1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የኢንተርኔት መሹለኪያና መደበቂያዎች

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 5 2009

በኢንተርኔት የሚንሸራሸሩ መረጃዎች እገዳ አለያም መሰናክል ሲገጥማቸው ዜጎች ከሌላው ዓለም ጋር ግንኙነታቸው በአያሌው ይስተጓጎላል። ለዚህ ግን መላ አልጠፋም። የተከለከሉ ወይንም በኢንተርኔት በኾነ ምክንያት ከእይታ የተሰወሩ መረጃዎችን እና ድረ-ገጾችን እንዴት መከታተል እና ማሰስ ይቻላል? ራስንስ ከክትትል እና ስለላ በምን መልኩ ማዳን ይቻላል?

https://p.dw.com/p/2UE4i
Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

የፕሬስ ነፃነት በታፈነባቸው ሃገራት የሚኖሩ ዜጎች ኢንተርኔት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በአግባቡ ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ይቸገራሉ። እንደ ፌስቡ እና ትዊተርን የመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችንም በቀላሉ ለማግኘት የማይችሉበት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ሲከሰት ይታያል። በኢንተርኔት የሚንሸራሸሩ መረጃዎች እገዳ አለያም መሰናክል ሲገጥማቸው ዜጎች ከሌላው ዓለም ጋር ግንኙነታቸው በአያሌው ይስተጓጎላል። ለዚህ ግን መላ አልጠፋም። የተከለከሉ አለያም በኢንተርኔት በአንዳች ምክንያት ከእይታ የተሰወሩ መረጃዎችን እና ድረ-ገጾችን እንዴት መከታተል እና ማሰስ ይቻላል? ራስንስ ከክትትል እና ስለላ በምን መልኩ ማዳን ይቻላል? 

በመላው ዓለም የፕሬስ ነጻነት የሌለባቸው ሃገራት የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በተደጋጋሚ ሲዘጉ አለያም ከአነአካቴው ገደብ ሲያበጁለት ይታያል። እንደ ፍሪደም ሐውስ የዚህ ዓመት ዘገባ ኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ከሌለባቸው 18 የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ትመደባለች። ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያልተሰጣት ጎረቤት ሶማሊላንድ በዘገባው መሠረት ከኢትዮጵያ ተሽላ «ከፊል ነጻነት» ያለባት ሀገር ተብላለች። የኢንተርኔት ገደብ ዜጎች ነፃ መረጃዎችን በቀላሉ እንዳያገኙ ወይንም ፈጽሞ ከመረጃ እንዲርቁ ሊያደርግ ይችላል።   

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Lei

ኦሊቨር ሊኖው በዶይቸ ቬለ የአቅርቦት እና ማከፋፈያ የቴክኒክ ክፍል ውስጥ ባለሙያ ናቸው። የዶይቸቬለ ዝግጅቶች በኢንተርኔት እንዲሁም በአጭር ሞገድ ኅብረተሰቡ ጋር በተገቢው መንገድ መድረስ ስለመቻላቸው መከታተል እና እንዲደርሱም ማድረግ ነው ዋነኛ ተግባራቸው። በኢንተርኔት ላይ የሚንሸራሸሩ መረጃዎች ገደብ ሲጣልባቸው መሹለኪያ አማራጭ ስለሆነው የዙር አዙር ማገናኛ (proxy server)  ያብራራሉ። 

«ፕሮክሲ ሰርቨር ማለት በቀላል አገላለጽ የኢንተርኔት ግንኙነትን ማስቀየሺያ ማለት ነው። ኢንተርኔት ላይ አንድ ነገር ብጠይቅ፥ ጥያቄ የቀረበለት ድረ-ገጽ ላይ የእኔ የኢንተርኔት አድራሻ አይታይም። ይልቁንስ የሚታየው የዙር አዙር ማገናኛው ፕሮክሲ ሰርቨር አድራሻ ነው። ከዚህ የዙር አዙር ማገናኛ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ግን የተሸፈነ ወይንም የተደበቀ አይደለም። ከላኪ እና ከተቀባይ ውጪ ሦስተኛ የዙር አዙር ማገናኛ ከሚጠቀመው ከቪፒኤን ይለያል። ቪፒኤን መረጃዎችን ቆልፎ ነው የሚልከው።»

ከማንኛውም ኮምፒውተር ጋር በኢንተርኔት ደኅነነቱ የተጠበቀ ግንኙነት ለማከናወን የሚደረግ ሒደት የሠነድ ቊለፋ (VPN) ይባላል። የቪ ፒ ኤን ቴክኖሎጂ እንደ መሽሎኪያ ቋት (proxy server) በላኪው እና በተቀባዩ መካከል ሦስተኛ አገናኝ ይፈልጋል። ልዩነቱ ድረ-ገጾች በታገዱባቸው አካባቢዎች ግለሰቡ የኢንተርኔት ፍለጋ ወይንም አሠሣውን ማንም ሳያይበት እንዲያከናውን ያስችለዋል። ይኽ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ የሚደረግ የመረጃ ልውውጥ ሌላ አገር የተደረገ ያስመስለዋል ማለት ነው።

ይኽን በምሳሌ ለማስረዳት ያኽል ፍሪደም ሐውስ በዘንድሮ ዘገባው «የፕሬስ ነጻነት የሌለባት» ሀገር ካላት ኢትዮጵያ አንድ መልእክት ወደ ፈለጉበት ቦታ መላክ ወይንም መቀበል ፈለጉ እንበል። ቪፒኤን ተጠቃሚ ከሆኑ ኢትዮጵያ ሆነው የላኩት አለያም የተቀበሉት ሠነድ ለሌላው የሚታየው ከሌላ ሀገር የተላከ ወይንም ወደ ሌላ ሀገር የተላከ መልእክት ሆኖ ነው።

ILLUSTRATION Internetseite des Kurzmeldungsdienstes Twitter
ምስል picture alliance/dpa

የመልእክት ልውውጡን ፍሪደም ሐውስ «ከፊል የፕሬስ ነጻነት አላት» ካላት ሶማሊላንድ ወይንም ደግሞ ሌላ ሀገር ውስጥ የተደረገ የመረጃ ልውውጥ አድርጎ ሊሆን ይችላል የሚያሳየው። ያም ማለት በኢንተርኔት የሚልኩት መረጃ በሙሉ ወደ ሌላ ሀገር ደርሶ ነው እርስዎ ጋር የሚመለሰው ማለት ነው። ለእርስዎም የሚላከው መልእክት የሚደርስዎ በሌላ ሀገር ኔትወርክ በኩል አሣብሮ ነው። ከእነዚህ የዙር አዙር ማገናኛዎች መካከል ሳይፎን (Psiphon) አንዱ ነው።

«ሳይፎን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማል። የዙር አዙር ማገናኛ ቋት ይጠቀማል። ቪፒኤን ይጠቀማል። እንደ ማይክሮሴፍት ያሉ የተለያዩ ሶፍትዌሮችንም ይጠቀማል። ስለዚህ ሳይፎንን ለማገድ ያስቸግራቸዋል። ምክንያቱም ሳይፎንን ልገድብ ቢሉ ሌሎች ብዙ ሶፍትዌሮችንም ስለሚያጠፋ ተያይዞ መጥፋት ነው የሚሆነው።»

ሳይፎን በባሕሪው በበርካታ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ መሥሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች አገልግሎት ላይ የሚውለው የማይክሮሶፍት እና ሌሎች ሶፍትዌሮችን ይጠቀማል። ሳይፎንን ለመገደብ ወይንም ለማገድ የሚደረግ ሙከራም ሌሎች ጠቃሚ ሶፍትዌሮችም ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ያደርጋል። ሳይፎን ሲገደብ ሌሎች አገልግሎቶች ከጥቅም ውጪ ስለሚሆኑም ነው ባለሙያው «ተያይዞ መጥፋት» ይኾናል ሲሉ ያብራሩት።

ሳይፎን እንደ ፌስቡክ እና ትዊተርን የመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በደንብ መጠቀም ያስችላል ይላሉ የዶይቸ ቬለው ባለሙያ ኦሊቨር ሊኖው።  በሳይፎን የዶይቸ ቬለ ድረ-ገጽን መከታተል ይቻላል፤ ከዚያም ባሻገር ሌሎች ድረ-ገጾችንም መጠቀም አያዳግትም ብለዋል። ከዶይቸ ቬለ የሚሰናዱ የድምጽ እና የቪዲዮ መረጃዎችን በሳይፎን በቀላሉ መጠቀም ይቻላል። የዙር አዙር የኢንተርኔት ማገናኛዎች በርካታ ናቸው። ሳይፎን በዋናነት የሚለየው ቶር (TOR) ከሚሰኘው ሌላኛው የዙር አዙር ማገናኛ ቋት ነው።

Screen-Shot der Webseite Tor
ምስል DW/P. Bykowsky

«ቶር በኢንተርኔት ውስጥ ማንነትን ሙሉ ለሙሉ ለመደበቅ የሚያስችል ማገናኛ ነው። ሳይፎን እንክብካቤ የሚያደርግለት ባለቤት አለው። ቶርን የሚንከባከቡት ቶርን ለማበልጸግ ፍላጎቱ ያላቸው የቶር ማኅበረሰብ አባላት ናቸው። የቶር ዋነኛ ጠቀሜታው ኢንተርኔት ውስጥ አሰሳ ሲደረግ ተጠቃሚው ማንነቱ እንዳይታወቅ መደበቅ ማስቻሉ ነው። ያም ሆኖ ግን ተግዳሮቱ ዝግተኛ መሆኑ ነው። ስለዚህም የድምጽ እና የቪዲዮ መልእክቶች ላሉት ድረ-ገፃችን የመጀመሪያ ተመራጭ አይደለም። ኾኖም ማንነትን መደበቅ ይበልጥ ወሳኝ በሚሆንበት ጊዜ ምናልባት ቶርን መጠቀም ይበጃል።»

ማንነትን ሙሉ ለሙሉ የሚደብቀው ቶርንም ሆነ ማንነትን ሳይደብቅ ግን በፈጣን መልኩ የተከለከሉ መረጃዎችን እንዲታዩ የሚያደርገው ሳይፎንን ከኢንተርኔት በነፃ ማግኘት ይቻላል። የአንድሮይድ ማስተናበሪያ ስልክ እና ኮምፒውተር ተጠቃሚዎች ከጉግል ፕሌይ እንደ አይፎን የመሳሰሉት የአይኦ ኤስ ማስተናበሪያ ያላቸው ስልኮች ወይንም ኮምፒውተሮች ደግሞ ከአይቲውንስ ስቶር መጫን ይቻላሉ። ወይንም ደግሞ ጉግል የኢንተርኔት ማሰሻ ላይ https://psiphon3.com ብሎ በመጻፍ በቀጥታ ስልክ፣ ታብሌት አለያም ኮምፒውተር ላይ መጫን ይቻላል። ከዚያ በኋላ ድረ-ገጾች ቢዘጉ እንኳን የኢንተርኔት አገልግሎት እስከተገኘ ድረስ በተጫነው ማስተናበሪያ ድረ-ገጾቹንም ሆነ የማኅበራዊ መገናኛ አገልግሎቶችን መከታተል ይቻላል።

ከሳይፎን እና ከቶር ሌላ በርካታ የዙር አዙር ማገናኛዎች ኢንተርኔት ውስጥ በነፃ ይገኛሉ። ከአንዱ አንዱ እያቀያየሩ መፈለግም ይቻላል። ያን ለማድረግ የኢንተርኔት ማሰሻ ወይንም መፈለጊያው ላይ proxy server ብሎ መጻፍ እና መመሪያዎቹን መከተል ነው።

Symbolbild Internet Hacker Sicherheit Computer www Passwort
ምስል Fotolia/Yong Hian Lim

ከዙር አዙር ማገናኛዎች ባሻገር የኢንተርኔት ክትትል እና ገደብ በሚኖርባቸው ሃገራት ሌላው ጠቃሚ ነገር የቊለፋ ስልት (encryption) የሚባለው ነው።  ኢንተርኔት ውስጥ በነፃ የሚገኙ በርካታ የቊለፋ ስልቶች ቢኖሩም የተወሰኑት ዋነኞችን እንጠቁማችሁ።

ከመደበኛ ስልክ በተለየ መልኩ መረጃዎች በላኪ እና በተቀባይ ብቻ እንዲታዩ ከሚያደርጉ ማስተናበሪያዎች መካከል ዋትስአፕ (whatsApp) ዋነኛው ነው። ቫይበርም የመረጃ ቅብብሎሽ ባልተፈለገ ወገን እንዳይታይ የማድረግ የቊለፋ ስልት መጀመሩን ካስታወቀ ሰነባብቷል። ሲግናል (Signal) የድምጽ ጥሪዎችን እና የጽሑፍ መልእክቶችን በላኪ እና በተቀባይ ብቻ እንዲታዩ አድርጎ በመደበቅ ይታወቃል። ለአፕል ተጠቃሚዎች መሴጅ እና ፌስ ታይም (Messages and FaceTime) የሚባል አለ። በሁለት የአፕል አይ መሴጅ ተጠቃሚ ስልኮች የሚደረግ የመረጃ ልውውጥን ሰብሮ ለመግባት እጅግ አዳጋች እንደሆነ ይነገርለታል። አንዳንዶች እንደውም ሰብሮ መግባቱ «ፈጽሞ የማይቻል ነው» ሲሉ ይደመጣሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ