1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ምርጫና ያስከተለው የከፋ ቀውስ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 27 2000

የኬንያ ምርጫ መጭበርበርና ምናልባትም ተቃዋሚው ወገን አዲስ ፕሬዚደንት የመሰየም ድሉን መነጠቁ ብዙዎች እንደገና አፍሪቃ ውስጥ ምርጫ መካሄዱ ምን ጥቅም አለው የሚል ጥያቄን እስከማንሣት እንዲደርሱ ነው ያደረገው። አፍሪቃና ምርጫዎቿ፤ ጉዳዩ እንደገና አጠያያቂ መሆኑ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/E0Zy
ፕሬዚደንት ኪባኪ
ፕሬዚደንት ኪባኪምስል AP/Presidential Press Services

በዕውነትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክፍለ-ዓለሚቱ ምርጫ ተብዬ ምርጫዎች የባለድምጹ ሕዝብ ፍጋጎት መግለጫ በመሆን ፋንታ በተከታታይ ሕልምን ወደ ቅዠት መለመጣቸው ለብዙ ጥያቄዎች መንስዔ የሚሆን ነው። የአፍሪቃ መሪዎች ቀንቶኝ ካሸነፍኩ ሥልጣኔን የዴሞክራሲ ልባስ ላጎናጽፈው ካልቀናኝ ደግሞ ንቅንቅ ላልል በሚል የሚያካሂዱት ምርጫ መዘዙ ቀላል አልሆነም። መብታችሁ ነው፤ አደባባይ ወጥታችሁ ምረጡ የተባሉ ዜጎች ድምጻችን ይከበር ማለታቸው ከአንዴም ብዙ ጊዜ እንወንጀል ተቆጥሮባቸው ተገድለዋል። በፍርድም ሆነ በምርጫ ሥርዓቱ ላይ ዓመኔታ እንዲያጡ ተገደዋል። አፍሪቃ በ 21ኛው ምዕተ-ዓመት! ዕድገቷ በዴሞክራሲና በማሕበራዊ ፍትህ እጦት ታፍኖ፤ ተተብትቦ እንደቀጠለ ነው።

የኬንያ ፕሬዚደንታዊና ምክርቤታዊ ምርጫ ያለፈው ሐሙስ ሣምንት ተጣምሮ ሲካሄድና በዋዜማው ከብዙዎች፤ በተለይም ከአካባቢው መንግሥታት ሲነጻጸር የተሻለ ዕርጋታ በሚታወቅባት አገር የሰሞኑ አስደንጋጭ ዓመጽ በዚህ መጠን ይከሰታል ብሎ የጠበቀ ብዙ አልነበረም። ምርጫው ሲካሄድ በማግሥቱ አርብ ምሽት የመጀመሪያው ይፋ ውጤት ይቀርባል ነበር የተባለው። ግን አልሆነም። እርግጥ ተቃዋሚው ወገን ያሸነፈበት የም/ቤት ምርጫ ውጤት አልዘገየም። የፕሬዚደንትነቱ ድምጽ ግን ታፍኖ ቆየ። የተቃዋሚው ወገን ዕጩ ራኢላ ኦዲንጋ ከጅምሩ እንደሚመሩ ፍንጭ እየተሰጠ፤ በሰፊው አደባባይ ወጥቶ ድምጽ የሰጠው መራጭም ውጤቱን ትዕግሥት አጥቶ እየተጠባበቀ ከሰነበተ በኋላ ባለፈው ዕሑድ ብሄራዊው አስመራጭ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ኪባኪን ከኋላ እንዴት እንደደረሱ ባይታወቅም አሸናፊ ብሎ አወጀ።

ኪባኪ ውጤቱ እንደተገለጸ ቃለ-መሃላ ለመግባት ምንም ጊዜ አልፈጀባቸውም። በዚያ ላይ ድምጽ ቆጠራው በአግባብ መካሄዱን አጠያያቂ ያደረጉት የኦዲንጋ መራጮች ወይም ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች ብቻ አልነበሩም። ኬንያ ውስጥ በጠቅላላው ፕሬዚደንት ኪባኪ የምርጫውን ውጤት ለራሳቸው እንዲመች አድርገው መደለዛችውን የሚጠራጠር የለም። ሌላው ቀርቶ ባለፈው ዕሑድ የኪባኪን ማሸነፍ በይፋ ያስታወቁት የምርጫው ሃላፊ ሣሙዔል ኪቩኢቱ እንኳ የኋላ ኋላ ከመንግሥት በኩል ብርቱ ተጽዕኖ እንደተደረገባቸው አልሸሸጉም። የምርጫው ሃላፊ ራሳቸው እርግጠኛ ያልሆኑበትን ድል ታዲያ ተራው ዜጋ እንዴት አምኖ ይቀበለው።

ለማንኛውም የተቃዋሚው ወገን ድል መነጠቅ አገሪቱን አስፈሪ ከሆነ ዓመጽ ላይ ለመጣል ጊዜ አልወሰደም። ባለፈው ማክሰኞ የዘመን መለወጫ ዕለት በምዕራባዊቱ የኬንያ ከተማ በኤልዶሬት አንድ ቤተ-ክርስቲያንን ተገን ያደረጉ ብዙ ሕጻናትና ሴቶች ቁጣቸው የገነፈለ ሰዎች ባቀጣጠሉት እሣት በሕይወታቸው ይጋያሉ። ይህ ድርጊት ከሁሉም ባላይ ነው የኬንያን ገጽታ የቀየረው። በማግሥቱ ረቡዕ መንግሥትና ተቃዋሚው ወገን በዚህ ምርጫው ባስከተለው የከፋ ፍጅት አንዱ ሌላውን ተጠያቂ በማድረግ ሲወናጀሉ ከሰላሣ የሚበልጡ ሰዎች የነደዱበት የኤልደሮት ቤተ-ክርስቲያን ቃጠሎ ዓመድ ጋና ትኩስ ነበር። ዓመጹ ጋብ አለ እንጂ ጨርሶ አላበቃም። ምርጫውን ተከትሎ በፈነዳው ቁጣ ሳቢያ እስካሁን የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ 350 የሚበልጥ ነው።
ያለፉት ሁለት ቀናት ምዕራባውያን መንግሥታት ከአሜሪካ እስከ ብሪታኒያ ዓመጹ እንዲቆምና ተቀናቃኙ ወገኖች ችግሩን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪና ግፊታቸውን ያጠናኩሩባቸውም ናቸው። የአፍሪቃ ሕብረት ተጠሪዎችም ለበኩላቸው የሽምገላ ጥረት ወደ ናይሮቢ መዝለቃቸው አልቀረም። ከትናንት በስቲያ ናይሮቢ የገቡት የደቡብ አፍሪቃው የኖቤል ሰላም ተሸላሚ ዴስሞንድ ቱቱ ደግሞ ከተቃዋሚው ወገንና ከመንግሥት ጋር ተነጋግረዋል። ቱቱ የጋናውን ፕሬዚደንት ጆን ኩፉርን በሸምጋይነት ለመሰየም ከአሜሪካና ከአውሮፓ በቀረበው ሃሣብ ከራኢላ ኦዲንጋ ጋር ለሁለት ሰዓታት ተነጋግረዋል። በንግግሩ መርካታችውንም ነው የገለጹት። ችግሩ የኪባኪ መንግሥት የኩፉርን ሸምጋይነት ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ ነው። ኬንያ ውስጥ ዓመጹ እንዲበርድና ሰላም እንዲሰፍን ምርጫው አንድ ብቻ ይሆናል። ድምጽ እንደገና ተቆጥሮ አሸናፊው በውል እንዲጣራ ማድረግ ወይም አዲስ ምርጫ ማካሄድ!