1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ እና የኃይማኖት ተቋማት 

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 12 2010

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሐገሪቱን የሚያዉከዉ፤ ዜጎችዋን የሚገድለዉ ግጭት እንዲቆም የመጀመሪያዉን ጥያቄ በይፋ ያቀረበዉ መጋቢት 2008 ነበር። ጠየቀ። መልስ ግን የለም። ከነበረም የተቃዉሞዉ መስፋፋት፤ የግጭቱ ንረት፤ የሟች ቁስለኛዉ ቁጥር መበራከት ነዉ።

https://p.dw.com/p/2pmQ8
Infografik Karte Proteste und Ausschreitungen in Äthiopien 2016

NM - MP3-Stereo

ኢትዮጵዮጵዉያን የሐገሪቱን ሠላም እና አንድነት ለማስከበር በጋራ እንዲጥሩ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠይቋል። የተለያዩ የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ተቋማትን የሚያስተናብረዉ ጉባኤ ትናንት ባወጣዉ መግለጫዉ ኢትዮጵያን በሚያብጠዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ ሕይወታቸዉን ላጡ የተሰማዉን ሐዘን ገልጧል። ወጣቶች በተለይም የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለሰላም መከበር እንዲጥሩ ጠይቋልም። መግለጫዉን የተከታተሉ የሃይማኖት መሪዎች እና ተንታኞች ጉባኤዉ ለሠላም ያደረገዉን ጥሪ ደግፈዉታል። ይሁንና መሪዎቹ እንደሚሉት ጥሪዉ «ዘግይቷል»፤ ይዘቱም የመንግሥት አስተሳሰብ ተጫጭኖታል። 

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሐገሪቱን የሚያዉከዉ፤ ዜጎችዋን የሚገድለዉ ግጭት እንዲቆም የመጀመሪያዉን ጥያቄ በይፋ ያቀረበዉ መጋቢት 2008 ነበር። ጠየቀ። መልስ ግን የለም። ከነበረም የተቃዉሞዉ መስፋፋት፤ የግጭቱ ንረት፤ የሟች ቁስለኛዉ ቁጥር መበራከት ነዉ።የሐገሪቱን አንጋፋ፤  መንፈሳዊ ተቋማት የሚያስተናብረዉ ጉባኤ ዓመት ለዘጠኝ ወር አድፍጦ ትናንት እንደገና ብቅ አለ።«ዘገየ» ይላሉ ዲያቆን አባይነሕ ካሴ።
                                       
በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተጠሪ ሊቀካሕናት መርዓዊ ተበጀም  የዲያቆን አባይነሕን ሐሳብ ይጋራሉ። ጠበኞችን ለማስታረቅ የሃይማኖት መሪዎች መዘግየት አልነበረባቸዉም።
                              
የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቆጣጠረዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተሠራጨዉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ፤ ሊቀካሕናት መርአዊ እንደሚመክሩት ጠበኞችን ለማስታረቅ ሥለመፈለግ አለመፈለጉ ያለዉ የለም። ይልቅዬ ራሱ ተቃዉሞ ያየለበት መንግሥት መፍትሔ ይስጥ ነዉ ጥሪዉ።                     
ይሕ ነዉ ለዲያቆን አባይነሕ የመግለጫዉ ሁለተኛ ድክመት።                         
ሊቀ ካሕናት መርዓዊ እንደሚሉት የሃይማኖት መሪዎች ተልዕኮ እዉነትን መናገር፤ ማስተማር እና መምከር መሆን አለበት።                                    
ዲያቆን አባይነሕ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ ለሃይማኖት መሪዎችም መፈተኛ ነዉ ባይ ናቸዉ።                               
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ትናንት ባወጣዉ መግለጫ በተለይ የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ብሔራዊ አንድነትን ለመጠበቅ እና ሐገርን ለመገንባት ጠንክረዉ እንዲሰሩ ጠይቋል። 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ