1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የደቡብ አፍሪቃ መጤ-ጠል ኹከት እና የኢትዮጵያውያኑ ሥጋት

ረቡዕ፣ የካቲት 22 2009

ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪቃ እንደገና በመጤ-ጠል ተቃውሞ እና ኹከት ተንጣለች። ጊዜ እየቆጠረ የሚያገረሸው የአገሬው ተቃውሞ ዘንድሮ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሶማሊያ እና ናይጄሪያ ዜጎች ላይ አነጣጥሯል። ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም መጪው ጊዜ አስጊ ነው ሲሉ ይናገራሉ። 

https://p.dw.com/p/2YTv0
Südafrika Pretoria Unruhen wegen Migranten
ምስል AFP/Getty Images

የኢትዮጵያውያኑ ፈተና በደቡብ አፍሪቃ

 የሖሳዕናው ልጅ ፊንያስ አበራ በፕሪቶሪያ ከተማ ያገሩ ልጆች ከከፈቱት ሱቅ ውስጥ መሥራት ከጀመረ አመት ሞላው። ፊንያስ ጓዙን ሸክፎ ደቡብ አፍሪቃ የከተመው የተሻለ ሥራ እና ገቢ ፍለጋ ነበር። ፊንያስ የደቡብ አፍሪቃው ሥራ ቢመቸውም ከአምስት አመት በላይ የመቆየት እቅድ የለውም። ፊንያስ አበራ ሁሉ የተሻለ የሥራ እድል እና ገቢ ፍለጋ ለሚያማትሩ ኢትዮጵያውያን ደቡባዊውን የፍልሰት መሥመር ተከትለው ፕሪቶሪያን ወደ መሳሰሉ ከተሞች መትመም ከጀመሩ አመታት ተቆጠሩ። አብዛኞቹ ኬንያ እና ታንዛኒያን የመሳሰሉ አገራት አቋርጠው በሕገ-ወጥ መንገድ ደቡብ አፍሪቃ ለመድረስ በመሞከራቸው መከራ እና ችግር አያጣቸውም። በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ.ም. የለንደን የኤኮኖሚ እና የፖለቲካ ትምህርት ቤት መረጃ እንዳተተው በየአመቱ ከ17,000 እስከ 20,000 የሚደርሱ ሶማሊያውያን እና ኢትዮጵያውያን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ይጓዛሉ። ከዚህ ቁጥር ውስጥ ወደ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ይኸው ትምህርት ቤት በዘገባው ገልጦ ነበር። ከተለያዩ የአኅጉሪቱ ክፍሎች ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚጓዙት ሥራ ፈላጊዎች ጊዜ እየጠበቀ ብቅ እያለ አገሪቱን የሚያምሳት መጤ-ጠል ኹከት ይፈትናቸዋል። ፊንያስ የሚሰራበት የፕሪቶሪያ ከተማ ክፍል ወቅታዊው መጤ-ጠል ኹከት ባይደርስበትም ጉዳዩ ግን ያሳስበዋል።

ባለፈው ሳምንት የደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ በፕሪቶሪያ የተቀሰቀሰውን መጤ-ጠል ተቃውሞ ለመበተን አስለቃሽ ጭስ፤ የጎማ ጥይት እና ውሐ ለመጠቀም ተገዷል። ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ጸረ-መጤውን ኹከት አውግዘው መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል። ፖለቲከኞቹ «ሁሉን ተቀባይ» የሚሏት ደቡብ አፍሪቃ እንደገና እየተፈተነች ነው። ባለፈው አርብ ኢትዮጵያውያን፤ ሶማሊያውያን እና ናይጄሪያውያንን ጨምሮ በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች በአገሪቱ የተቀሰቀሰውን መጤ-ጠል እንቅስቃሴ በመቃወም በፕሪቶሪያ ሰልፍ ወጥተዋል። ለሕይወታችን እንሰጋለን ያሉት የውጭ አገር ሰዎች ራሳቸውን ለመከላከል መሞከራቸውን ይናገራሉ። ደቡብ አፍሪቃውያኑ በበኩላቸው የውጭ አገር ዜጎች ሥራችንን ነጥቀውናል ሲሉ ይወቅሳሉ። በፕሪቶሪያ ዙሪያ የሚኖረው ዳናን ኑቾ ከአስር አመታት በላይ በደቡብ አፍሪቃ ኖሯል። ደቡብ አፍሪቃ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ አገር ዜጎች ይኖሩባታል። በባለፈው ሳምንት ኹከት በፕሪቶሪያ አካባቢ የንግድ ሱቆች ተዘርፈዋል። ከፕሪቶሪያ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው አተሪድገቪል መንደር ብቻ 20 ሱቆች ኢላማ ሆነዋል። ከጁሐንስበርግ በስተደቡብ በሚገኘው የሮዝተንቪል መንደር ነዋሪዎች 12 መኖሪያ ቤቶችን አጥቅተዋል። የአገሪቱ ፖሊስ ጣልቃ ከገባ በኋላ ረገብ ያለው ኹከት ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘቱ ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው። የደቡብ አፍሪቃው የዶይቼ ቬለ ወኪል ቱሶ ኩሕማሎ የደቡብ አፍሪቃ ሰማይ አሁንም ለስደተኞቹ የስጋት ዳመና አርግዟል ባይ ነው።
«ሁኔታው ምንም የማይታወቅ ነው። ቀጣዩ ጥቃት መቼ እና የት እንደሚፈጸም ስደተኞች የሚያውቁት ነገር የለም። በባለፈው አርብ ተቃውሞ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ግጭቱ መቆም አለበት ብሏል። ፖሊስ የአስለቃሽ ጭስ የመሳሰሉ ነገሮችን በመግባት ጣልቃ ሲገባ ስደተኞቹ ሁሉም ነገር ያለቀ መስሏቸው ነበር። ነገር ግን በሳምንቱ መጨረሻ የውጭ አገር ሰዎች ንብረት የሆኑ የንግድ ሱቆች ተዘርፈዋል። በጁሐንስበርግ በእኩለ ለሊት ወደ 15 የሚጠጉ ሰዎች ፖሊስ እስኪመጣ ድረስ ስደተኞችን ሲያሰቃዩ እና ሱቆቻቸውን ሰብረው ሲገቡ ነበር። በአሁኑ ወቅት ያለው ለስደተኞች አስፈሪ ሁኔታ ነው። ነገሩ ሁሉ በውጥረት የተሞላ ነው። መንግሥት ይኸ ድርጊት ሊቆም ይገባል ይበል እንጂ ሕዝቡ እየሰማ አይደለም።» 
ዳናን ኑቾ እንደሚለው በሰሞኑ ኹከት በኢትዮጵያውያኑ ላይ የከፋ ጥፋት አልደረሰም። አሁን ሁኔታው ተረጋግቷል የሚለው ዳናን ዳግመኛ ቢቀሰቀስ ሊደርስ የሚችለው ጥፋት ያሰጋዋል። 
የጁሐንስበርግ ከተማ ከንቲባ ሔርማን ማሻባ በውጭ አገር ዜጎች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት እና ለተቀሰቀሰው ኹከት መነሾው ደካማው ኤኮኖሚያዊ እድገት እና በደቡብ አፍሪቃ ተንሰራፍቷል ያሉት የተዛባ የኃብት ክፍፍል ነው ሲሉ ተናግረዋል። ከንቲባው የሰጧቸው አስተያየቶች መጤ-ጠል ጥቃቶች እንዲባባሱ አድርገዋል የሚል ወቀሳም ይቀርብባቸዋል። ቱሶ ኩሕማሎ እንደሚለው በከንቲባው ላይ የሚሰነዘረው ወቀሳ ከመንግስትም ጭምር ነው።«ብዙ ሰዎች በተለይ የውጭ አገር ሰዎች ለተቀሰቀሰው መጤ-ጠል ተቃውሞ ማሻባን ይወቅሷቸዋል። ባለፈው አመት ታኅሳስ ወር በጁሐንስበርግ የሚገኙ ሁሉም ሕገ-ወጥ ስደተኞች ወንጀል እየፈጸሙ በመሆኑ ለቀው መውጣት አለባቸው የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር። ከዚያ በኋላ ነው ተቃውሞዎቹ የተቀሰቀሱት። ከንቲባው የኤኮኖሚው ሁኔታም ለኹከቱ መባባስ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል። ሰዎች በዚህ አስተያየታቸው ይስማማሉ። የውጭ አገር ሰዎች ላይ ጥቃት የሚፈፅሙት ዜጎች ሥራ አጥ ናቸው። ሥራ አጦቹ ዜጎች የውጭ አገር ዜጎች የተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ለእኛ ይገባናል ባይ ናቸው። ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች የቀውሱ አካል መሆናቸው እርግጥ ነው። ማሻባ በመንግሥት ጭምር ነው እየተወቀሱ ያሉት።  የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒሥትሩ የማሻባ አስተያየት ግዴለሽነት የተሞላበት እና ከእርሳቸው የማይጠበቅ ነው ሲሉ ተችተዋል። ነገር ግን መንግሥት ማሻባ ለኹከቱ መቀስቀስ ቀጥተኛ ምክንያት ናቸው አላለም። አሁን በማሻባ እና በመንግሥት መካከል እንካ ሰላንትያ ተቀስቅሷል። በተቃውሞዎቹ ላይ ለሚሳተፉ የደቡብ አፍሪቃ ዜጎች ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ፤ሥራ አጥነት አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸው። ለዚህም ነው ሥራችንን እና እድሎቻችንን ነጥቀውናል ሲሉ የሚከሷቸው። ከዚህ በተጨማሪ የውጭ አገር ሰዎች ወንጀል ይፈፅማሉ፦በዚህም አገራችንን ለቀው ይውጡ ሲሉ ይደመጣል። ይኽ በርካታ ተቃዋሚዎች ከማሻባ ጋር ከሚስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።»
ደቡብ አፍሪቃ ከገባ አስር አመታት ላስቆጠረው ዳናን መጪው ጊዜ አስጊ ይመስላል። አገሪቱ በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ.ም. የምታካሒደው ምርጫ ደግሞ የእነ ዳናን ሥጋት ያጠናክረዋል። 
ደቡብ አፍሪቃ እንዲህ መጤ-ጠል እንቅስቃሴ ስታስተናግድ የመጀመሪያዋ አይደለም። ከሁሉም የከፋው እና በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ኹከት የ60 አፍሪቃውያንን ህይወት ነጥቋል። ከሁለት አመት በፊት በጁሐንስበርግ እና ደርባን የተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ኹከት ሰባት ሰዎች ተገድለዋል። ቱሶ ኩሕማሎ  የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት የተለያዩ ተቋማት መሰል ኹከት ሊቀሰቀስ ይችላል ሲሉ የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ችላ ብሎታል ሲል ይናገራል። ቱሶ የፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ መንግሥት ከቃላት የዘለለ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ተስኖታል ባይ ነው። ከጁሐንስበርግ ወደ ፕሪቶሪያ የተስፋፋው ይኸ ኹከት በደርባንም ሊቀጥል ይችላል የሚል ሥጋት መኖሩን ቱሶ ኹሕማሎ ተናግሯል። ዳናን ኑቾ የበርካታ አገራት ድንበር አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለሚዘልቁ አዲስ ስደተኞች ፈታኝ ሆናለች ሲል ያስጠነቅቃል።

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ

Südafrika Pretoria Unruhen wegen Migranten
ምስል Getty Images/AFP/M. Longari
Friedensmarsch in Durban Südafrika
ምስል Getty Images/Afp