሰሜን ኮሪያ ታዳላለች እየተባለች የምትወቀሰዉ ቻይናም ለዉጊያ የሚዛዛቱት መንግስታት ጠባቸዉን ለማርገብ እንዲደራደሩ አደራ ብላለች።የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹንዪንግ እንዳሉት ጠቡን የሚያባብስ እርምጃ መቆም አለበት። 
                                     
«ባሁኑ ሰዓት መደረግ ያለበት በጣም አስፈላጊዉ ነገር ሰሜን ኮሪያ የሚሳዬልና የኑክሌር ኃይሏን ማዳበሯን ማቆም ነዉ።አካባቢዉን የሚያነካካ ዉጥረትን ከሚያባብስ ነገር መታቀብም አስፈላጊ ነዉ።የኮሪያ ልሳነ ምድር ከዉጥረት አዙሪት መዉጣት አለበት።ከዚሕ ግብ ለመድረስ የመጀመሪያዉን ጥሩ እንርምጃ ለመዉሰድ መሽቀዳደም አስፈላጊ ነዉ።ትኩረት እና ኃይልን  በሙሉ ድርድሩን አስቀድሞ በመጀመሩ ላይ ማዋል ያስፈልጋል።»
ማስጠንቀቂያ፤ ምክር አደራዉን የሰማ የለም።ዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ዛሬ ሰሜን ኮሪያ ጥግ አዲስ ወታደራዊ ልምምድ ጀምረዋል።አስራ-ሰባት ሺሕ አምስት መቶ የአሜሪካ ወታደሮች፤ ከሐምሳ ሺሕ ከሚበልጡ የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች ጋር የሚያደርጉት ልምምድ ከሰሜን ኮሪያ የሚሰነዝርን ጥቃት በመከላከሉ ላይ ያተኮረ ነዉ ተብሏል።
ሰሜን ኮሪያ ልምምዱን አዉግዛ አፀፋዉን «ጠብቁ» ብላ ዝታለች-እንደተጠበቀዉ።የፖለቲካ ታዛቢዎች የጦር ልምምዱ ሰሜን ኮሪያን  «ከመጓጎጥ የሚቆጠር»  በማለት ተችተዉታል።የዋሽግተንና የሶል ባለሥልጣናት ግን ልምምዱ በየዓመቱ የሚደረግ ነዉ ባይ ናቸዉ።ይዋጉ ይሆን?አይታወቅም።
የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እንዳሉት ግን ዓለም ስንቴ-ስንቱን ቀዉስ ታስናግዳለች።ደግሞስ እስከ መቼ? እንጃ? 

Südkorea Militärmanöver U.S. Air Force U-2 Dragon Lady
ምስል Reuters/Yonhap/Lee Sang-hak

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ