1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ምርጫ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደረገ

ዓርብ፣ ነሐሴ 26 2009

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ወር የተከናወነውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ውድቅ አደረገው። ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያሸነፉበትን ምርጫ ሕገ-መንግሥቱን የጣሰ በማለትም ነው ፍርድ ቤቱ በ60 ቀናት ውስጥ አዲስ ምርጫ እንዲከናወን የወሰነው።  በውሳኔው የተደሰቱት ተቃዋሚዎች ምርጫ ቦርዱ ዳግም ምርጫ የመጥራት የሞራል ልዕልና የለውም ብለዋል።

https://p.dw.com/p/2jE8u
Kenias Oberstes Gericht
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Azim

በምሥራቅ አፍሪቃዋ ኬንያ ባለፈው ወር የተከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድቅ መደረጉን ያወደሱት ተቃዋሚዎች የምርጫ ኮሚሽኑ አባላት ለፍርድ መቅረብ አለባቸው አሉ። በሀገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድቅ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው።  ባለፈው ነሐሴ 2 ቀን፣ 2009 ኬንያ ያከናወነችውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዑሁሩ ኬንያታ አሸንፈዋል መባሉ ሀገሪቱ በተቃውሞ ሰልፍ እንድትናጥ አድርጎ ሰንብቷል። 

በእንግሊዥኛ ምኅጻሩ (IEBC) የሚሰኘው ነጻ የምርጫ እና ድንበሮች ኮሚሽን አባላት ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ወንጀለኞች ናቸው ሲሉ የዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲው ናሳ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ዛሬ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል። የአማኒ ብሔራዊ ኮንግሬስ (ANC) ፓርቲ መሪ ሙሳሊያ ሙዳቫዲ በበኩላቸው ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፦ ምርጫ ኮሚሽኑ ተአማኒነትም ሆነ ቀጣይ ምርጫ የማከናወን የሞራል ልዕልና እንደሌለው ገልጠዋል።

«እጅግ አጥብቀን ልንናገር የምንፈልገው ምርጫ ኮሚሽኑ ሌላ ምርጫ የማስፈጸም ዕድል እንደማይገባው ነው። ምክንያቱም እነሱ አሠራራቸው ተበላሽቷል፤ በወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፈዋል፤ የሚንቀሳቀሱትም ከህገመንግሥቱ ውጪ ነው ። ስለዚህ አዲስ ምርጫ የማስፈጸም የሞራል ልእልናው የላቸውም።»

የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ፍቅረማርያም መኮንን በኬንያ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች በደስታ አደባባይ መውጣታቸውን ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ እና ደጋፊዎቹም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በፀጋ መቀበላቸውን አክለው ገልጠዋል። 

«በተቃዋሚም ሆነ በፕሬዚዳንቱ ወገን ያሉትም  ቀደም ብለው የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚቀበሉ ሲገልጡ ቆይተዋል። አሁን በዛሬው እለትም የሆነው እንደዚህ ነው። የፕሬዚዳንቱ ጠበቆች ምንም እንኳን ውሳኔው ፖለቲካዊ ውሳኔ ቢመስልም  የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ስለሆነ፤ የመጨረሻ እና ይግባኝ የሌለው ስለሆነ እንቀበለዋለን፤ በአዲስ ምርጫም ዕጩዎቻችን ተሳትፈው እንደገና እንዲያሸንፉ ጥረት ያደርጋሉ ብለዋል። በተቃዋሚዎች በኩል ከፍተኛ ደስታ ነው የሚታየው። የናይሮቢን ጨምሮ፤ በሞንባሳ፣  በኪሲሙ በመሳሰሉ ደጋፊዎቻቸው ባሉባቸው የተለያዩ ከተሞች በከፍተኛ ደረጃ ደስታቸውን እየገለጡ ነው።»
ራይላ ኦዲንጋ የሚመሩት የኬንያው ብሔራዊ ከፍተኛ ጥምረት (NASA) ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ (ANC)መሪው ሙሳሊያ ሙዳቫዲ የዛሬውን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ታሪካዊ ብለውታል።

Kenia Unterstützer von Raila Odinga jubeln nach der Gerichtsentscheidung zu neuen Wahlen
ምስል Reuters/T. Mukoya

«እጅግ በጣም እፎይታ ተሰምቶናል። ውሳኔውም ታሪካዊ ነው። ምክንያቱም የሚታየው ነገር የሚያመለክተው ዲሞክራሲ ኬንያ ውስጥ ተደፍልቋል ስንል መክረማችን ሙሉ ለሙሉ ትክክል እንደነበረ ነው።»
የኬንያ የምርጫ ኮሚሽንን ጨምሮ ምርጫው ተጭበርብሯል ሲባል በቸልታ ተመልክተዋል ያሏቸው የውጭ ሃገራት የምርጫ ታዛቢዎችንም የዛሬው ውሳኔ «እፍረት ውስጥ የሚጥላቸው ነው» ብለዋል።

Kenia Raila Odinga mit Unterstützern nach der Gerichtsentscheidung zu neuen Wahlen
ምስል picture alliance/AP Photo/B. Curtis

ደጋፊዎቻችን በተረጋጋ መንፈስ ኹነው ለቀጣዩ ምርጫ መዘጋጀት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የምርጫ ታዛቢዎችና የምዕራብ ሃገራት ባለሥልጣናት የተቃዋሚ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ሽንፈታቸውን በጸጋ እንዲቀበሉ አሳስበው ነበር። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንቱ አሸነፉ የተባለበትን ምርጫ ውድቅ ማድረጉን የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎችም ተቀብለውታል። 

«በመንግሥት ደጋፊዎች በኩል የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና የመገናኛ አውታሮች እንደሚዘግቡት  ከሆነ ውጤቱን ተቀብለዋል። ምንም እንኳን በውሳኔው መከፋት ቢኖርም የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት  የወሰነው ስለሆነ፤ በአይነቱም የመጀመሪያው ውሳኔ ስለሆነ መከፋቱ ቢኖርም ምንም አይነት ረብሻ የለም፤ ብጥብጥም እስካሁን አልተከሰተም ። ሕዝቡ እንደገና ወደ ምርጫ ጣቢያ ሄደን  በታዘዝነው መሠረት እንደገና እንመርጣለን የሚል  አጠቃላይ መንፈስ እንዳለ ነው መረዳት የቻልኩት።»

የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ባይስማሙበትም እንኳ እንደሚያከብሩት ከመዲናዪቱ ናይሮቢ ኾነው በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ወትሮ የምርጫ ስርአት የብጥብጥ እና የግድያ ሰበብ ሆኖ በሚስተዋልበት የምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ እና የፖለቲከኞቹ ድርጊት በርካቶችን አስደምሟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ