የኢትዮጵያ ጦር ከሑዱር መዉጣቱና አ-ሸባብ
ሐሙስ፣ መጋቢት 12 2005
ሶማሊያ የዘመተዉ የኢትዮጵያ ጦር የባኮል ክፍለ-ግዛት ዋና ከተማ ሑዱርን ለቅቆ በወጣ በሰዓታት ልዩነት ዉስጥ የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አ-ሸባብ ከተማይቱን ተቆጣጥሯቷል።አንዳድ ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ ጦሯን ከሑዱር ያስወጣችዉ ከሶማሊያ መንግሥትና ከአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት (AMISOM) ጋር ባለመግባባቷ ነዉ።የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግን «አለመግባባት ተፈጥሯል» የሚለዉን ዘገባ አስልተቀበሉትም። አሸባብ ሑዱርን መቆጣጠሩ ታዛቢዎች እንደሚሉት ማሳሰቡ አልቀረም።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና ጋዜጠኛ መሐመድ ዑመር ባንድ ጉዳይ-አንድ ናቸዉ።አ-ሸባብ ሑዱርን መቆጣጠሩ በጥቅል ሶማሊያ ሠላምና መረጋጋት ላይ የሚያሳድረዉ ተፅዕኖ የለም-በማለት።
ጋዜጠኛ መሐመድ ዑመር ቀጠለ፤
«የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሑዱር መዉጣታቸዉና አሸባብ ከተማይቱን መቆጣጠሩ በሶማሊያም ሆነ በመንግሥቷ ላይ የሚያሳድረዉ ተፅዕኖ የለም።ምክንያቱም አሸባቦች ከበርካታ የሶማሊያ ከተሞች ተባርረዋል።እና አሁን በጣም ደካማ ናቸዉ።»
ሌሎች በዚሕ አይስማሙም። አሸባቦችም ሑዱሩን ለመቆጣጠር አልሰነፉም። እንደ ድል አድራጊም እየጨፈሩ ነዉ። «መሸሻቸዉ አይቀርም።» ይላል የሞቅዲሾዉ ጋዜጠኛዉ።
«ባይደዋ የሚገኘዉ የሶማሊያ ጦርና የአፍሪቃ ሕብረት ተባባሪዎቹ ወደ ሑዱር ከተቃረቡ አ-ሸባቦች ከተማይቱን ለቅቀዉ ወደ ጫካ መግባታቸዉ አይቀርም»
«አዲስ ነገር አይደለም።» አሉ አምባሳደሩ።
መሳሳብ። ዉሐ ቅዳ ዉሐ መልስ አይነት።የኢትዮጵያ፥ የሶማሊያ መንግሥት ወይም የአሚሶም ጦር ሲመጣ አሸባብ ይሸሻል።ጦሩ ሲወጣ አሸባብ ይመለሳል።እስከ መቼ? አይታወቅም።ኢትዮጵያ ከሁዱር የወጣችበት ምክንያትም እንደተመልካቹ ይለያይል።
አዣንስ ፍራንስ ፕረስ የጠቀሳቸዉ የአሚሶም ባለሥልጣናት እንደሚሉት ኢትዮጵያ ጦሯን ያስወጣችዉ ጦሯ የሚቆጣጠረዉን አካባቢ አሚሶም እንዲረከበዉ ላቀረበችዉ ጥያቄ አፋጣኝ መልስ ባለመግኘቷ ነዉ።የአዲስ አበበና የሞቃዲሾ መንግሥታት ግንኙነትም በዉጥረት የተሞላ ነዉ ባዮች ናቸዉ፥ የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ምንጮች።
ጋጠኛ መሐመድ ዑመር ደግሞ ከሶማሊያ ባለሥልጣናት ያገኘዉን መረጃ ጠቅሶ እንደሚለዉ ኢትዮጵያ ጦሯን ያስወጣችዉ ለማንም ሳታማክር ነዉ።
«ከአካባቢዉ በደረሰን ዘገባና መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ወታደሮችዋን ከሁዱር እንደምታስወጣ ለከተማይቱም ሆነ ለአካባቢዉ ባለሥልጣናት አላስታወቀችም።ማንንም ሳታስጠነቅቅ ከተማይቱን ለቅቃ ስትወጣ ባካባቢዉ የነበሩት የአሸባብ ተዋጊዎች ወደ ከተማይቱ ገቡ።»
አምባሳደር ዲና በዚሕ አይስማሙ።ጦሩ ሑዱርን የለቀቀዉም ለተለመደ ወታደራዊ ታክቲክ ነዉ ባይ ናቸዉ።የኢትዮጵያ ሶማሊያ የዘመተችበት አለማ አምባሳደር ዲና እንደሚሉት አሁንም አልተቀየረም።
ተልዕኮዉ ለመሳካት አለመሳካቱ ሁሉንም የሚያግባባ መለኪያ የለም።ኢትዮጵያ በራሷ መመዘኛ ተልዕኮዉ ተሳክቷል ብላ፥ በራሷ ጊዜ እንደ ሁዱር ሁሉ ሥልታዊቱን የባይደዋን ከተማ ከለቀቀች ግን ብዙዎች እንደሚሉት ለአሸባብ ታላቅ ድል፥ አሸባብን ለሚወጉት ሐይላት ባንፃሩ ከፍተኛ ዉድቀት ነዉ-የሚሆን።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ