1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መዘዙ

ሰኞ፣ ጥቅምት 21 2009

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚሉት የሰዎችን የወትሮ እንቅስቃሴን መልሶ፤ ሐገርም አረጋግቷል ይባል ይሆናል።ሰዎች መንግሥት ከሚፈልገዉ ዉጪ ከፃፉ፤ ካነበቡ፤ ካዳመጡ ወይም ካዩ ግን ይወነጀላሉ።

https://p.dw.com/p/2RxEC
Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu
ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መዘዙ

 

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈዉ መስከረም ማብቂያ የደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሐገሪቱን ለማረጋጋት፤ የሕዝቧን ሰላም፤ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዉንም ለማክበር በእጅጉ ጠቅሟል። የመንግሥት ባለሥልጣናትን መግለጫ የተከታተሉ ኢትዮጵያዉያን አንድ ቀላል ጥያቄ ያነሳሉ አዋጁ ወር ባልሞላ ጊዜ ሐገር፤ ሕዝብን ካረጋጋ ከእንግዲሕ ምን ይፈይዳል-እያሉ። የሠብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናትን መግለጫ ይቃረናሉ። የሕዝብን ዕንቅስቃሴ በአዋጅ እያፈኑ የሕዝብ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ተመልሷል፤ ሐገር ተረጋጋቷል የሚባልበት አመክንዮ የለም-ባይናቸዉ። 

ቫይበር፤ ዋትስአፕ፤ ፌስቡክ፤ ቲዊተር እያሉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን አገልግሎትን ይቁጠሩ። ብዙዎቹ ወትሮም ለአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ብልጭ ድርግም የሚሉ ነበሩ። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ  ለዘመናዊዉ  የኢንተርኔት አገልግሎት ባዳ ከምትሆንበት ደረጃ ላይ የደረሰች መስላለች። የሥልክ መስመር ለማግኘት ትዕግስት፤ ጠቀም ያለ ወጪ፤ ረጅም ጊዜ መጠበቅ፤ ደጋግሞ መደወል ግድ ነዉ። ተፈላጊዉን ሰዉ ወይም መስመር ሲያገኙ እፎይ ይሉ ይሆናል።ግን እንዳይሳሳቱ። ሌላ ፈተና አለ።

                                   

አይነት ፈተና። ወይም። ዓይነት።

«ግድ-ይላል» ይላሉ አዲስ አበቦች።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግድ-የሚለዉ ብዙ ነዉ።አላማ፤አስፈላጊነቱ ማወዛገቡ እንደቀጠለ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር አቶ ጌታቸዉ ረዳ እንደሚሉት መንግሥታቸዉ ብዙ ገደቦችን የጣለዉን አዋጅ የደነገገዉ ፀጥታ ማስከበር ግድ ሥለሚለዉ ነዉ።

Infografik Karte Proteste und Ausschreitungen in Äthiopien 2016

                       

የፖለቲካ ተንታኝ ቻላቸዉ ታደሰ ግን መንግሥት በይፋ የሰጠዉን ምክንያት አይቀበሉትም። በተለያዩ አካባቢዎች ለተቃዉሞ አደባባይ የወጣዉን ሕዝብ ያሰባሰበዉ፤ ብዙዎች እንደሚስማሙበት የመብት ጥያቄ ነዉ። የመሬት ባለቤትነት፤የአስተዳደር፤የመካለል፤ ፍትሐዊነት፤ የእኩልነት፤ የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ።የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከደቡብ ኮንሶ ጥግ-እስከ ሰሜን ጎንደር ጠረፍ፤ የደቡብ፤ የኦሮሞ፤ እና የአማራ ሕዝብ ላነሳዉ በርካታ ግን ተመሳሳይ ጥያቄ መንግሥት እስካሁን ተገቢ መልስ  አልሰጠም።

የመብት ተሟጋቾች  እንደሚሉት ደግሞ መንግሥት ለሕዝቡ ጥያቄ ተገቢዉን መልስ ከመስጠት ይልቅ የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎቹ ያልታጠቁ ሰልፈኞችን መግደል፤ማቁሰል፤ ማሰር ማፈኑን ነዉ የተካኑበት። ሕዝባዊ ተቃዉሞዉ ከተቀሰቀሰበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስከታወጀበት እስካለፈዉ መስከረም ማብቂያ ድረስ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ታስረዋል፤ የደረሱበት ያልታወቀዉን የቆጠራቸዉ የለም።

የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሕዝቡ ጥያቄ ተገቢዉን መልስ እንዲሰጡ ይሕ ቢቀር ማስገደል፤ ማሳሰራቸዉን እንዲያቆሙ የመከሩ፤ የጠየቁ፤ያሳሰቡ፤ ያስጠነቀቁም መንግሥታት፤ ማሕበራት የመብት ተሟጋች፤ ድርጅቶች፤ፖለቲከኞች ጋዜጠኞችም ነበሩ።

የመንግሥት ካድሬዎች አፀፋ ግን እዉነትን የዘገቡ፤ ስሕተትን ወይም ስሕተት የመሰላቸዉን የጠቆሙ ጋዜጠኞችን፤ ተንታኞችን እና አስተያየት ሰጪዎችን በሐሰት መወንጀል፤ ማስፈራራት፤መገናኛ ዘዴዎችን ማፈን፤ መካሪ ዘካሪ፤ አስጠንቃቂዎችን ማኪያኪያስ፤ የመንግስትነት አቅም የሌላቸዉን ተቋማት፤ድርጅቶች ወይም ግለሰቦችን መወንጀልን ነዉ የፈቀዱት። የፍልስፍና ፕሮፌሰር ዳኛቸዉ አሰፋ መንግስት ወትሮስ መቼ የሚመከር ሆነና ይላሉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚሉት የሰዎችን የወትሮ እንቅስቃሴን መልሶ፤ ሐገርም አረጋግቷል ይባል ይሆናል።ሰዎች መንግሥት ከሚፈልገዉ ዉጪ ከፃፉ፤ ካነበቡ፤ ካዳመጡ ወይም ካዩ ግን ይወነጀላሉ። አዋጁ ለቀድሞዉ የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ አንጋፋ ታጋይ ለአቶ አስገደ ገብረ ስላሴ የቆየ ትዝታ ነዉ የቀሰቀሰባቸዉ። የደርግ ዘመንን መጥፎ ትዝታ።

                        

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ይሕን አይቀበሉትም።ባለሥልጣናቱ ባሉፉት ሐያ-ምናምን ቀናት ደጋግመዉ እንደነገሩን አዋጁ ሐገርና ሕዝብን ለማረጋጋት በእጅጉ ጠቅሟል።የኮሙኒኬሽን ሚንስትር አቶ ጌታቸዉ ረዳ አዋጁ ገቢር ከሆነ ወዲሕ ግድያ፤ መፈናቀል፤ ጥፋትን አስቁሟል ብለዋል ዛሬ።የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገዉም ይኽንን ነዉ።ገዳዩ ማን ነበር? አሳሪዉስ።የፖለቲካ ተንታኝ ቻላቸዉ ታደሰ ገለልተኛ ወገን ሳያጣራዉ ገዳይ፤ ዘራፊ፤ አሳሪ፤ አጥፊዉን ማወቅ አይቻልም።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ ወትሮም የማይታወቀዉን ይበልጥ የሚያዳፍን ነዉ።

Äthiopier demonstrieren gegen Kanzlerreise
ምስል picture-alliance/dpa/M. Gambarini

                                

በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞዉ ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ እንደራሴ አቶ ግርማ ሰይፉም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰዎችን መብትና ነፃነቶች ይበልጥ ከማፈን ባለፍ የሕዝብ ጥያቄን አይመልስም። ዶክተር ዳኛቸዉ ያክሉበታል። የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ ከሩቅም ከቅርብ፤ ከዉስጥም ከዉጪም  ሆነዉ የሚከታተሉ ወገኖች ባንድ ነገር አንድ ይመስላሉ። ኢትዮጵያን ካለፈዉ ሕዳር ጀምሮ የሚያብጠዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ ሐገሪቱን የኋሊት እንዳሾራት ያሰጋል-በሚለዉ።የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ባዮች በጋራ ካልጣሩ ለሕዝብ ጥያቄ መልስ አይገኝም፤ ሥጋቱንም ምናልባት ማዳፈን እንጂ ጨርሶ ማጥፋት አይቻልም። 

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ