የኢትዮጵያ አዉሮፕላን የአደጋ መንስኤ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9 2005የብሪታንያዉ የሲቪላቬሽን የአደጋ መርማሪ ተቋም የአይን ምስክሮችን እና በአዉሮፕላኑ ላይ የተገኙ መረጃዎችን ጠቅሶ ጢሱ የተከሰተዉ በሞተሩ ከፍተኛ ግለት በመፈጠሩ እንደሆነ አስታዉቆአል።
ባለፈዉ አርብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር የመንገደኞች ማመላለሻ አዉሮፕላን በለንደኑ ሂትሮው አየር ጣቢያ አንድም ተሳፋሪ በሌለበት እና በቆመበት የታየዉ ጢስ እንደተጠበቀዉ በቀጥታ የባትሪ ችግር እንዳልሆነ እየተነገረ ነዉ። የቃጠሎዉ ትክክለኛ መንስኤ ግን አልታወቀም። የብሪታንያዉ የሲቪላቬሽን የአየር አደጋ መርማሪ ተቋም ባወጣዉ መግለጫ ከቀኑ 9: 50ላይ የተነሳዉ ጢስ ምስክሮች በሰጡት ቃል እና በአዉሮፕላኑ አካል ላይ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እሳቱ የተነሳዉ በላይኛዉ ወይም ስተኋላ ላይ ባሉት ሞተሮች በተፈጠረ ግለት ነዉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቃጠሎዉን መንስዔ ገና እየተጣራ መሆኑን አስታዉቆአል። የአየር መንገዱ የበረራ ኦፕሪሽን ኋላፊ ካቲቴን ደስታ ዘርኡም ይህንኑ ነዉ የገለጹልን።
በብሪታንያ ሲቪላቬሽን መርማሪ ተቋም ከባድ ያለዉ አደጋ መንስኤ በጥንቃቄ እየመረመረ መሆኑን አስታዉቆአል። ተቋሙ ምርመራዉን ትኩረት ሰቶ የሚከታተለዉ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ለመከላከል ነዉ ይላል። በብሪታንያ ሲቪላቬሽን የአየር አደጋ መርማሪ ተቋምም የአደጋዉን መንስኤ ለማጣራት ቴክኒካዊ ምርመራዉ ጀምሮአል። አዉሮፕላኑ በአሁኑ ወቅት በለንደን ሂትሮ አየር ማረፍያ መጠለያ ቦታ መቆሙንና የአዉሮፕላኑ የላይኛዉ አካል እስከ መጨረሻዉ ሞተር ድረስ መቃጠሉን የመርማሪ ተቋሙ ጋዜጣዊ መግለጫዉ ያትታል። የአዉሮፕላኑ ዉስብስብ ክፍሎች በመጎዳታቸዉ የምርመራዉ ሂደት ግዜ ሳይፈጅ እንደማይቀር ተያይዞ ተጠቅሶአል። እንድያም ሆኖ ሌሎቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር የመንገደኛ ማጓጓዣ አዉሮፕላኖች በረራቸዉን መቀጠላቸዉ ካፒቴን ደስታ ዘርኡ ገልጸዉልናልድሪምላይነር የተሰኘዉ አሜሪካ ሰራሽ አዉሮፕላን ከዚህ ቀደም የባትሪ ችግር አጋጥሞት በመላዉ ዓለም የሚገኙ ድሪምላይነር ቀዉሮፕላኖች እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸዉ የሚታወስ ነዉ።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሀመድ