1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ጦር፥የሶማሊያ ፀጥታ፥የተመድ

ረቡዕ፣ ጥር 23 2004

ያንዴዉ ጥቃት ግን በርግጥ ቀላል-የሚባል አይደለም።አለም አቀፍ የዜና ምንጮች

https://p.dw.com/p/13pmq
የአሸባብ ተዋጊዎችምስል AP

እንደዘገቡት አንድ አጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ያጨቀበትን መኪና እያሽከረከረ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሰፈሩበት ቅጥር ግቢ በራፍ ጋር አላታመዉ።አካባቢዉ ጋየ።ጢስ ጠለሱ የከተማይቱ ነዋሪዎች እንዳሉት ከሩቅ ይታይ ነበር። ማዕከላዊ ሶማሊያ በልደንወይን-ከተማን በሚቆጣጠረዉ የኢትዮጵያ ጦር ላይ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ትናንት ባፈነዳዉ ቦምብ ከስድስት-እስከ አስር የሚደርሱ የኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸዉ ተዘገበ። አጥፍቶ ጠፊዉን እንዳዘመተ ያስታወቀዉ አሸባብ ከሰላሳ በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች መግደሉን አስታዉቆ ነበር።የኢትዮጵያ መንግሥት ሥለ ጥቃቱ እስካሁን በይፋ ያስታወቀዉ ነገር የለም።በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶማሊያን ጉዳይ የሚከታተል ፅሕፈት ቤቱን ከናይሮቢ ወደ ሞቃዲሾ ማዞሩ ለሶማሊያ የሽግግር መንግሥት እንደ ፖለቲካ ድጋፍ እየታየ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።


በሞቃዲሾ የዶቸ ቬለ ዘጋቢ ሁሴይን አዌይስ-የበለድወይን ከተማ ነዋሪዎችን ጠቅሶ እንዳስታወቀዉ ከጥቃቱ በሕዋላ ከተማይቱ-የወትሮ እንቅስቃሴዋን ቀጥላለች።ዉጊያ፥ ግጭት የለም።

«አንድ ጊዜ ብቻ የደረሰ ጥቃት ነዉ።በለድወይን ዉስጥ አሁን የተኩስ ልዉዉጥ የለም።ፀጥታ እንደ ሰፈነ ነዉ።የኢትዮጵያ ወታደሮች ከተማይቱንና አካባቢዉን እየተቆጣጠሩ ነዉ።»

ያንዴዉ ጥቃት ግን በርግጥ ቀላል-የሚባል አይደለም።አለም አቀፍ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት አንድ አጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ያጨቀበትን መኪና እያሽከረከረ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሰፈሩበት ቅጥር ግቢ በራፍ ጋር አላታመዉ።አካባቢዉ ጋየ።ጢስ ጠለሱ የከተማይቱ ነዋሪዎች እንዳሉት ከሩቅ ይታይ ነበር።

የኢትዮጵያ ጦር ባለፈዉ ታሕሳስ ለሁለተኛ ጊዜ ሶማሊያ ከዘመተ-ወዲሕ ይሕን መሰል ጥቃት ሲፈፀምበት የትናንቱ የመጀመሪያዉ ነዉ።አጥፍቶ ጠፊዉያን «አዘመትኩ» ያለዉ የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ በጥቃቱ በጥቅሉ አንድ መቶ የኢትዮጵያ ወታደሮች ገድያለሁ ወይም አቁስያለሁ ባይ ነዉ።ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ አማርኛ ተናጋሪ ከዚያዉ ከበለድ ወይኔ እንዳለዉ ግን በአደጋዉ የሞቱት ሁለት ናቸዉ።

የበለድወይን ነዋሪዎችና ሌሎች መገናኛ ዘዴዎች ግን-ሁሴይን አዌስ እንዳለዉ ሌላ-ነዉ-ያሉት።

«ሌሎች መገናኛ ዘዴዎች እና የአካባቢዉ ነዋሪዎች በጥቃቱ የተወሰኑ ሰዎች መገደል-መቁሰላቸዉን አስታዉቀዋል።እነሱ እንዳሉት ወደ አስር የሚሆኑ ወታደሮች ተገድለዋል።ሌሎች አስር ደግሞ ሳይቆስሉ አልደሩም።»

የኢትዮጵያ መንግሥትን አስተያየት ለማካተት ከትናንት ጀምሮ ሞክረን ነበር።አልተሳካልንም።ትናንት በለድወይን ላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች መገደል-መቁሰላቸዉ ሲነገር ርዕሠ-ከተማ ሞቃዲሾ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛን ለማስተናገድ ሽር ጉድ ስትል ነበር።

የዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ልዩ መልዕክተኛ አጉስቲን ማሒጋ ሞቃዲሾ የገቡት እንደ ከዚሕ ቀደሙ ደርሰዉ ለመመለስ ሳይሆን የሶማሊያን ጉዳይ የሚከታተለዉ ፅሕፈት ቤታቸዉ ከናይኖሮቢ ወደ ሞቃዲሾ መዛወሩን ለማብሰር ነዉ።አለም አቀፉ ድርጅት ሞቃዲሾ ዉስጥ ፅሕፈት ቤት ሲከፍት ከአስራ-ሰባት አመት ወዲሕ የትናንቱ የመጀመሪያዉ ነዉ።

አንዳድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ዓለም አቀፉ ድርጅት ፅሕፈት ቤቱን ወደ ሞቃዲሾ ማዛወሩ የሶማሊያ ፀጥታ አስተማማኝነቱን ጠቋሚ ነዉ።ሞቃዲሾ የሚኖረዉ ጋዜጠኛ ሁሴይን አዌስም በተለይ የርዕሠ-ከተማይቱ ፀጥታ-ተሻሽሏል ባይ ነዉ።አስተማማኝ ከሚባልበት ደረጃ ግን ገና አልደረሰም።

«የሞቃዲሾ የፀጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ ነዉ ማለት እንችላለን።ምክንያቱም አሸባብ ከሁሉም የከተማይቱ ወረዳዎች ተገፍቶ ወጥቷል።ይሕ ማለት ግን ፀጥታዉ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ነዉ ማለት አንችልም።የፅሕፈት ቤቱ መከፈትም ፖለቲካዊ ነዉ።የተከፈተዉም ቢሆን የአሚሶም ሐይል በሰፈረበት በአዉሮፕላን ማረፊያዉ ቅጥር ግቢ ነዉ።ይሕ ማለት በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ፀጥታ የለም ማለት ነዉ።»
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ