1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ፖለስ እርምጃና የተመድ ወቀሳ

ሐሙስ፣ የካቲት 19 2001

ፖሊሶች አንዳዴ «በግል-ቂም ይገድላሉ።አንዳዴ የተጋፋቸዉ የሚመስላቸዉን ይገድላሉ።ሌላ ጊዜ ጉቦ ጠይቀዉ እንቢ ከተባሉ ይገድላሉ።» ለሁሉም አይነት ግድያ የሚሰጠዉ ምክንያት ግን አንድ ነዉ-ቀጠሉ ባለሙያዉ «ወንጀልን መቆጣጠር።»

https://p.dw.com/p/H1tB
«የኪባኪ ዝምታ---ያጠራጥራል» አልስተንምስል AP

የኬንያ ፖሊሶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሱት ሕገ-ወጥ ግድያና በደል መባባሱን ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ባለሙያ አስታወቁ።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕገ-ወጥ ግድያ ልዩ ባለሙያ ፊሊፕ አልስተን እንዳስታወቁት የኬንያ ፖሊሶችን በቀነባበረና በተጠና ሥልት ሰዎችን እንደሚገድሉ የሚያረጋግጡ በርካታ መረጃዎች አግኝተዋል።አልስተን ለግድያዉ ተጠያቂ ያሏቸዉ የኬንያ ባለሥልጣናት ከሥልጣን እንዲነሱ ሲጠይቁ፥ ፕሬዝዳት ምዋዪ ኪባኪን ግድያዉን በቸልታ አልፈዉታል በማለት ወቅሰዋል።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።

አምና ታሕሳስ ኬንያ የተደረገዉ ምርጫ ዉጤት ዉዝግብ የጎሳ ጠብ ተላብሶ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲያስገድል፥ በሚሊዮን የሚገመት ሐብት ንብረት አስጠፍቶ፥ ብዙ ሺዎችን አሰድዷል።የኬንያ ፖለቲከኞች የኋላ ኋላ ከየሚሹት ሥልጣን መድረሳቸዉ ላይቀር ያን-ያሕል ሕይወት፥ ደም፥ ሐብት ንብረት ያጠፉ-ያስጠፉበት ሰበብ-ምክንያት አሁንም ብዙዎችን በጣሙን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎችን እንዳሳዘነ-እንዳስተዛዘበ ነዉ።

የአመፅ ሁከቱ ቀስቃሾች እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸዉ የመብት-የሕግ ተሟጋቾችን «የዘገየ-ፍትሕ፥- የተነፈገ ነዉ» ነባር ብሒልን ደጋግመዉ እንዲጠቅሱ አስገድዷቸዋል።ያም ሆኖ ፖለቲካ የቀሰቀሰዉ የጎሳ ግድያ አምና ይሕን ጊዜ በጋመበት ወቅት የኬንያ ፖሊስ በተለይ ደግሞ ጦር ሐይሉ ለሾመ-ለሸለመዉ ወግኖ በግድያዉ ሙሉ በሙሉ አለመሳተፉ በብዚዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት ያልተለመደ አስመስጋኝ በጎ ምግባር አይነት ተደርጎ ነበር የታየዉ።

የሕግ-አስከባሪዎችን ሕገ-ወጥ እርምጃ የሚከታተሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ባለሙያ ፊሊፕ አልስተን ትናንት እንዳሉት ግን ምስጋና-የበጎ ምግባር አብነቱ ለኬንያ ጦር ሐይል እንደሁ እንጂ ለፓሊስ የሚገባዉ ተቃራኒዉ ነዉ።ገዳዩ-ማን ሆነና-አይነት።

ድምፅ

«ኬንያ ዉስጥ የሐገሪቱ ፖሊስ ግለሰቦችን በየጊዜዉ እንዲገድል የተቀነባበረ፥ መጠነ-ሠፊ እና በቅጡ የታቀደ ሥልት መኖሩን የሚያረጋግጡ የበርካታ እማኞችን ምሥክርነት-መረጃዎችም አግኝቻለሁ።»

ፖሊስ ሰዎችን እንደፈለገ የገደለና የሚገደለዉ ባለሙያዉ፥ እዚያዉ ናይሮቢ ሆነዉ እንዳሉት፥ በምርጫዉ ዉዝግብ ወቅት፥ ከወዝግቡ በፊትና በኋላ ብቻ አይደለም።ሁሌም እንጂ።እጅግ ብሶ የነበረዉ ግን አምና-እና ሐቻምና ነበር።በሐይማኖት ሽፋን «ሙንጊኪ» በሚል ሥም የተደራጁ ወጣት ወንበዴዎች ዘረፋ፥ ግርፊያና አሰቃቂ ግድያ ሐቻምና አለቅጥ ተበራክቶ ነበር።

ወንበዴዎቹ «ጠላት» የሚሉትን አንገቱን እየቀሉ፥ አንዳዴም ቆዳዉን እየገፈፉ መግደል-ማሰቃያተቸዉን እንዲያስቆም የዘመተዉ ፖሊስ፥ ይላሉ የአለም አቀፉ ድርጅት ባለሙያ፥ እስከዚያ ጊዜ ከሚያደርገዉ በባሰ መልኩ ያሻዉን፥ በፈለገዉ ጊዜ ይረሽን ገባ።ፖሊሶች አንዳዴ «በግል-ቂም ይገድላሉ።አንዳዴ የተጋፋቸዉ የሚመስላቸዉን ይገድላሉ።ሌላ ጊዜ ጉቦ ጠይቀዉ እንቢ ከተባሉ ይገድላሉ።» ለሁሉም አይነት ግድያ የሚሰጠዉ ምክንያት ግን አንድ ነዉ-ቀጠሉ ባለሙያዉ «ወንጀልን መቆጣጠር።»

ለዘፈቀደዉ ግድያ ቁልፍ-ከሚባሉ ችግሮች አንዱ-አሉ አልስተር የፖሊስን ተጠያቂነት የሚያሳይ ዉሰጥ-ደንበ አለመኑሩ ነዉ።

ድምፅ

«ከዋንኞቹ ችግሮች አንዱ በፖሊስ ሐይሉ አሰራር ዉስጥ ተጠያቂነትን የሚያሳይ የዉስጥ አሰራር ሥልት አለመኖሩ ነዉ።ፖሊስ የፈፅመዉን የሚያጣራዉ የገደለዉ ፖሊስ ራሱ ነዉ።»

አልስተን እንደሚሉት የኬንያ ፕሬዝዳት ምዋዪ ኪባኪ እጅግ የተሰራፋዉን ሕገ-ወጥ ግድያ ማስቆም ነበረባቸዉ።ለግድያዉ ቀዳዳ የከፈቱ ደንቦችን ማስወገድ፥ ወይም የደብ ጉድለቶችን ማሟላት፥ ተጠያቂዎችን ለሕግ ማቅረብ ነበረባቸዉ።ፕሬዝዳቱ ይሕን ሊያደርጉ ቀርቶ ሕገ-ወጥ ግድያ እንደሚፈፀም እንኳን በግልፅ አልተናገሩም-አልስተን እንደሚሉት።ይሕ ደግሞ በባለሙያዉ እምነት የእስከዛሬዉን ችግር ለነገም-የሚያሻግር ነዉ።

ድምፅ

«የኬንያ ፕሬዝዳት ኬንያ ዉስጥ ሕገ-ወጥ ግድያ በጣም መስፋፋቱን በይፋ መቀበል ነበረባቸዉ።በፖሊስ ሐይሉ ዉስጥ መሠረታዊ የተሐድሶ ለዉጥ እንደሚያስፈልግ ማስታወቅም ነበረባቸዉ።ፕሬዝዳቱ እስከ ዛሬ ድረስ ዝም ማለታቸዉ ጉዳዩን አጠራጣሪ፥ አስቸጋሪም ያደርገዋል።»

አልተስተን ለግድያዉ በግንባር ቀደም ተጠያቂ ያደረጓቸዉ የኬንያ ፖሊስ አዛዥና የሐገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከስልጣን እንዲነሱ ጠይቀዋል።የተቀበላቸዉ ግን የለም።የመንግሥት ቃል አቀባይ አልፍሬድ ሙትዋ የአልስተር ዘገባ እንዳበሳጫቸዉ አልደበቁም።«ኬንያን ለአስር-ቀን ብቻ ያየ ሰዉ ሥለ ኬንያ ያሉትን ሁሉ ሊሉ አይችሉም»።ቢሉም አከሉ ቃል አቀባዩ «መንግስቴ አይቀበለዉም።»

Dw (Töne),Afp

Negash Mohammed

Hirut Melesse