1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ንግድ ተባለጥ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2005

ከፍተኛዉ ጉድለት መሸፈን አለበት። ጉድለቱ ዘንድሮና ወደፊት ባምናዉ መጠን ተደግሞ የዉጪ ምንዛሪ እጥረት በዉጤቱም የምጣኔ ሐብት ክስረት እንዳይደግም አቶ ሳምሶን እንደሚያምኑት መንግሥት በሰወስት መስኮች በርትቶ መስራት አለበት።

https://p.dw.com/p/16aEd
ምስል Solomon Mengist

ኢትዮጵያ በዘንድሮዉ ሩብ የበጀት ዓመት (Fiscal Year) ወደ ዉጪ የላከችዉ የሸቀጥ መጠን በሰባት ከመቶ መቀነሱን የሐገሪቱ የንግድ ሚንስቴር አስታወቀ።ሌሎች አጥኚዎች እንደሚሉት ደግሞ ኢትዮጵያ ባለፈዉ የበጀት ዓመትም ወደ ዉጪ የላከችዉ ምርት መጠን፥ ወደ ሐገር ዉስጥ ካስገባችዉ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጉድለት አሳይቷል።አክሰስ-ካፒታል የተሰኘዉ ተቋም አጥኚዎችና ሌሎች የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት፥ ከፍተኛዉ ጉድለት ዘንድሮ እንዳይደገም ሐገሪቱ ወደ ዉጪ የምትልከዉንና የዉጪ ምንዛሪ የምታገኝበትን መንገድ ማጠናከር አለባት።

የኢትዮጵያ የንግድ ሚንስቴር በኢሜይል ያሠራጨዉን መረጃ የጠቀሱ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ካለፈዉ ሀምሌ፥ እስከ መስከረም ማብቂያ በተቆጠረዉ አራት ወር ወይም ሩብ የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ ወደ ዉጪ የላከችዉ ሸቀጥ ካምናዉ ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በሰባት ከመቶ ቀንሷል።

የዚሕ ሰበቡ ሚንስቴሩ እንደሚለዉ በአብዛኛዉ ወደ ዉጪ የተላከዉ ቡና እና የቅባት እሕል መጠን መቀነሱ ነዉ።ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኘዉ የወርቅ ሽያጭ ግን ካምናዉ ጋር ሲነፃፀር የበሁለት ከመቶ አድገት አሳይቷል።ይሕ ግን አጠቃላይ የዉጪ ንግድ ጉድለቱን አይቀይረዉም።

መንበሩን አዲስ አበባ ያደረገዉ አክሰስ ካፒታል የተሰኘዉ ተቋም እንደዘገበዉ ደግሞ ያለፈዉ በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ንግድ ተባለጥ የከፍተኛ ከፍተኛ ጉድለት አሳይቶ ነበር።የተቋሙ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳይ አጥኚ አቶ ሳምሶን ወሌ እንደሚሉት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ መሠረታዊ የግብርና ምርቶች ወደ ዉጪ የሚልኩ ሐገራት የንግድ ተባለጣቸዉ ጉድለት ማሳያቱ እንግዳ ነገር አይደለም።

የኢትዮጵያ የአምናዉ ጉድለት ግን ከፍተኛ ነዉ።7.5 ቢሊዮን ዶላር።ወደ ዉጪ ከሚላከዉ ሸቀጥ የሚገኘዉ ገቢ ወደ ሐገር ዉስጥ ለሚገባዉ ከሚወጣዉ ጋር የሚያሳየዉ ጉድለት እንዲሕ ከፍተኛ ከሆነና ከተደጋገመ ግን በላሙያዎቹ እንደሚሉት ሐገሪቱን የዉጪ ምንዛሪ ሊያሳጣ፥ በዉጤቱም ምጣኔ ሐብቷን ሊጎዳ ይችላል።

የአምናዉ የወጪና የገቢ ንግድ ከፍተኛ ጉድለት የታየበት ምክንያት አቶ ሳምሶን እንደሚሉት ብዙ ነዉ።ዋናዉ ግን ኢትዮጵያ ወደ ዉጪ የላከችዉ ሸቀጥ መጠን ቢጨምርም፥ በፊት የታቀደዉን ያክል ሸቀጥ ወደ ዉጪ መላክ አለመቻሏና ከዉጪ የገባዉ ሸቀጥ መጠን መጨመሩ ነዉ።

ከፍተኛዉ ጉድለት መሸፈን አለበት።ጉድለቱ ዘንድሮና ወደፊት ባምናዉ መጠን ተደግሞ የዉጪ ምንዛሪ እጥረት በዉጤቱም የምጣኔ ሐብት ክስረት እንዳይደግም አቶ ሳምሶን እንደሚያምኑት መንግሥት በሰወስት መስኮች በርትቶ መስራት አለበት።

ወደ ዉጪ የሚላኩ ሸቀጦችን አይነት መጠንና የሚላክባቸዉን ስፍራዎች ማብዛት፥ ዉጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ገንዘብ እንዲልኩ ማበረታታ እና ርዳታና ብድርን ለማግኘት መጣር።

Markt in Äthiopien
ምስል picture alliance/dpa

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ