የኦጋዴን ችግርና የቀድሞዉ የአካባቢዉ ወጣቶች መሪ
ረቡዕ፣ ጥር 8 2005
የሶማሊያ መሥተዳድር ልዩ ፖሊስ ሠላማዊዉን ሕዝብ እንደሚበድል፥ ሠብአዊ መብት እንደሚጥስ እና እንደሚዘርፍ የቀድሞዉ የሶማሌ መስተዳድር የወጣቶች ፌደሬሽን ሊቀመንበር እና የመስተዳሩ አምደ-መረብ (ኢንተርኔት) ሐላፊ አስታወቀ።በቅርቡ ከሐገር የወጣዉ ወጣት አብዱላሒ ሁሴን እንደሚለዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በአሸባሪነት ወንጀል ተፈርዶባቸዉ በይቅርታ በተለቀቁት ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች ላይ ቀርቦ የነበረዉን የቪዲዮ መረጃም በመስተዳድሩ ልዩ ፖሊስ የተዘጋጀ «የሐሠት ፊልም» ብሎታልም።የኢትዮጵያ መንግሥት ኦጋዴን ዉስጥ ሠላም ለማስፈን ከፈለገ ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦብነግ) ጋር እንዲደራደርም ወጣቱ መክሯል።
የብሪታንያ መንግሥት በቅርቡ ሶማሌ መስተዳድር ለሠፈረዉ ልዩ ፖሊስ ማሠለጠኛ እስከ አስራ-አምስት ሚሊዮን ፓዉንድ የሚደርስ እርዳታ ለመስጠት መዘጋጀቱ የመብት ተሟጋቾችን ተቀዉሞ ቀስቅሷል።አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና ሑዩማን ራይትስ ዋችን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት የብሪታንያ መንግሥት ይረዳዋል የተባለዉ ልዩ ፖሊስ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚፈፅም ሐይል ነዉ።
የብሪታንያ መንግሥት ርዳታዉ ለልማት እንጂ መብት ይረግጣል ለተባለዉ ሐይል አይዉልም ባይ ነዉ።አብዱላሒ ሁሴይን ግን የመብት ተሟጋች ድርጅቶቹን ሐሳብ ነዉ-የሚጋራዉ።
የሶማሌ መስተዳድርን በመወለድ፥ ማደግ እና በመኖር ጠንቅቆ ያዉቀዋል።የአካባቢዉን ፖለቲካዊ ዉጥንቅጥ የሚያዉቅበት መንገድ ደግሞ ብዙ ነዉ።የሶማሌ መስተዳድር የወጣቶች ፌደሬሽን ሊቀመንበር፥ የኢትዮጵያ የፌደራል ወጣቶች ማሕበር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልም ነበር። በመስተዳድሩ ፕሬዝዳት ቢሮ የሚዘጋጀዉ «ሐካራ ኒዊስ» የተሰኘዉ አምደ-መረብ ሐላፊም ነበር።
እስከተሰደደበት ድረስ የኖረበትን፥የኦጋዴንን ችግር-ለማቃለል ብልሐቱ ሁለት ነዉ-ባይ ነዉ-አብዱላሒ።በወጣትነት እድሜዉ «በቂ» የሚባል ሥልጣን፥ሥራዉን ምናልባትም ጥሩ ገቢ፥ ሐገር ኑሮዉን ትቶ ለመሰደዱ ምክንያት-የሚለዉ ብዙ ነዉ።ዋናዉ ግን በኦጋዴን ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉ በደልና የሹማምንታቱ አሰልቺ «ዉሸት» ናቸዉ ይላል።
ከሐገር ሲወጣ ከቋጠራቸዉ ሰነዶች መሐል ኢትዮጵያ ዉስጥ በአሸባሪነት ወንጀል እያንዳዳቸዉ አስራ-አንድ ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዉ በነበሩት ሁለት የሲዊድን ጋዜጠኞች ላይ በመረጃነት ቀርቦ የነበረዉ ቪዲዮ አንዱ ነዉ።
ሐምሌ-ሁለት ሺሕ ሰወስት ኦጋዴን ዉስጥ የተያዙት ዮሐን ፔርሰንና ማርቲን ሺብዬ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በሕገወጥ መንገድ መሆኑ አላነጋገረም።እነሱም አልካዱምም።የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ከሚለዉ ከኦብነግ ታጣቂዎች ጋር ማበራቸዉን፥ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር መታኮሳቸዉን የሚያሳዉ ፊልም ግን አብዱላሒ እንደሚለዉ የሐሰት ነዉ።
ሁለቱ ጋዜጠኞች የ«ሐሰት» የተባለዉን ቪዲዮ በሐራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች አሰራጭተዉታል።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ