1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ረቡዕ፣ ኅዳር 28 2009

በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ተቃዉሞ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ለደህንነታቸዉ በመስጋት አካባቢያቸዉን ጥለው ወደ ጎረቤት ኬንያ፣ ሱዳንና ግብፅ ተሰደዋል።

https://p.dw.com/p/2TuzQ
Symbolbild Flüchtlingsboot
ምስል Getty Images/G. Bouys

Oromo-Refugee Crisis in Cairo - MP3-Stereo

ከነዚህ መካከል በካይሮ፣ ግብፅ የሚገኙት የተገን ማመልከቻ ያስገቡት ስደተኞች የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት በምፃሩ UNHCR አድሎ አድርሶብናል ብሎ መክሰሳቸዉን ሮይቴርስ ትላንትና ባወጣዉ ዘገባ አመልክተዋል። በዚህም የተነሳ በህገ ወጥ መንገድ በሜድትሬንያን ባህር በኩል አድርገው ወደ አዉሮጳ ለመምጣት ሲሞክሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸዉን ማጣታቸዉን ዘገባዉ ይጠቅሳል።

ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ካይሮ መሰደዳቸውን የገለጹት አቶ ጣሶ ጣቡር ለUNHCR ያስገቡትን የተገን ማመልከቻቸውን ጉዳይ እየተከታተሉ መሆኑን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። መስሪያ ቤቱ ለስደተኞቹ ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም ይላሉ፣ «እዉነቱን ለመናገር በዚህ አገር ያለው UNCHR የኦሮሞን ጉዳይ ይመለከታል ለማለት ይከብዳል። ምክንያቱን ባላዉቅም፣  የኦሮሞ ችግር መስሎ አልታያቸውም። ግን እንደሚመስለኝ፣ ባሁኑ ሰዓት የኦሮሞ ተወላጆች መቸገራቸዉ፣ በአገር ቤት እየሞቱ ባለበት ሰዓት፣ UNHCR ጉዳያችን ለምን እንዳማይቀብል ነዉ ያልገባኝ። የናንቴ የተገን ጥያቄ ተቀባይነት የለዉም በሚል የብዙ ስድተኞችን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል።»

ከየካቲት ወር ጀምሮ በካይሮ እንደሚገኙ ለዶይቸ ቬለ የተናገሩት ፍስሃ ብራሳ የተባሉት ሌላ ተገን ጠያቂ ለUNHCR ቃሉ እንደሰጠ እና ልስ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን  ይናገራል። በኢትዮጵያ  ከእስር ከተለቀቁ እና በኦሮሚያ ተቃዉሞ ከተጀመረም በኋላም በደህንነት ሰዎች ብዙ ማስፈራሪያዎች እንደደረሱባቸውስደርስብኝ ነበር ይላሉ። መስርያቤቱ ላለፉት ጥቅት ወራቶች በኢትዮጵያ የምከሰተዉን በዘገባ መስማት ከጀመሩ በኋላ የተወሰኑ ሰዎችን ለቃለ መጠይቅ መጥራት መጀመራቹዉን ጠቅሰዋል።

ግን አሁንም ቀጥለዋል ያሉትን ችግር እንድህ ያብራራሉ፣ « አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ችግሩን ለመናገር ወደ UNHCR ቢሄድም በዚያ ብርድ እገረፈው ወረፋ ቢጠብቅም፣ ተራዉ ስለማይደርሰው ተመልሶ ይገባል ማለት ነዉ። ይህ  UNHCR ችግር እንዳለበት ያሳያል። ብዙ ሰዎች ተቸግረዋል። እናቶች እና  ትልቅ ችግር ያለባቸዉ ሰዎች ችግራቸዉን የሚያቀርቡበት መንገድ የለም፣ በፍጹም ትኩረት አይሰጡም። ከደህንነት ሸሽቶ የመጣዉን ሰዉ  የሚያስቀምጡበት ቦታ የለም፣ ሶስተኛ አገር ለማፈላለግም ተነሳሽነት የላቸዉም። በጣም ደካማ አሰራር ስላለ፣ እግዚአብሄ ይጠብቀኝ ብሎ መኖር ብቻ ነዉ።» 

በካይሮ የሚገኘዉ UNHCR መስርያቤት የኮሙኒኬሼን ባለሙያ የሆኑት ታሪቅ አርጋዝ መስሪርያ ቤታቸዉ የሚከተላዉ ደንብ እንዳለ ጠቅሰው ጉዳዮች ለምን እንደሚዘገይ አስረድተዋል።

«አሁን እየመዘገብን ያለነዉ ብዙ ቁጥር ያላቸዉ ስድተኞችን ነዉ። ማመልከቻ የሚያዝገቡ ስደተኞች ቁጥር ከባለፈዉ ዓመት ጀምሮ እየጨመረ ነዉ። በዚህ ሁኔታ ዉስጥም ሆነን ከማመልከቻ ማስገባት እስከ የስደተኝነት ሁኔታ ማረጋገጫ ድረስ የነበረዉ የመጠበቂያ ግዜ ከ 28 ወር ወደ 16 መቀነስ ችለናል። እዉነት ነዉ መጀመርያ ላይ አካሄዴ ዘገምተኛ ነበር። ምክንያቱም ብዙ አመልካቾች ስለነበሩና ይህን ስራ የሚሰሩ ሰዎችን ለመቅጠር የበጀት ችግር ነበረን።»

ከስርያውያን እና ከሱዳናውያን ቀጥሎ ከኢትዮጵያ የሚመጡ ስድተኞች ሶስተኛ ደረጃ እንደ ያዙ ታርቅ ተናግረው ከ67 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ከኦሮሚያ ክልል እንደሚመጡም ለዶይቸ ቬለ ይናገራሉ። ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ UNHCR ከኢትዮጵያ የመጡትን 11, 685 ሰዎችን እንደመዘገበ ተናግሮ ይህም ከባለፉት ዓመት ጋር ካወዳደርነዉ በሁሉት እጅ መጨመሩን ገልጾዋል።

መርጋ ዮናስ

አረያም ተክሌ