የእሥልምና ሃይማኖት ትምሕርት በኖርድ ራይን ቬስትፋለን
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 29 2004በምዕራብ ጀርመኑ የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ከ2 ሳምንት አጋማሽ በፊት በተጀመረው በአዲሱ የትምህርት ዘመን ለ 1ኛ ደረጃ ተማሪዎች የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት ለመሰጠት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ። ለዚሁ አላማ የሚውል የትምህርት መርጃ መፀሐፍም ተዘጋጅቷል ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ።
ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ሙስሊም ይኖርባታል በሚባለው በጀርመን ከ1999 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለሙከራ ተብሎ የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት በአንዳንድ የጀርመን ትምህርት ቤቶች ይሰጥ ነበር ። ከዛሬ 2 ሳምንት ጀምሮ ግን በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ለመጀመሪያ ጊዜ የእስልምና ትምሕርት በመደበኛ ትምህርትነት ለ1 ኛ ደረጃ ተማሪዎች ለመሰጠት እንቅስቃሴዎች ተጀምሯል ። በዚሁ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተማሪዎች የእስልምናን ባህላዊ እሴቶችና ደንቦችን ይማራሉ ። ለዚሁ ዓላማም የትምህርት መርጃ መፀሐፍ ተዘጋጅቷል ። መፀሐፉ ወደፊት እስከ 2 ተኛ ደረጃ ድረስ እንዲዘልቅ ይደረጋል ተብሎ ለሚታሰበው ለዚህ ትምህርት መሠረት ይጥላል ተብሉ ይታመናል ። የእስልምና ጉዳዮች አጥኚ ሚኻኤል ኪፈር እንዳሉት « በአንድነት ጉዞ » የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ የትምሕርት መርጃ መፀሀፍ በስእል የተደገፈ በመሆኑ ተማሪዎች በቀላሉ ሊረዱት ይችላሉ
« እርግጥ ነው ይሄ ትምህርት ለ1 ና 2ተኛ ክፍል ተማሪዎች የሚጠቅም ነው ። በዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት በተለይ ለ 1 ኛ ክፍል ተማሪዎች ያን ያህልም ማንበብ ለማይችሉ በስእል እርዳታ ማቅረቡ የተለየ ትርጉም እንዳለው ነው ። »
በተለይም ለ 1 ኛ ና 2 ተኛ ክፍል ተማሪዎች በተዘጋጀው የትምሕርት መርጃ መፀሐፍ ውስጥ መሰረታቸው የውጭ የሆነ ሳራና ቢላል የተባሉ ልጆች ታሪክ ተካቷል ። ሁለቱ ልጆች ህፃናት ሊረዱ በሚችሉበት አቅም መፀሀፉ የሳራ ወላጆች ከሳውዲ አረቢያ የቢላል ደግሞ ከ ቱርክ ወደ ጀርመን የመጡ መሆናቸውን በመተረክ ነው የሚጀምረው ። በዚህ መፀሃፍ ሌሎች ሃይማኖቶችም ይጠቀሳሉ ። የእስልምና ሃይማኖት ጉዳዮች አጥኚው ሚኻኤል ኪፈር ከመፀሐፉ ውስጥ አንዳንዱን ክፍል መተቸታቸው አልቀረም
«የወደድኩት ነገር ቢኖር ስለ ሃይማኖቶች መወራረስ የሚያወሳውን ክፍል ነው ። ይህ እጹብ ድንቅ ሆኖ ነው የተዘጋጀው ። ምክንያቱም መፀሐፉ ስለ ይሁዲ እምነትና ስለ ክርስትና ምንነት ያስተምራል ። ያልወደድኩት በታሪኩ ላይ የጠቀሱት 2ቱ ልጆች የሳራና የቢላል ወላጆች ወደ ጀርመን ተሰደው የገቡ መሆናቸው ነው ። እንደኔ ግምት ጥሩ የሚሆን የነበረው እስልምና ያን ያህል የውጭ ዜጎች ሃይማኖት የሆነ አስመስሎ ማቅረቡን ነው ። መዘንጋት የሌለብን ቱርኮች ወደ ጀርመን ለሥራ እንዲገቡ የተደረገበትን ስምምነት 50 ኛ አመት ባለፉት አመታት አክብረናል ። ያ ማለት ከዚያን ጊዜ አንስቶ በጀርመን የሚኖሩ ሙስሊሞች እኛ እዚህ የምንኖር 4 ተኛ ትውልድ ላይ የምንገኝ መሆናችን ነው ። »
መሐመድ ኮርሺድ ከመፀሃፉ 6 ደራሲዎች አንዱ ናቸው ። እርሳቸውና ሌሎች ደራሲዎች ፣ የምሁራንን የሙስሊሙን ማህበረሰብ እንዲሁም የወላጆችና ተማሪዎችን ፍላጎት ለሟሟላት የተቻላቸውን ሙከራ አድርገዋል ።
« ማድረግ የፈለግነው ለሁሉም የሚስማማ የእስልምና ትምሕርት መፀሐፍ ማዘጋጀት ነበር ። የሙስሊሙ ማህበረሰብም በጀርመን ሃገር የእስልምና ትውፊትና ሃይማኖቱ እ ንዲሁም መለያውም ሆነ መታወቂያው እንዲጠበቅ ነው ፍላጎቱ ። ይህ አንዱ ተግዳሮት ነበር ። እናም ዘመናዊውና ባህላዊው ሚዛኑን ጠብቆ እንዲቀርብ ለማድረግ ሞክረናል ። »
በመፀሐፉ ውስጥ የተካተቱት የሳራና የቢላል እናቶች ቤት ውስጥ አይከናነቡም መፀሃፉ ውስጥ ያሉት ገፀ ባህርያት በውጭ አንዳንዴ ራሳቸውን ሸፍነው ይታያሉ አንዳንዴም አይሸፍኑም ። ይህን ጉዳይ በትምህርት መርጃው መፀሐፍ ውስጥ በጥንቃቄ ለማካተት መሞከሩን ነው ኮርሺድ የሚናገሩት ።
« ለምሳሌ ራስ መከናነብን በተመለከት ሙስሊሙ ማህበረሰብ በመፀሃፉ ውስጥ አንዲት ሙስሊም አስተማሪ ራስዋን እንድትከናነብ ይጠብቅ ይሆናል ። በጀርመን መርህ ግን አስተማሪዎች መከናነብ አይፈቀድላቸውም ። እናም ይሄንን እንዴት መወጣት ይቻላል ? ብለን በመፍትሄነት በስእሉ ላይ አስተማሪው ወንድ እንዲሆን አድርገናል ። »
ይም ሆኖ መፀሐፉ በተለይ አንዳንድ እውነታዎችን እንዳሉ ባለማቅረብ ወይም ትክክለኛ ትርጉሞችን ባለመስጠት ከተለያየ አቅጣጫ መተቸቱ አልቀረም ። ለምሳሌ መፀሃፉ የጀርመንኛውን ጎት ወይም እግዚአብሄር የሚለውን ቃል ከመጠቀም ይልቅ የአረብኛውን ቃል አላህን መውሰዱ በአንዳንድ ወገኖች አስተችቶታል ። ከተችዎቹ መካከል የሃይማኖት ትምህርት መምህርና አሳታሚው ላምያ ካዶር አንዱ ናቸው ።
« እንደሚመስለኝ እንደ የሃይማኖት ትምህርት አስተማሪ ና አሳታሚ አንድ መፀሐፍ ሲያቀርብ ጠቅላላውን ይዘት ሳያዛንፍ ማቅረብ ይኖርበታል ። የእስልምናውን ትምህርት ለሚከታተሉት ሰዎችም ሃላፊነት አለበት ። እነዚህ ተማሪዎች አላህና እግዚዘብሔር አንድ አይደሉም የሙስሊሞቹ ፈጣሪ አላህ የሌሎቹ ደግሞ እግዚአብሄር የሚሉ ከሆነ ለዚህ ሃላፊነት መውሰዱ ይከብደኛል »
ሙንሰትር የሚገኘው የእስልምና ትምሕርት ማዕከል ሃላፊ ሙሃናድ ኮርሺዴ ከአሁን በኋላም ከዚህ መፀሐፍ ጋራ ተያይዞ ከባህላዊውና ከዘመናዊው ወገን እንዲሁም ከመንግስትና ከሃይማኖት ተቋማት በኩል የሚነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮችን ማስተናገዳቸውን ይቀጥላሉ ። ለ1 ኛ ና 2ተኛ ክፍል ተማሪዎች ከተዘጋጀው በአንድነት ጉዞ ከተባለው መፀሐፍ በተጨማሪ ሌሎች አጋዥ የትምህርት መርጃዎችን የማዘጋጀት እቅድ አለ ። እስልምናና የሙስሊሞች ጉዳይ በየጊዜው የመነጋገሪያ ርዕስ በሆኑባት በጀርመን የእስልምና ሃይማኖት ትምሕርት ለመስጠት የተጀመሩት እንቅስቃሴዎች አበረታች ተደርገው ነው የሚታዩት ። በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መካከል የአንዳንዶቹን አስተያየት ጠይቄ ነበር ። አቶ መኪ ረዲ የኮሎኝ ነዋሪ ናቸው ። የመጀመሪያዋ ሴት ልጃቸው በቅርቡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምራለች ። በሚኖሩበት ፌደራዊ ክፍለ ሃገር የእስልምና ሃያማኖት ትምህርት ለመስጠት የተጀመረው እንቅስቃሴ አስደስቷቸዋል ።
አቶ አንዋር ሚፍታህ ጀርመን ሲኖሩ 21 አመታት ተቆጥረዋል ። በኮሎኝ ከተማ ሲኖሩ ደግሞ 12 አመት ሆኗቸዋል ። የ 4 አመት ልጅ አላቸው ። ከ አንድ ወይም ከ2 አመት በኋላ ትምህርት ቤት ይገባል ። የእስልምና ሃይማኖት መሰጠቱ የሚያስገኘውን ጥቅም ሰፋ አድርገው ነው የተመለከቱት ።
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ