1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከሸፈው የአይቨሪ ኮስት መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አንደኛ ዓመት

ዓርብ፣ መስከረም 8 1996
https://p.dw.com/p/E0lQ

በአይቨሪ ኮስት ፕሬዚደንት ሎውሮ ግባግቦ አንፃር ከአንድ ዓመት በፊት፡ መስከረም አሥራ ዘጠኝ፡ 2003 ዓም የተካሄደውና የከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፡ ይህችው የምዕራብ አፍሪቃ ሀገር ባካባቢው መረጋጋትና ብልፅግና የሠፈነባት ደሴት ትባል የነበረበትን ጊዜ አብቅቶዋል። የኤኮኖሚውን ተዓምር ገሀድ በማድረግዋ እንደምሳሌ ትጠቀስ በነበረችው አይቨሪ ኮስት ውስጥ እአአ ከ 1990 ኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ወዲህ በምርጫ ወቅት የታየው የማጭበርበር ሙከራ እና ከሀገሪቱ መሥራች አባት ሑፌት ቡዋኜ ሞት በኋላ የተፈጠረው ምስቅልቅል ሁኔታ፡ እንዲሁም፡ ብሔረተኞች በሀገሪቱ ያስፋፉት አክራሪው ርዕዮት ባንድነት ለከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሁኔታዎችን አመቻችተዋል።

ከዓምናው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ምንም እንኳን ተደጋጋሚ የሰላም መግለጫዎች ቢወጡም፡ አይቨሪ ኮስት አሁንም ገና መፍትሔ ባልተገኘበት የውዝግብ ሁኔታ ውስጥ እንደተዘፈቀች ነው የምትገኘው። አይቨሪ ኮስት ዓማፅያኑ በሚቆጣጠሩት ሰሜናዊው እና ፕሬዚደንት ሎውሮ ግባግቦ የሚመሩት የዕርቀ ሰላም መንግሥት በሚቆጣጠረው ደቡባዊ አካባቢዎች ተከፋፍላለች። አራት ሺህ ወታደሮች የሚጠቃለሉበት የፈረንሣውያኑ ጦር በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል አንድ ከጥቃት ነፃ የሆነ ቀጠና በማቋቋም፡ አንድ ሺህ አምስት መቶ ከሚሆኑ የምዕራብ አፍሪቃ ሰላም አስከባሪ ጓድ ወታደሮች ጋር ባንድነት ለአይቨሪ ኮስት የተደረሰውንና ብዙም አስተማማኝ ያልሆነውን የተኩስ አቁም ደምብ በመቆጣጠር ላይ ይገኛል።

በአይቨሪ ኮስት የተነቃቃው የሰላም ሂደት እጅግ አዝጋሚ ቢሆንም፡ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ርምጃዎች ተንቀሳቅሰዋል። ከነዚህም መካከል በፈረንሣይ ግፊት ባለፈው ጥር ወር በፓሪስ አቅራቢያ የአይቨሪ ኮስት ተቀናቃኝ ወገኖች አንድ የሰላም ውል የተፈራረሙበት ድርጊት አንዱ ነው። በዚሁ ፕሬዚደንት ሎውሮ ግባግቦ እና ደጋፊዎቻቸው ከልብ ባልተቀበሉት የሰላም ስምምነት መሠረት፡ የአይቨሪ ኮስት ፓርቲዎች በጠቅላላና ዓማፅያኑ ጭምር የተጠቃለሉበት አንድ የዕርቀ ሰላም መንግሥት ባለፈው መጋቢት ተመሥርቶዋል፤ በውዝግቡ ለተፋለሙት ወገኖች በጠቅላላ ምሕረት ሰጪው ሕግም ወጥቶዋል። ተፋላሚዎቹ ወገኖች ባለፈው ሐምሌ ወር የርስበርሱ ጦርነት በይፋ እንዳበቃ ያስታወቁበትን ድርጊት ተከትሎም፡ ባለፈው ጳጉሜ አምስት አይቨሪ ኮስትና ቡርኪና ፋሶን የሚያዋስነው ድንበር እንደገና ተከፍቶዋል።

ምንም እንኳን እነዚህ ርምጃዎች አዎንታዊ ቢሆኑም፡ የሰላሙ ሂደት፡ በሀገሪቱ አሁንም ገና ባልተወገዱ በርካታ መዋቅራዊ ችግሮች የተነሣ ገና አስተማማኝ ሊሆን አልበቃም። በጎኦረቤት ሀገሮች መካከል፡ እንዲሁም በአይቨሪ ኮስት ተፋላሚ ወገኖች መካከል አለመተማመኑ አሁንም ሥር እንደሰደደ ነው የሚገኘው። ፕሬዚደንት ግባግቦ የሀገሪቱን የመከላከያ እና የፀጥታ ሚንስቴሮችን ሥልጣን እንዲይዙ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከጥቂት ሣምንታት በፊት የሾሙዋቸውን ባለሥልጣናት የዓማፅያኑ እንቅስቃሴዎች ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑበት ድርጊት በተቀናቃኞቹ ቡድኖች መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት የሚጠቁም ምልክት ሆኖዋል።

ያለፈው ዓመቱን የከሸፈ የእቨሪ ኮስት መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ግለሰብ እንደገና በግባግቦ አንፃር አዲስ ሤራ አቅደዋል በሚል ጥርጣሬ ባለፈው ነሐሴ መጨረሻ ገደማ በፓሪስ ታሥረው ነበር፤ ይሁንና፡ አንድ የአይቨሪ ኮስት ፍርድ ቤት በዚህ ሣምንት ግለሰቡ በነፃ እንዲለቀቁ ወስኖዋል። በሀገሪቱ የጎላው የጎሣና የሀይማኖት ልዩነት፡ የባዕዳን ሙያተኞች አሀዝ መበራከት ያስከተለው ምሬት፡ እንዲሁም፡ አከራካሪው የዜግነት ጥያቄ፡ እንዲሁም አድልዎ የበዛበት የሀገሪቱ የምርጫ እና የመሬት ባለቤትነት መብት ጉዳይ አይቨሪ ኮስት ከፖለቲካዊው መረጋጋት ብዙ ርቃ እንደምትገኝ እና ልትከፋፈል የምትችልበትም ሥጋት እንደተደቀነባት አሳይቶዋል። ካለ ፖለቲካ መረጋጋት ደግሞ ኤኮኖሚዋ ሊያገግምና ዕድገት ሊያስገኝ አይችልም። ታድያ ላካባቢው ኅልውና ወሳኝ የሆነውና በጦርነቱ ሰብብ ተቋርጦ የነበረው የንግዱ መንገድ አሁን የአይቨሪ ኮስትና የቡርኪና ፋሶ ድንበር መልሶ በተከፈተበት ሁኔታ እንደገና ይዳብራል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል። የአይቨሪ ኮስት የግዛት ሉዓላዊነት እንደተጠበቀ እንዲቆይ የምትሻው ፈረንሣይ በሀገሪቱ መረጋጋት እስኪሠፍን ድረስ ወታደሮችዋን በዚችው የምዕራብ አፍሪቃ ሀገር ውስጥ እንደምታቆይ አስታውቃለች።