1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ መንስኤና መፍትሔዉ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ጥቅምት 20 2010

ለሐገር የሚያስብ ወይም እዉነቱን ማወቅ የሚፈልግ ካለ ብዙዎች እንደሚያምኑት የኢትዮጵያ ወደድንም ጠላንም ከደም አፋሳሽ  ቀዉስ መግባቷን መቀበል፤ ከቻለ ምክንያቱን መፈለግ፤ ለመፍትሔዉ መጣርም አለበት።ሁለት ዓመቷ።

https://p.dw.com/p/2mlWV
Äthiopien Proteste Gebet
ምስል Reuters/T. Negeri

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፤ ቀዉስ መንስኤና መፍትሔዉ

የኢትዮጵያ መሪዎች አዲስ አበባ ዉስጥ ይሰበሰባሉ፤ይነጋገራሉ ይናገራሉም።በሐገሪቱ ሠላም እንደሚያስከብሩ ጦር ሠራዊታቸዉን «ይወዳል» ያሉትን ሕዝብ ደሕንነት እንደሚያስጠብቁ፤ልማትን እንደሚያፋጥኑ ይደሰኩራሉ። ቃል ይገባሉ።ተስፋዉም በሽ ነዉ።የሰላም ደሕንነቱ ቃል ተስፋ ጭናቅሰን አይደለም ጫንጮ ሳይደርስ የወለፊንድ የመባረቁ ሐቅ እንጂ ሕቅታዉ።ከአምቦ እስከ ጭሮ፤ ከጂጂጋ እስከ ቦሎ ዴዴሳ ሰዎች እየተገደሉ፤ እየታሰሩ፤ እየታገዙ፤ መቶ ሺዎች እየተሰደዱ ነዉ።ሐብት ንብረት ወድሟል፤  ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ፤የሸቀጦች ዝዉዉር ተገድቧል፤ መተማመን ጠፍቷል።አዲስ አበባ በቴሌቪዥን የሚባለዉ ከሚሆነዉ በእጅጉ ተራርቋል።ከእንግዲሕስ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።                                  

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ መንግሥት (ደርግ) የተቃዋሚዎቹን ጩኸት፤ ጥያቄ ለማጣጣል «በጫጫታ የፈረሰች ሐገር ብትኖር እያሪኮ ብቻ ናት» በሚል መግለጫ ያኪያኪስ ነበር።በዘመናችን ሥለ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞ ሲጠየቅ የዘመኑ የአምደ መረብ ፋኖዎች «ሐገር በወሬ አትፈርስም» እያሉ የቀዳሚ ብጤያቸዉን ሥልት እንደ ዘመናቸዉ ፈሊጥ እየደገሙት ነዉ።

በወሬ የሚፈርስም የሚገነባም ሐገር እስካሁን የለም።የመንግሥትን አገዛዝ በመቃወም በየሥፍራዉ አደባባይ የሚወጣዉን ሕዝብ ጥያቄን፤ የሕዝብ እንቅስቃሴን የሚያወሱ ዘገቦችን-«ከሐገር አፍራሽ ወሬ» መቁጠር ግን ደንቁሮ-የዋሆችን የማደናቆር ሥልት ዉጤት ነዉ።ለሐገር የሚያስብ ወይም እዉነቱን ማወቅ የሚፈልግ ካለ ብዙዎች እንደሚያምኑት የኢትዮጵያ ወደድንም ጠላንም ከደም አፋሳሽ  ቀዉስ መግባቷን መቀበል፤ ከቻለ ምክንያቱን መፈለግ፤ ለመፍትሔዉ መጣርም አለበት።ሁለት ዓመቷ።የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ መስራች እና የቀድሞ መሪ ዶክተር አረጋዊ በርሔ ቀዉሱን «አስጊ» ይሉታል። ቀዉስ አልነዉ ብጥብጥ ችግሩ አለ።እና ከየት እና እንዴት መጣ? በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም ጉዳይ መምሕር ናሁሰናይ በላይ እንደ ሂሳብ ያሰሉታል።                                

Äthiopien Irreecha Feierlichkeiten
ምስል DW/Y. Gebregzihabher

ዶክተር አረጋዊ የረጅም ጊዜ ተደራራቢ ችግር ዉጤት ነዉ ባይ ናቸዉ።                             

የኢትዮጵያ መንግስት ቀዉሱን ለማስወገድ ባለፉት ሁለት ዓመታት አዋጆን ሽሯል፤ ከጎንደር እስከ ዶዶላ ጠንከራ የኃይል እርምጃ ወስዷል፤ በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን በየጦር ሠፈሩ አስሮ «አይደገምም» እያሰኘቷልም።ካቢኔ ሽሮ አዲስ ሾሟል፤ «ጥልቅ» ያለዉን ተሐድሶ ማድረጉን አስታዉቋል፤ 10 ወራት የቆየ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፤ ሁነኛ መፍትሔ ግን እስካሁን የለም።

አቶ ናሆሰናይ «በዴሞክራሲ እጦት» ተፈጠረ ያሉት ችግር ከተፈጠረ በኋላም ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ አልተሰጠም ይላሉ።                    

Äthiopien Premier Hailemariam Desalegns Rede in Parlament
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሹም ሽር፤ ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ፤ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ የሚቃረን መግለጫ፤ የቃል ድርጊታቸዉ መቃረን ለችግሩ የጋራ እና ሁነኛ መፍትሔ እንዳይፈልጉ እንቅፋት ሆኗል የሚሉ ወገኞች አሉ።ሌሎች ደግሞ ሐገሪቱን የሚመራዉ ኃይል በግልፅ አይታወቅም ይላሉ።አቶ ናሁሰናይ ተጠያቂነት የሚሰማዉ ባለሥልጣን አለመኖሩ ነዉ ባይ ናቸዉ።በኢሕአዲግ መሪዎች መካከል ሽኩቻ አለ የሚለዉን ግምትም የሚጋሩ ይመስላሉ።

ፈረንሳሲዉ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ሬኔ ለፎ በቅርቡ እንደ ፃፈዉ ደግሞ በኢሕአዴግ ነባር እና አዳዲስ መሪዎች መካከል መግባባት ያለ አይመስልም።በጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራዉ ካቢኔ ሐገሪን ሙሉ በሙሉ ማስተዳደሩን ይጠራጠራል።ለፎ እንደሚለዉ የቀድሞዉ ጠንካራ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዉት የነበረዉን የመንግሥት ሥርዓት ከመለስ ሞት በኋላ የሚዘዉሩት አንድም የደሕንነት (የፀጥታ) ሁለትም የጦር ሠራዊቱ አዛዦች ናቸዉ።

ዶክተር አረጋዊ በርሔ ግን ጉዳዩን ሰፋ አድርገን ማየት አለብን ባይ ናቸዉ።የሐገሪቱን ፖለቲካዊ ሥርዓት በመዘወሩ ሒደት የኃያላን እጅም አለበት-እንደ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ።                            

ሩዋንዳ ስምንት መቶ ሺዎችን የፈጀዉን ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋን ባስተናገደች ማግሥት ኪጋሊን ቀድመዉ ከጎበኙ ጥቂት የዉጪ መሪዎች አንዱ የያኔዉ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ፕሬዝደንት አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ።አቶ መለስ ለሁለተኛ ጊዜ ኪጋሊን ሲጎበኙ ትንሽቱ ሐገር የትልቅ ጥፋትዋን ማቅ እንዳጠለቀች በዓለም አደባባይ ብቅ ያለችበት ጊዜ ነበር።1995 እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር።

አቶ መለስ በያኔዉ የሩዋንዳ ምክትል ባሁኑ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሚ ጋባዥነት አዲስ ለተከፈተዉ ለኪጋሊ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ንግግር አደረጉ። አሰቃቂዉን ግፍ አንስተዉ «እንዳትረሱት ግን ይቅር በሉ» አሉ ኢትዮጵያዊዉ መሪ አዳራሹን ላጨናነቀዉ ተማሪ forgive but not Forget።«ኢትዮጵያ ለብዙ ሺሕ ዘመናት ነፃነትዋን ጠብቃ የኖረችዉ በብሔርችዋ መካካል ልዩነት ሳይኖር ቀርቶ አይደለም-----» ጠንካራዊ ኢትዮጵያዊ መሪ አደራሹን የሚያነቃንቀዉ የአድናቆት  ጭብጨባ ጋብ እስኪልላቸዉ እየጠበቁ----ቀጠሉ «ትልቅ ብሔራዊ ችግር በተለይ የዉጪ ወረራ ሲኖር ሕዝቡ ልዩነቱን አቻችሎ በጋራ ሥለሚቆም እንጂ» እያሉ።

አዲስ አበባ ላይ የኢትዮጵያን የመቶ አመት ታሪክ የነገሩን መሪ ኪጋሊ ሲሻገሩ ወደ ብዙ ሺሕ መቀየራቸዉን የሰሙ ጋዜጠኞች ጉዳዩን የቡና እና ሲጋራ ማወራረጃ አድርገዉት ነበር።የመለስዋ ኢትዮጵያ በርግጥ ከችግር አልወጣችም ነበር።ጠንካራ መሪዋን ከሸችበት ጊዜ ጀምሮ ግን እሳቸዉ «ብሔራዊ» ካሉት ዓይነት ትልቅ ቀዉስ ዉስጥ ናት።

Äthiopien Gedeo Grundstücke Brand Protest
ምስል W/O Aynalem/R.Abeba

ቀዉሱ በመቶ ከመቶ የምርጫ ዉጤት ሊጀቦን አልተቻለም።አሸባሪ፤ ፀረ ሠላም፤የጎረቤት መንግሥታት ተላላኪ እየተባለ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችዋን፤  ጋዜጠኞችዋን፤ የመብት ተሟጋቾችዋን፤ የኃይማኖት መሪዎችዋን ወሕኒ መወርወሩም የተከረዉ የለም።ዛሬም የዜጎችዋ ሕይወት፤ ደም አካል እየተገበረ ነዉ።እስከመቼ? አቶ ናሁሰናይ እሰወስት የተከፈለ የመፍትሔ ሐሳብ አላቸዉ።

                                    

ዶክተር አረጋዊ ተቃዋሚዎች በጋራ እስኪ ቆሙ ባይ ናቸዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ እስኪ ቸር ያሰማን እንበል።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ