የኬንያ ዘመቻ በሶማሊያ
ሰኞ፣ ሰኔ 25 2004ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ ቡድን ባይኖርም ኬንያ የምትጠረጥረው አሸባብን ነው።
ትናንት በኬንያ ጋሪሣ ከተማ በተጣለው ፈንጅ ቢያንስ 17 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። እንደዚህ አይነቱ በዓብያተ-ክርስቲያን ላይ የተጣለ ጥቃት ምን ያመላክታል? በአለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም- ISS የሶማሊያ ተንታኝ -ኢማኑኤል ኪሳንጋኒ
« ቀደም ሲል በውጭ አገር ዜጎች ላይ ነበር ጥቃት የሚጣለው። ነገር ግን ኬንያ ጣልቃ ከገባች በኋላ ተራ ኬኒያውያን ኢላማ የሚሆኑበት አዲስ የጥቃት አቅጣጫ ይታያል። ። እና ጥቃቱ በዓብያተ ክርስትያን ላይ መጣሉ የሚያመላክተው የአሸባብ ደጋፊዎች ወይንም አሸባብ ራሱ በሶማሊያ ያለውን ግጭት ልክ በክርስትያን እና ሙስሊሞች መካከል እንዳለ ግጭት አድርጎ ለማጠቃለል መሞከሩን ያመላክታል። እንደሚመስለኝ የትናንትነው ጥቃት ለዚህ ማረጋገጫ ይሆናል።»
ኪሳንጋኒ እንዳሉት ሁሉ በርካታ ተንታኞችም ኬንያ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ካዘመተች በኋላ አሸባብ ጥቃት ሊጥልባት እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር። ለሶማሊያ ድንበር ቅርብ በሆነችው የኬንያ ጋሪሣ ከተማ እንዲሁም በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ አካባቢ በተደጋጋሚ አሸባብ ከዚህ ቀደም ጥቃቶች አድርሷል።
« በነዚህ በተወሰኑ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃት ከዚህ ቀደም ሲጣል ነበር። ያሁኑ ግን ከሁሉም ትልቁ ነው። የኬንያ በግልፅ ጣልቃ መግባት ጥቃቱ እንዲደርስ አድርጓል። ስለዚህ አስገራሚ አይደለም። ይሁንና ሰዎች እንደዚህ ቁጥሩ ከፍ ያለ 17 አሁን ደግሞ 18 ሰዎች የሞቱበት ጥቃት በዓብታተ ክርስትያን ላይ ይጣላል ብለው አልጠበቁም።»
ኬንያ ባለፈው ጥቅምት ወር አክራሪውን የዓማፂ ቡድን አሸባብን ለመውጋት ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ካሻገረች ወዲህ በተደጋጋሚ የጥቃት ዒላማ ሆና ቆይታለች። በኃገሪቷ ጠንካራ የሆነ የደህንነት ጥበቃ የለምን? ኪሳንጋኒ?
« ሰዎች የወንጀል መርማሪው ክፍል የብሔራዊ ፀጥታ መ/ቤት የት ናቸው? ምን እየሰሩ ነው? እንዴት እንደዚህ አይነቱን ነገር ሊከላከሉ አልቻሉም ይላሉ። ሆኖም ሁላችንም እንደምናውቀው አንዳንዴ የሽብር ጥቃቶችን መከላከል ከባድ ነው። አስቀድመው ስለ ጥቃቱ አይናገሩም። በተጨማሪ የእያንዳንዱን ዜጋ ደህንነት በተናጠል ማስጠበቅ አዳጋች ነው። ምክንያቱም ብዙ የፖሊስ ወታደሮች አስፈላጊ ናቸውና። በዮናይትድ እስቴትስ የመስከረም አንዱን ጥቃት ተመልክተናል። ያ ሁሉ ቴክኖሎጂ ያላት አሜሪካም ተጠቅታለች።»
ስለሆነም ይላሉ ኪሳንጋኒ ኬኒያውያን መንግስት ለደህንነት የበለጠ ትኩረት ይስጥ የሚሉት አግባብ ነው ይሁንና እንደዚህ አይነቱን ጥቃቶች ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም ከባድ ነው።
አሸባብን ለመዋጋት የጦር ኃይሏን የላከችው ኬንያ ብቻ አይደለችም። እንደ ኢትዮጵያ እና ዮጋንዳ የመሳሰሉ አገሮች ጦራቸውን ወደ ሶማሊያ ልከዋል። በተደጋጋሚ ግን ጥቃት ሲጣል የሚታየው በኬንያ ላይ ነው ለምን? ኪሳንጋኒ መልስ ሰተውናል።
«ቁጥራቸው ከፍ ያለ ኢትዮጵያውያን ለረዥም ጊዜ ሶማሊያ ውስጥ ነበሩ። የኢትዮጵያ ወታደሮች ከ2006 ዓ ም አንስቶ ወደ ሶማሊያ የእስላማዊ ኃይል ህብረትን ለመዋጋት ዘምተዋል። በጊዜ ብዛት ሊደርስ ከሚችል ማንኛውም ጥቃት ራሳቸውን መጠበቅ ችለዋል። ዮጋንዳ ላይ በ2010ሩ የአለም ዋንጫ ጊዜ አደጋ ተጥሎ ነበር።»
ልደት አበበ
ሒሩት መለሰ