1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦብነግ ሥምምነት

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 2 2003

ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የተሰኘዉ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ረሺድ አብዲ እንደሚያምኑት ግን ድርድር-ስምምነቱ ምን ሆነ ምን የኢትዮጵያ መንግሥት የመርሕ ለዉጥ ማድረጉን የሚያሳይ ከሆነ እና ከልብ የመነጨ ከሆነ ጠቃሚ ነዉ።

https://p.dw.com/p/PcmQ
ጎዴ አጠገብ-ግጭቱ ብዙ ሰዉ ጎድቷልምስል picture alliance/dpa

ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ዛሬ የሠላም ሥምምነት የተፈራረመዉ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦብነግ) ጠቅላይ ወይም ላዕላይ ምክር ቤት የሚወክለዉ ቡድን ማንነትና ብዛት ብዙም እዉቅና እንደሌለዉ አንዳድ የፖለቲካ ተንታኞች እያስታወቁ ነዉ።ዉጪ የሚገኙ የኦብነግ ባለሥልጣናትም ግንባራቸዉ ከመንግሥት ጋር የሚያደረገዉ ድርድርም ሆነ ስምምነት የለም ብለዋል።ይሁንና የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ አስተንታኝ አቶ ዩሱፍ ያሲንና International Crisis Group የተሰኘዉ ጥናት ተቋም ባልደረባ ረሺድ አብዲ በየፊናቸዉ እንዳሉት ድርድር ስምምነቱ ሁሉንም የፖለቲካ አንጃዎች ካካተተና በቅንነት ላይ ከተመሠረተ ላካባቢዉ ሠላም ጠቃሚ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።

ዉጪ የሚገኙት አንዳድ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ግንባራቸዉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተደራደረ አይደለም።የሚፈርመዉም የሠላም ሥምምነት የለም።በተለይ ዶሐ-ቀጠር የሚገኙት አንድ የግባሩ ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት ግንባሩ እስካሁን በሚያደርገዉ የነፃነት ዉጊያ ይቀጥላል።አቶ ዩሱፍ ያሲን በበኩላቸዉ ዛሬ ከመንግሥት ጋር የሠላም ዉል የተፈራረመዉ ሐይል ማንነት ግልፅ አይደለም።

ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የተሰኘዉ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ረሺድ አብዲ እንደሚያምኑት ግን ድርድር-ስምምነቱ ምን ሆነ ምን የኢትዮጵያ መንግሥት የመርሕ ለዉጥ ማድረጉን የሚያሳይ ከሆነ እና ከልብ የመነጨ ከሆነ ጠቃሚ ነዉ።

«ድርድሩ ለዉጤት እንዲበቃ እና በአካባቢዉ ያለዉን ሁኔታ እንዲቀይረዉ ቅንነትና ታማኝነት ሊኖረዉ ይገባል።አላማዉ በኦጋዴን አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሐይላትን በሙሉ ለመከፋፈል ከሆነ ግን ለዉጤት አይበቃም።ሁኔታዉን ማረጋጋትም አይችልም።»
አቶ ዩሱፍ ያሲንም የረሽድን ሐሳብ ይጋራሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጥቂት ወራት በፊት የምዕራብ ሶማሊ ነፃ አዉጪ ግንባር ከተሰኘዉ ቡድን ጋር የሠላም ስምምነት ተፈራርሞ ነበር።በዚያዉ ሰሞን የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ጦራቸዉ ሰወስት መቶ ያሕል የኦብነግ ደፈጣ ተዋጊዎችን መማረኩን አስታዉቀዉ ነበር።

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ