1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢየሩሳሌም ዋና ከተማነት መዘዝ

ዓርብ፣ ኅዳር 29 2010

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌምን በእስራኤል ዋና ከተማነት እዉቅና መስጠታቸዉን በማውገዝ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ዛሬ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ። ከፍልስጤም አንስቶ ሙስሊሞች በሚያመዝኑባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት፤ በእስያ እና በአፍሪቃ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች እስራኤልን እና አሜሪካንን ኮንነዋል።

https://p.dw.com/p/2p2JE
Ägypten Proteste gegen die Verlegung der US Botschaft nach Jerusalem
ምስል Reuters/M. A. E. Ghany

ፍልስጤማዉያንብቻ ሳይሆኑ የአረቡን ዓለም አስቆጥቷል፤

በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከዛሬው የሙስሊሞች የጁማ ስግደት እና ፀሎት በኋላ በዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻዎቹ በሄብሮን በቤተልሄም እና በረመላሕ ከተሞች ተቃውሞ ሲያሰሙ ከፖሊሲች ጋር ተጋጭተዋል። ሰልፈኞች በእስራኤል ወታደሮች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ወታደሮች ደግሞ በአፀፋው አስለቃሽ ጢስ እና የላስቲክ ጥይቶች መተኮሳቸው ተዘግቧል። በጋዛ ጎዳናዎችም በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የትራምፕን ውሳኔ በማውገዝ ሰልፍ ወጥተዋል። እየሩሳሌም በሚገኘው የአል አቅሳ መስጊድ አካባቢም በሺህዎች የተገመቱ ፍልስጤማውያን ሙስሊሞች ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። በግብጽ ርዕሰ ከተማ ካይሮም ከጁማ ስግደት በኋላ በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ  ላይ ሰልፈኞች« እስራኤል ትውደም» «ለፍልስጤማውያን ደማችንን እናፈሳለን ነፍሳችንን እንሰጣለን» ብለዋል። ህንድ በምትቆጣጠረው ካሽሚር ለተቃውሞ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች «አሜሪካ ትውደም» «እሥራኤል ትውደም» የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር። የካሽሚር መሪዎች የትራምፕን እርምጃ ፀረ ሙስሊሞች ሲሉ ኮንነዋል። ዮርዳኖስ ውስጥ የተሰለፉት ደግሞ «እየሩሳሌም አረብ ናት» «አሜሪካን የእባብ ጭንቅላት ናት» የሚሉ መፈክሮችን አስተጋብተዋል። ኢራናውያንም ቴህራን ውስጥ «ሞት ለአሜሪካ» «ሞት ለእስራኤል» እያሉ ቁጣቸውን ገልጸዋል። ሶማሊያ መዲና መቅዲሾም ለፍልስጤማውያን አጋርነትን ለመግለፅ በተካሄደ ሰልፍ ላይ «ትራምፕ ይውደም» የሚሉ ፀረ እሥራኤል እና ፀረ አሜሪካ መፈክሮች ተሰምተዋል። በሊባኖስ ከ5 ሺህ በላይ ፣ኢስታንቡል ቱርክ ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች የተካፈሉበት ሰልፍ ተካሂዷል። በማሌዥያ ደግሞ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ርዕሰ ከተማ ክዋላላምፑር የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲሲ ፊት ለፊት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። 
 

Iran Proteste in Teheran gegen Anerkennung Jerusalems als Israels Hauptstadt
ቴህራን ላይ የተካሄደዉ የተቃዉሞ ሰልፍምስል picture-alliance/AA/Stringer

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸዉ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ለመሆኗ እዉቅና ሰጥታለች ካሉ ወዲህ በመካከለኛዉ ምስራቅ ዉጥረት ነግሷል። የዉሳኔያቸዉ መዘዝ በዛሬዉ ዕለት ፍልስጤማዉያን የቁጣ ቀን አዉጀዉ ከእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች ጋር ሲያጋጫቸዉ ዉሏል።

 የሰዉ ሕይወት መጥፋቱንም ዘገባዎች ያሳያሉ። እስራኤል እና ፍልስጤም ከሚወዛገቡባቸዉ ጉዳዮች መካከል ሰፊ ድርሻ የያዘችዉ የኢየሩሳሌም ጉዳይ በዉስጧ የሚኖሩትን ፍልስጤሞች ብቻ ሳይሆን በቅርብም ሆነ በሩቅ የሚገኙ የአረብ እና ሙስሊም ሃገራትንም ቁጣ ቀስቅሷል። በሙስሊሞች ዘንድ የጸሎት ዕለት በሆነዉ ዓርብ በአካባቢዉ ስለነበረዉ ሁኔታ ጄዳ የሚገኘዉን ተባባሪ ዘጋቢያችንን ነቢዩ ሲራክን ስቱዲዮ ከመግባቴ አስቀድሜ በስልክ አነጋግሬዋለሁ።

ነቢዩ ሲራክ/ ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ