1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ

Negash Mohammedእሑድ፣ መስከረም 1 2009

በአመፅ ግጭቱ የሚገደለዉ ሰዉ ያነሰ ይመስል፤ ቂሊንጦ ወሕኒ ቤት በተነሳ ቃጠሎና ፀጥታ አስከባሪዎች በተኮሱት ጥይት ቢያንስ 23 እስረኞች መሞታቸዉን መንግሥት አምኗል። የሞቱትን እስረኞች ማንነት ለማሳወቅ ግን መንግሥት አንድ ሳምንት ያሕል ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/1JzXa
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ

ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ መስተዳድሮች የተቀጣጠለዉ ተቃዉሞ፤ የአደባባይ ሠልፍ፤ አድማና አመፅ ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ፤ እየከረረ እና እየተጠናከረ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰዳቸዉ የሐይል ርምጃዎች የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት፤ አካል፤ ሐብትና ንብረት ከማጥፋት በስተቀር የሕዝቡን ጥያቄዎች አልመለሱም።

የገዢዉ ፓርቲ ኢሕአዴግ ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገዉ ስብሰባዉም ሕዝቡን ለአመፅ ያነሳሱ መሠረታዊ የመብትና የፍትሕ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚጠቅም ዉሳኔ ወይም ሐሳብ አላቀረበም።እንዲያዉም ከስብሰባዉ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ሐይለማርም ደሳለኝ ተቃዉሞዉን ለመደፍለቅ ጦር ሐይሉ እንዲዘምት ማዘዛቸዉ ነዉ የተሰማዉ።ትዕዛዙ የተቃዋሚዉን ቁጣ ይበልጥ ነዉ ያባባሰዉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ተቃዉሞዉን የሚቀሰቅሱት «ዶላር በጆንያ የሚታደላቸዉ ሐይላት» ናቸዉ ባሉ ማግሥት፤ አራት የኢሕአዴግ ነባር ታጋዮች ሕዝቡን ለተቃዉሞ ያሳደመዉ የአመራር ችግር ወይም በነሱ ቋንቋ «የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ያላቸዉ» የኢሕአዲግ መሪዎች ናቸዉ በማለት የጠቅላይ ሚንስትራቸዉን መግለጫ ተቃርነዋል።

የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት ተቃዉሞ የቀሰቀሰዉን ሕዝባዊ ቅሬታ በማብረዱ ሐሳብ፤እርምጃ፤ ወይም መፍትሔ ላይ የኢሕአዴግ መሪዎች አንድ ወጥ አቋም የያዙ አይመስሉም።በአመፅ ግጭቱ የሚገደለዉ ሰዉ ያነሰ ይመስል፤ ሰሞኑን አዲስ አበባ አጠገብ በሚገኘዉ ቂሊንጦ ወሕኒ ቤት በተነሳ ቃጠሎና ፀጥታ አስከባሪዎች በተኮሱት ጥይት ቢያንስ 23 እስረኞች መሞታቸዉን መንግሥት አምኗል።የሞቱትን እስረኞች ማንነት ለማሳወቅ ግን መንግሥት አንድ ሳምንት ያሕል ቆይቷል።

የእስረኞች ወላጅ፤ ወዳጅ ዘመዶች የተወዳጆቻቸዉን እርም ሳያወጡ አንድ ሳምንት መቆየት ግድ ነበረባቸዉ።

ሕዳር በተጀመረዉ ግጭት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከሰባት መቶ መብለጡን የመብት ተሟጋቾች እየዘገቡ ነዉ።ለኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛዉን ድጋፍ የምትሰጠዉ ዩናይትድ ስቴትስ፤ የመንግሥት ፀጥታ ሐይሎች የሚወስዱትን ርምጃ «አለቅጥ የበዛ እና እጅግ አስጊ» ብላዋለች።ተቃዉሞ፤ ግጭት ግድያዉ በዚሁ ከቀጠለ ሐገሪቱን ወደሚበታትን አደጋ አለያም ወደ እርስበርስ እልቂት ሊያመራ ይችላል ብለዉ የሚሰጉ ታዛቢዎች ብዙ ናቸዉ።እንደ ልማዱ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ነዉና የመልካም ምኞት መግለጫን ባስቀደምን በወደድን ነበር ግን የኢትዮጵያ አሳሳቢ ሁኔታ ይሕን አልፈቀደልንም።አሳሳቢዉን ሁኔታ አንስተን እንወያያለን።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ