የኢድ አል አድኻ አከባበር
ሐሙስ፣ መስከረም 13 2008በዓሉ ኢትዮጵያ ዉስጥም በድምቀት ተከብሯል ። በተለይ በአዲስ አበባ ስታድዮም በርካታ ሙስሊሞች በተገኙበት በጋራ ፀሎትና ስግደት ነው የተከበረው ። ከፀሎትና ስግደት በኋላም የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከንቲባ ለበዓሉ ታዳሚዎች ንግግር አድርገዋል ። ዘንድሮ በአዲስ አበባ ስታድዮም የተገኘው ሙስሊም ቁጥር ከበፊቶቹ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ያነሰ እንደሆነ የአዲስ አበባው ወኪላችን ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ ዘግቧል ።የኢድ አልአድሃ በዓል የእርድ በዓል ነው ። አቅሙ ያለው ለበዓሉ በግ ወይም ከብት አርዶ ከድሆች ጋር ተካፍሎ መብላት ይጠበቅበታል ። በየቤቱ አቅም እንደፈቀደ ምግብ አዘጋጅቶ ከዘመድ ወዳጅ ከጎረቤት ጋር መብላት መጠጣትም በዚህ በዓል የተለመደ ነው ። የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ሙስሊሞች በዓሉን ያከበሩት ድሆችንም በመርዳት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን በየዓመቱ የሃጂ ጉዞ በሚያደርጉባት በሳውዲ አረቢያ ዛሬ የደረሰው የሞት አደጋ በበዓሉ ላይ ጥላ አጥልቷል ። መካ አቅራቢያ በምትገኘው በሚና ከተማ በተፈጠረ መጨናነቅ ና ግፍያ ከ700 በላይ ሰዎች መሞታቸውን መንግስት አስታውቋል።
በአደጋው ከ800 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል ። የሳውዲ መንግሥት እስካሁን የሟቾቹን ዜግነት አላሳወቀም ። ኢራን ግን 41 ዜጎቿ በአደጋው መሞታቸውን አስታውቃለች ።በሙስሊሞቹ ቅዱስ ሥፍራ መካሕና እና አካባቢዉ ሕይወት ያጠፋ አደጋ ሲደርስ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ የዛሬዉ ሁለተኛዉ ነዉ።ከአስራ-ሁለት ቀን በፊት በታላቁ የመካሕ መስጂድ ላይ የግንባታ ክሬን ወድቆ ከአንድ መቶ አስር በላይ ሰዎች ሞተዋል።በርካቶች ቆስለዋል።ለዘንድሮዉ ሐጂ 2 ሚሊዮን ያሕል ምዕመን ለዚያራ ተጉዟል።ሳውዲ አረቢያ ስለ በዓሉ ድባብና ስለ ደረሰው አደጋ መጠን ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክን አነጋግረናል ። በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት በዋሽንግተን ኢድ አል አድሃ እንዴት እንደሚከበር መክብብ ሸዋ ዘገባ አለው ።
ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
ነበዩ ሲራክ
መክብብ ሸዋ
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ