1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ በጀርመናዊዉ ጋዜጠኛ እይታ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 4 1999

«የአዲስ አበባ የትኩረት አቅጣጫ ከአስመራ ይልቅ እንደ መሰንበቻዉ ሁሉ መቅዲሾ ላይ ነዉ ያነጣጠረዉ።ከሁሉም በላይ ሶማሊያ የዘመቱት የኢትዮጵያ ወታደሮች በሠላም ወደ ሐገራቸዉ የሚመለሱበት ብልሐት ማፈላለግ እና አሁኑኑ ማስወጣት የሚቻልበትን ሥልት መቀየስ----

https://p.dw.com/p/E0hD
ሶማሊያ፣- የኢትዮጵያ ትኩረት
ሶማሊያ፣- የኢትዮጵያ ትኩረትምስል AP

የታዋቂዉ የጀርመን ዕለታዊ ጋዜጣ ፍራንክፉርተር አልጋማይነ ጋዜጠኛ ክርስቲያን ሮስለር የኢትዮጵያ መንግሥት የወቅቱ ዋነኛ የቱክረት አቅጣጫ ሶማሊያ የሠፈረዉ የኢትዮጵያ ጦር የሚወጣበትን ብልሐት ማፈላለግ እንደሆነ አስታወቀ።ኢትዮጵያን ጎብኝቶ የተመለሰዉ ጋዜጠኛ እንደሚለዉ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ይልቅ በሶማሊያ ጉዳይ ሳትጠመድ አልቀረችም።አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሥለ ኢትዮጵያ የሚከተለዉ መርሕ ደግሞ ጋዜጠኛዉ እንደታዘበዉ ወቀሳና ትችትን ከድጋፍ ጋር የቀየጠ አይነት አይነት ነዉ።ሉድገር ሻዶምስኪ ሮስለርን አነጋግሮታል።ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

በድበር ይገባኛል ሰበብ የሚወዛገቡት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአካባቢዉ የሚሆነዉን ሁሉ የመወቃቀሻ ምክንያት እንዳደረጉት ነዉ።የየተቃዋሚዎቻቸዉ እንቅስቃሴ፤ የሶማሊያ ግጭት፤ የዉጪ ሰዎች መታገት፤ ሁሉም የሁለቱ መንግሥታትን ዉዝግብ ለማናር ሰበቦች ናቸዉ።የታዋቂዉ የፍራንክፉርተር አልጋማይነ ጋዜጣ የአፍሪቃ ጉዳይ አዘጋጅ ክርስቲያን ሮስለር በኢትዮጵያ ቆይታዉ ይሕን በቅጡ አስተዉሏል።

«በርግጥ ኤርትራ ቀደም ሲል በሶማሊያ ግጭት የተጫወተችዉ ሚና ነበር።ኢትዮጵያ እንዳለችዉ ኤርትራ ከሶማሊያ ተቀናቃኝ ሐይላት አንዱን በመርዳት አፍራሽ እርምጃ ወስዳለች በማለት መዉቀስዋም አንዱ ምክንያት ነበር።»

በቅርቡ አፋር መስተዳድርን መጎብኘት ላይ የነበሩ የአዉሮጳ እና የኢትዮጵያ ዜጎች መታገታቸዉም ለሁለቱ ሐገሮች ዉዝግብ ምክንያት ሆኗል።ኤርትራ ሰዎቹን አግታለች ወይም አሳግታለች በማለት ኢትዮጵያ መዉቀሷ የዉዝግቡን እንዴትነት ጠቋሚ ነዉ።ያም ሆኖ ጋዜጠኛ ጋዜጠኛዉ እንደታዘበዉ የወቅቱ የኢትዮጵያ አብይ ትኩረት ከአስመራ ይልቅ መቅዲሾ ነዉ።

«የአዲስ አበባ የትኩረት አቅጣጫ ከአስመራ ይልቅ እንደ መሰንበቻዉ ሁሉ መቅዲሾ ላይ ነዉ ያነጣጠረዉ።ከሁሉም በላይ ሶማሊያ የዘመቱት የኢትዮጵያ ወታደሮች በሠላም ወደ ሐገራቸዉ የሚመለሱበት ብልሐት ማፈላለግ እና አሁኑኑ ማስወጣት የሚቻልበትን ሥልት መቀየስ፣ ወይም የተጀመረዉ ማስወጣት የሚቀጥልበትን መንገድ ማመቻቸት ነዉ-ዋናዉ ትኩረት።»

የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሶማሊያ እንዲወጣ የሐገሪቱን ሠላም የሚያስከብር የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት በእግሩ መተካት አለበት።የዩጋንዳ ሠራዊት ሶማሊያ መዝመት መጀመሩ ጥሩ እመርታ ቢሆንም በጥቅሉ የሚፈለገዉ ስምንት ሺሕ ሠራዊት ሶማሊያ እስካልሰፈረ ድረስ በሐገሪቱ አንፃራዊ የሚባል ሠላም እምኳን መስፈኑ አጠራጣሪ ነዉ።ያም ሆኖ የሶማሊያ ግጭት-ጦርነት ከሶማሊዎች፣ ከኢትዮጵያም አልፎ የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጉዳይ መሆኑ ጋዜጠኛዉ እንደታዘበዉ ለኢትዮጵያ አስደሳች ነዉ።

«የሶማሊያ ችግር አለም አቀፍ ይዘት አለም አቀፋዊ መልክና ባሕሪ ትኩረትም መያዙ (ለኢትዮጵያ) አስደሳች ነዉ።አለም አቀፉ ማሕበረሰብ በስተመጨረሻዉ አሁን እስካሁን ከሚያደርገዉ የበለጠ ለማድረግ መጣሩ ጥሩ ነዉ።»

አለም አቀፉ ማሕበረሰብ የአፍሪቃ ቀንድን ከሚያነካካዉ ከኢትዮ-ኤርትራ ዉዝግብ፣ ከሶማሊያ ግጭት በተጨማሪ የኢትዮጵያን የዉስጥ ፖለቲካዊ ሁኔታም የዘነጋዉ አይመስልም-ጋዜጠኛዉ እንደታዘበዉ።በ1997 ከተደረገዉ ምርጫ ዉጤት በሕዋላ የታሰሩት የፖለቲካ ማሕበራት መሪዎች፣ ጋዜጠኞች እና የሲቢክ ማሕበረሰብ ተወካዮች በቅርቡ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የችሎቱን ሒደት ተከታትሎም ነበር።-ጋዜጠኛዉ።የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎቹን በማሠሩ ከመብት ተሟጋቾችና ከአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለሚሰነዝርበት ወቀሳና ትችትም እንግዳ አይደለም-ሮስል።በዚሕ ጉዳይ ላይ ጀርመንን ጨምሮ አለም አቀፉ ማሕበረብ የሚከተለዉን መርሕ ቅይጥ ብሎ ደመደመዉ።

«አዎ በዚሕ ጉዳይ ከአለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሚንፀባረቀዉ አመለካከት ቅይጥ ነዉ።ባንድ በኩል የሕግ የበላይነት ተጠብቆ ይሕ ሒደት እልባት እንዲያገኝ የሚደረገዉ አለም አቀፍ ግፊት እንደቀጠለ ነዉ።በሌላ በኩል ደግሞ የበጀት ድጎማዉ ከተቋረጠ በሕዋላም መሠረታዊ አገልግሎችን ለማዳረስ የሚባሉ አነስተኛ የልማት ተቋማትን ለመደገፍ የሚሰተዉ እርዳታ እንዲቀጥል ዝግጅቱን ታያለሕ።የአዉሮጳ ሕብረት፣ የአለም ባንክ እና ብሪታንያ የሚሰጡት ድጋፍና የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነዉ።ጀርመንም ይሕን መርሕ ትደግፋለች።እንዳልኩት አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሥለ ኢትዮጵያ የሚከተለዉ መርሕ ባንድ በኩል እየወቀሰ በሌላ በኩል ደግሞ አግባቢ መንገዶችን ወይም ትንሽ ድልድይ መገንባት ነዉ።»