1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ጊዚያዊ ሁኔታ

ሰኞ፣ ነሐሴ 8 2009

በኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ 54,2% የመራጭ ድምፅ በማግኘት ያሸነፉበትን ምርጫ ውጤት 44,9% ያገኙት ተፎካካሪያቸዉ ራይላ ኦዲንጋ እንደማይቀበሉት ባለፈው ዓርብ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ  በሀገሪቱ ውጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/2iCft
Markt in Nairobi
ምስል AP

«ናይሮቢ በተወሰነ ደረጃ ወደመደበኛው ኑሮ እየተመለሰች ነው»።

የኬንያ የምርጫ እና የድንበር ኮሚሽን የኦዲንጋን ወቀሳ አጣርቶ ምርጫው አልተጭበረበረም ቢልም እና ዓለም አቀፍ ታዛቢ ቡድኖች ምርጫው ነጻና ትክክለኛ እንደነበር ቢያመለክቱም፣ የተቃዋሚ ደጋፊዎች ቁጣቸውን በአደባባባይ በመውጣት ገልጸዋል። በምርጫው ባለፈው ማክሰኞ ከተካሄደ ወዲህ በተቃዋሚዎች እና በፀጥታ ኃይላት መካከል በተፈጠረ ግጭት በመዲናይቱ ናይሮቢ ከ30 የሚበልጥ ሰው መገደሉ በይፋ ተገልጿል። በተቃዋሚዎች ዘገባ መሰረት፣ በፖሊስ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ100 እንደሚበልጥ ነው የተነገረው። የሃገሪቱ ፕሬዚደንት የምርጫውን ውጤት ያልተቀበሉ ሰዎች ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጹ እና ከኃይል ተግባር እንዲቆጠቡ ጥሪ አስተላልፈዋል። በሌላ በኩል ተቀናቃኛቸው ኦዲንጋ ተጭበርብሯ የሚሉትን የምርጫ ውጤት ህዝቡ በመቃወም ዛሬ በቤቱ እንዲውል እና ወደስራ ገበታው እንዳይሄድ አድማ ጠርተዋል። በኬንያ ስለቀጠለው የድህረ ምርጫ ውጥረት እንዲነግሩን ናይሮቢ የሚገኙትን የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ፍቅረማርያም መኮንን በስልክ ጠይቄአቸው ነበር።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ