1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራዉያን ስደተኞች የተቃዉሞ ሠልፍ

ዓርብ፣ ሰኔ 19 2007

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኤርትራ የሚካሄደዉን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያጣራ ያቋቋመዉ ቡድን ያጠናቀረዉ ሪፖርት በመደገፍ ና በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በሚመራዉ መንግሥት ላይ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጫናዉን እንዲያጠናክር የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ እንዲሁም በበራኽሊና በአሳይታ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ተካሄደ።

https://p.dw.com/p/1FoAB
ምስል DW/Yohannes G/Egziabher

[No title]

በኤርትራ መንግሥት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በተለያዩ ሐገራት የተሠደዱ ኤርትራዉያን በአደባባይ ሠልፍ ጠየቁ።ኤርትራዉያን ስደተኞች በያሉበት ሐገር አደባባይ ወጥተዉ መንግሥታቸዉ ያወገዙት የተባባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤርትራ ዉስጥ ከፍተኛ የሠብአዊ መብረገጣ እንደሚፈፀም ካስታወቀ በኋላ መሆኑ ነዉ።የዓለም አቀፉ ድርጅት አጥኚዎች ባለፈዉ ሳምንት ይፋ ባደረጉት ጥናት መሠረት የኤርትራ መንግሥት ዜጎችን በዘፈቀ ያስራል፤ ይገርፋል፤ ይገድላል፤ ወይም ደብዛቸዉን ያጠፋል።ትናንት እስራኤል አደባባይ የወጡ በመቶ የሚቆጠሩ ኤርትራዉያን ስደተኞች፤«ከሐገራችን የወጣነዉ ነፃነት በማጣት እንጂ መኪና እና ሌሎች የቅንጦት ቁሳቁሶችን ፍለጋ አይደለም» ማለታቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።በእስራኤል የአዉሮጳ ሕብረት ፅሕፈት ቤት አካባቢ የተሠለፉት ስደተኞች ጥገኝነት እንዲሰጣቸዉም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የሚኖሩ በመቶ የሚቆጠሩ ኤርትራዉያን ስደተኞችም ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ መንግስታቸዉን ባደባባይ ሠልፍ አዉግዘዋል።አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበዉ በአፍሪቃና በአውሮጳ ሕብረቶች ፅሕፈት ቤቶች አጠገብ የተሠለፉት ስደተኞች እንዳሉት ኤርትራዉያን ሕይወትን የሚያሰጋዉን የስደት ጉዞ የሚጋፈጡት በሐገራቸዉ በሰላም መኖር ሥላልቻሉ ነዉ።

Demonstration gegen die eritreische Regierung in Addis Abeba
ምስል DW/Yohannes G/Egziabher

ዤኔቭ-ስዊዘርላንድ ዉስጥም ዛሬ የኤርትራን መንግሥት በመቃወም ሰልፍ እንደነበረ አንዳንድ ምንጮች ዘግበዋል።ሥለ ዤኔቩ ሠልፍ ዝርዝር ዘገባ ግን አልደረሰንም።ባለፈዉ ሰኞ እዚያዉ ዤኔቭ ዉስጥ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባን በሠልፍ ተቃዉመዉ ነበር።የኤርትራ መንግሥት የሚሰነዘርበትን ወቀሳና ትችት አይቀበልም።

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገ/እግዚአብሄር

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ