1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃና አርመናዉያን

ሐሙስ፣ ነሐሴ 3 2004

በ 1920 ዎቹ አመታት ግድም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በእስራኤል አገር እየሩሳሌም ዉስጥ አንድ የአርመናዉያንን ገዳም ሲጎበኙ በሙዚቃ አቀባበል ባደረጉላቸዉ ህፃናት ይማረካሉ። ጃንሆይ ልጆቹ ወላጅ አልባ መሆናቸዉን ሰምተዉ በእየሩሳሌም ለሚገኘዉ አርመናዊ የገዳሙ ሃላፊ፣ አርባ ልጆቹን ማሳደግ እንደሚፈልጉ ተናግረዉ ይፈቀድላቸዋል።

https://p.dw.com/p/15mGr

በ 1920 ዎቹ አመታት ግድም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በእስራኤል አገር እየሩሳሌም ዉስጥ አንድ የአርመናዉያንን ገዳም ሲጎበኙ በሙዚቃ አቀባበል ባደረጉላቸዉ ህፃናት ይማረካሉ። ጃንሆይ ልጆቹ ወላጅ አልባ መሆናቸዉን ሰምተዉ በእየሩሳሌም ለሚገኘዉ አርመናዊ የገዳሙ ሃላፊ፣ አርባ ልጆቹን ማሳደግ እንደሚፈልጉ ተናግረዉ ይፈቀድላቸዋል። ከዝያም አርባ አርመናዉያን ልጆች ኬቮርክ ናልቫንድያን ከሚባል አርመናዊ የሙዚቃ አሰልጣኝ ጋር እጎአ በ1924ዓ, ም አዲስ አበባ ይመጣሉ። የነዚህ አርባ ልጆች እና አርመናዊዉ የሙዚቃ አሰልጣኝ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦን እንዳደረገይነገራል። በሌላ በኩል ሙዚቀኞቹ አርመናዉያን «አርባ ልጆች» በመባል ታዋቂነትን አግኝተዋል። ትዝታ ኢትዮጵያዊአርመናዉያን የተሰኘ የአርመን እና የኢትዮጵያዉያንን ጥንታዊ ግንኙነት ባህልና ታሪክ የሚዳስስ አንድ ጥናታዊ ፊልም ሊሰራ የገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ ተጀምሮአል። ትዝታ በሚል ርዕስ ሊሰራ በታቀደዉ የኢትዮ አርመን ታሪክ ገላጭ ፊልም ዋና ተጠሪ ትዉልደ አርመናዊዉ አሜሪካዊ ስለ ፊልሙ ስራ እቅድ እንዲሁም በኢትዮዮጵያዉያ ስለ ሚኖሩ አርመናዉያን እና በኢትዮጵያ ስለነበራቸዉ ሚና እንዲያጫዉቱን በለቱ ዝግጅታች ጋብዘናል።

ትዝታ በሚል ርዕስ ስለ ኢትዮጵያ አርመናዉያን ሊሰራ የታቀደዉ ጥናታዊ ፊልም በተለይ አርመናዉያን ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ላይ የሚያተኩር የፊልም ስራዉ ዋና ስራ አስኪያጅ ትዉልደ አርመናዊዉ አሜሪካዊ አራምዛት ካልያጃን ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ የተለያዩ መረጃዎችን ለማፈላለግ ኑሮአቸዉን አዲስ አበባ ካደረጉም ወራቶችን አስቆጥረዋል። አራምዛት በጥናታዊ ፊልማቸው ላይ የአርመናዉያን እና የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በተለይም የጃዝ ሙዚቃ ትኩረታቸው እንደሆነ ገልጸዋል። የፊልም ስራ አዋቂዉ ትዉልደ አርመናዊ አራምዛት ካልያጃን እንዴት ይህን ጥናታዊ ፊልም ሊሰሩ ተነሱ።

«ይህን ጥናታዊ ፊልም ለመስራት የተነሳሁት በኒዮርክ ሳለሁ በአንድ የአፍሪቃ አሜሪካ ጥናት ኮሌጅ ዉስጥ በሚገኝ ቤተ-መጻህፍት ገብቼ ስለ አፍሪቃ አርሜንያ የባህል ግንኙነት የሚገልጽ መጽሃፍ እንዳለ ጠይቄ፣ አንዲት የአርመን ዝርያ ያላት የቤተ-መጻህፍቱ ባልደረባ ሁለት መጻህፍትን ከሰጠችኝ በኋላ ነዉ። ይህ መጻህፍ አርመናዉያን እና ኢትዮጵያዉያን በታሪካቸዉ ምን ያህል ረጅም ግንኙነት እንደነበራቸዉ ያትታል። አርሜንያዉያን እና ኢትዮጵያዉያን አንድ ከሚያደርጋቸዉ ከሚያምኑበት የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ጀምሮ በ12ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 15ኛዉ ክፍለ ዘመን በመካከላቸዉ የነበረዉ የንግድ ግንኙነት ሁሉ ተጠቅሶአል። በወቅቱ የፈረስ የበግ ና የመሳሪያ ንግድ ያካሂዱ ነበር»

Der äthiopische Kaiser Haile Selassie
ቀዳማዊ ኃይለስላሴምስል picture-alliance / dpa

አርሜንያዉያን በኦቶማን ግዛት ዘመን ጀምሮ በስደት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት መጀመራቸዉን በኢትዮጵያ የብሄራዊ ትያትር የመጀመርያዉ የሙዚቃ አስተማሪ ልጅ ቫርኬዝ ነርሲስ ናልባንድያን ይገልጻሉ።

ጣልያን መጣ ሄደ ተመለሰ

እንግሊዝም መጣ ሄደ ተመለሰ

ሚናስ ብቻ ቀረ ቤት እያፈረሰ

በአጼ ምኒልክ ዘመን የመዘጋጃ ቤት ምህንድስና ቢሮ ሃላፊ ሆነዉ ለተሾሙት ሚናስ ለተባሉ አርመናዊ የተገጠመ እንደነበር ነበር ቫርኬዝ ናልባንዲያን አጫዉተዉናል። በአሁኑ ግዜ ወደ 100 የሚጠጉ አርመኖች ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደሚኖሩ የነገሩን ቫርኬዝ ነርሲስ ናልባንድያን በሙዚቃዉ ረገድም ቢሆን ይላሉ በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን በተለይ አርባ ልጆች በመባል የሚታወቀዉ የአርመኖች ታሪክ ተጠቃሽ ነዉ።

አንጋፋዉ የኪነጥበብ ሰዉ ጸሃፊ ተዉኔት ጌታቸዉ ደባልቄ አርመኖች በተዉኔት እና በሙዚቃ ያደረጉትን አስተዋጽኦ እንዲሁም አርባ ልጆች ከሚባሉት መካከል በቅርብ የሚያውቋቸዉ የሙዚቃ ባለሞያ ነርሲስ ናልባንድያንን ያስታዉሳሉ። አንጋፋዉ እና የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ቁንጮ ከሚባሉት አርቲስቶች አንዱ አለማየሁ እሸቴ አሁን ለሚገኝበት የተሳካ የሙዚቃ ህይወት የአርመናዊያን ጠንካራ ድጋፍ እንዳለበትም ገልጾልናል። ሙሉዉን ቅንብር ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ