1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስራኤልና የፍልስጤም ድርድር

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2006

ለመወቃቀስ መካሰሱ ምክንያቱ በሁለቱም ወገን ሞልቶ ተርፏል።ጎልቶ የወጣዉ ግን ሁለት ነዉ። እስራኤል ፀጥታዬ-መከበር አለበት ትላለች።በዚያ ላይ በሐይል በያዘችዉ የፍልስጤሞች ግዛት የአይሁድ ሠፈራ መንደር ማስገንባቷን መቀጠል ትፈልጋለች።

https://p.dw.com/p/1Ajol
ምስል DW/T. Krämer

የእስራኤል እና የፍልስጤም ተደራዳሪዎች ባለፈዉ ሐምሌ አደረጉት በተለዉ ዉል መሠረት እስከ መጪዉ ሚያዚያ ድረስ ከሁነኛ ሥምምነት ላይ መድረስ አለባቸዉ።እርግጥ ነዉ ሁለቱ ወገኖች ሠሞኑን በዩናትድ ስቴትስ በኩል ተዘዋዋሪ የሐሳብ ልዉዉጥ ጀምረዋል።ከዚሕ ባለፍ ግን በአሜሪካኖች ግፊት እንዳዲስ ተጀመረ የተባለዉ ቀጥታ ድርድር እንደተቋረጠ ነዉ።ለድርድሩ መቋረጥ አንዱ ሌላዉን ከመዉቀስ በስተቀር ድርድሩን ፈጥነዉ የመቀጠል ፍንጭ እንኳ አላሳዩም።እስከ ሚያዚያ ባለዉ አራት ወር ዉስጥ ድርድሩ ዳግም ቢጀመር እንኳን ሐምሌ ላይ እንደታሰበዉ ከአግባቢ ሥምምነት መድረሳቸዉ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

የአሜሪካ ፖለቲከኞች ወደ ሥልጣን ሲመጡ እያነሱ፥ ሲሔዱ የሚጥሉት የእስራኤል ፍልስጤሞች ድርድር ባለፈዉ ሐምሌ ሊጀመር ነዉ ሲባልለት፥ እንዲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ እንደ ብዙ ቀዳሚዎቻቸዉ ሥልጣን ሲይዙ አነሱት ከማሰኘት እንደማያልፍ ለቅርብ ታዛቢዎች ግልፅ ነበር።ከሐምሌ-እስከ አሁን የተቆጠሩት ወራት ደግሞ የታዛቢዎችን የያኔ እምነት፥ አስተያየት እዉነት አስመሠከሯል።ሥምምነት አይታሰብም።ድርድር የለም።ጊዜዉ ግን ጊዜ እየተካ ይሔዳል።

ያ ምድር እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ከ1948 ጀምሮ የሠላም-ጦርነት፥ የድርድር-ግጭት አዋጅ ሲፈራረቁበት፥ላሰላ ስልሳ-ሰባት ዘመን ተጠናቀቀበት።ከዘንድሮ-ሐምሌ እስካሁን ስድስት ወር ቢታከልበት በርግጥ የሚደነቅ-የሚቆጭም የለም።የፍልስጤሙ ዋነኛ ተደራዳሪ ሰዓብ ኢርቃት ታዛቢ ለማስደነቅ-ማስቆጨት ያለሙ ይመስል ተዘዋዋሪ ድርድር ቀጥለናል አሉ-አል ቁዱስ አል አረቢያ ለተሰኘዉ ለደን ለሚታተም ጋዜጣ-በቀደም።

ተዘዋዋሪዉ ድርድር እስራኤል ከአሜሪካኖች፥ ፍልስጤሞች ከአሜሪካኖች ይነጋገራሉ ማለት ነዉ። ለዘመነ-ዘመናት አብረዉ የኖሩት፥ ለዘመነ-ዘመናት አብሮ በሠላም ለመኖር እንደሚሹ የሚናገሩት፥ ለዓመታት የተደራደሩት የሁለቱ ፖለቲከኞች በቀጥታ ለመነጋገር ግን አልፈለጉም።አልቻሉም ወይም ሁለቱም በየፊናቸዉ እንደሚሉት አንዱ ሲፈልግ-ሌላዉ እንቢኝ ይላል።

ለመወቃቀስ መካሰሱ ምክንያቱ በሁለቱም ወገን ሞልቶ ተርፏል።ጎልቶ የወጣዉ ግን ሁለት ነዉ። እስራኤል ፀጥታዬ-መከበር አለበት ትላለች።በዚያ ላይ በሐይል በያዘችዉ የፍልስጤሞች ግዛት የአይሁድ ሠፈራ መንደር ማስገንባቷን መቀጠል ትፈልጋለች።አንድ።

ፍልስጤማዊዉ የፖለቲካ ሳይቲስት ባሰም ዙባዲ ደግሞ እንዲያዉ ሁኔታዉ ተለዉጦ ፍልስጤም መንግሥት ቢመሠርት የሚያስተዳድረዉ ግዛት ማግኘቱንም ይጠራጠራሉ።

«እስራኤሎች እየሩሳሌም እና ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የአይሁድ ሠፈራ መንደሮችን የማስገንባት መርሐቸዉን ቀጥለዋል።በዚሕም ምክንያት የፍልስጤም መንግሥት ቢመሠረት፥ የሚመሠረትበት ግዛት የማግኘቱ ተስፋ በጣም የመነመነ ነዉ።የተረፈ መሬት የለም።»

ዙባዲ ይሠጋሉ።የአይሁድ የሠፈራ መንደር ግንታዉ መቀጠሉ፥ የድርድሩን ዉጤት ጨርሶ አዳፍኖት ፍልስጤሞችን ተስፋ እንዳያስቆርጥ፥ ተስፋ መቁረጡ ደግሞ ወደ አመፅ ሊያመራቸዉ ይችላል እያሉ።እስራኤላዊዉ የኢኮኖሚ አዋቂ ሺር ሐቬር ግን የፍልስጤሙን የፖለቲካ አዋቂ ትንታቴ አይቀበሉም።ሐቬር እንደሚሉት አመፅ ለፍልስጤሞች አመራጭ መሆን የለበትም። «ፍልስጤሞች አመፅ አልባ የትግል ሥልትን እና ዴሞክራሲያዊ መንገድን ይከተላሉ የሚል ጠንካራ ተስፋ አለኝ።ይሕ አማራጭ አስተማማኝ እና ገቢራዊ እንዲሆን የመጣር ሐላፊነትም አለብኝ።»

ምክንያት ሁለት እንደገና እስራኤል፥ ፍልስጤሞች ምናልባት ሆኖላቸዉ ነፃ መንግሥት ከመሠረቱ የሚመሠረተዉ መንግሥት በሚቆጣጠረዉ የፍልስጤም ግዛት የእስራኤል ጦር መስፈር አለበት ትላለች።ይሕ ሐሳብ የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ «የፀጥታ ሰነድ» ባሉት የማደራደሪያ ሐሳብ ላይም ተካቷል።

ሐሳቡን ግን ፍልስጤሞች ብቻ ሳይሆኑ የአረብ ሊግም ተቃዉሞታል።ነፃ መንግሥት ግን የእስራኤል ጦር የሚቆጣጠረዉ መንግሥት።ዙባይዲ እንደሚሉት አሜሪካኖችም፥ አዉሮጶችም እስራኤል ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ባለመፍቀዳቸዉ ለዘመናቱ እምቅ ችግር መፍትሔ አልተገኘም።

«አሜሪካኖችም፥ አዉሮጶችም፥ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ባጠቃላይ እስራኤል ላይ ግፊት ለማድረግም ሆነ በተጨባጭ ሠላም ለማዉረድ ፍላጎት የላቸዉም።እነሱ የሚፈልጉት የድርድር ሒደቱ መቀጠሉን ብቻ ነዉ።ሒደቱ በርግጥ አለ።እንደለ መታደል ሆኖ ይሕ ሒደት የሠላም ሒደት የመሆን አቅም የለዉም።»

እስራኤላዊዉ የምጣኔ ሐብት ሐቬር ፍልስጤሞች የሚሹትን በሠላማዊ መንገድ ማግኘት አለባቸዉ ባይ ናቸዉ።እስራኤል ፍልስጤሞችን መጉዳትዋን እንድታቆም ምዕራቡ አለም ብዙም ግፊት አላደረገባትም የሚለዉን ግን ሐቬር አይቀበሉትም።

«ሁሉም ወገን ሊያደርገዉ የሚገባ ነገር አለ ብዬ አምናለሁ።ለምሳሌ ጀርመን የእስራኤልን ምርቶች ላለመግዛት መወሰንዋ የእስራኤል መርሕ ሕጋዊ እንዳልሆነ ግልፅ እና ተጨባጭ መልዕክት ያስተላልፋል።መልዕክቱን አሁንም ቢሆን እስራኤሎች እየተረዱት ነዉ።እስራኤሎች አሁን በሚያደርጉት መንገድ ለዘላለም መቀጠል እንደማይችሉ እየተገነዘቡት ነዉ።ይሕ ፍልስጤሞች ፍትሕ እንዲጠይቁ፥ ለፍትሕ አመፅ በሌለበት መንገድ እንዲታገሉ ያበረታታቸዋል።»

ትግሉ-እስከ መቼ ይቀጥላል።ድርድሩስ?

John Kerry und Mahmoud Abbas 05.12.2013
ምስል Reuters/Mohamad Torokman
Kerry Netanyahu PK in Jerusalem 05.12.2013
ምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ