1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያዉያን የሥነ-ጥበብ ድግስ በጀርመን

ሐሙስ፣ ሰኔ 16 2008

ከሦስት ሳምንት ግድም በፊት የራድዮ ጣብያችን ከሚገኝበት ከቦን ደቡባዊ ምሥራቅ 310 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ክላይን ዛስን አነስተኛ ከተማ ዉስጥ በሚገኝ ጥንታዊ የሥነ-ጥበብ ማሳያ ታሪካዊ ሙዚም ዉስጥ ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ በኢትዮጵያ የነበሩ ጀርመናዉያን ኢትዮጵያን በተመለከተ ያቀረቡትን የሥነ-ጥበብ ሥራዎች አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/1JBzb
Deutschland Aida Muluneh City Life Ausstellung Kunststation Kleinsassen Äthiopien
ምስል David Krut Projects/Aida Muluneh

የኢትዮጵያዉያን የሥነ-ጥበብ ድግስ በጀርመን

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ጀርመን ፉልዳ ከተማ ባለች አንዲት አነስተኛ ከተማ በሚገኝ ታሪካዊ ኢግዚቢሽን ዉስጥ ለሦስት ወራት የሚዘልቅ የሥዕል አዉደ ርዕይ የመክፈቻ ሥነ- ስርዓት ላይ የተገኘዉ የአርቲስት ስለሺ ደምሲ ወይም በመድረክ ስሙ ጋሽ አበራ ሞላ፤ ዓዉደ ርዕዬን ለመጎብኘት የመጣዉ ታዳሚን አስደሞም ነበር።

Kunstausstellung Kunststation Kleinsassen 05.06.2016
ምስል DW/A. Tadesse

ፉልዳ የተሰኘችዉ ሰፋ ያለች ከተማ አዋሳኝ ላይ የምትገኘዋ አነስተኛዋ የጀርመን ክላይን ዛሰን ከተማ፤ ጥንታዊ የእግዚቢሽን ማዕከል በመያዝዋ በዓለም ታዋቂ የሆኑ ሰዓልያን ይጎበኝዋታል፤ የሥነ-ጥበብ ሥራዎቻቸዉንም ያቀርባሉ። የዛሬ ሦስት ሳምንት ግድም ኢትዮጵያዉያን ሰዓልያንን ጨምሮ ቆይታቸዉን በኢትዮጵያ አድርገዉ ኢትዮጵያን በሥነ-ጥበብ ስራዎቻቸዉ ያስቀመጡ ጀርመናዉያን ሥራዎቻቸዉን ለሦስት ወራት በሚቀርበዉ ዓዉደርዕይ አቀርበዋል። በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያዉያን ሠዓሊዎች በቪዛ ችግር ምክንያት በአካል ባይገኙም ሥራዎቻቸዉ በዚሁ ዓዉደ ርዕይ ላይ ቀርቦአል። ከኢትዮጵያዉያን ጋር የቆየ ግንኙነት ስላላቸዉ ለሃገሪቱ ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸዉ የሚናገሩት የኤግዚቢሽኑ ዋና ተጠሪ ሞኒካ ኤበርቶቭስኪ፤ በሚኖሩበት አካባቢ የኢትዮጵያን ገፅታ ማሳየት የሚመኙት ነበር።

«ይህን አዉደ ርዕይ ለማዘጋጀት ሳስብ ብዙ ጊዜያትን ወስዶብኛል ይህን የእግዚቢሽን ማዕከል በአስተዳዳሪነት ስመራም አንድ ዓመት ሆነኝ ። ከአንድ ዓመት በፊት ረዘም ላለ ጊዜ እኖር የነበረዉ በበርሊን ነዉ። በርሊን ሳለሁ እራስንህ ርዳ በሚል ኢትዮጵያዉያን ማኅበር ዉስጥ በንቃት ስሳተፍ ቆይቻለሁ። ማኅበሩ የኢትዮጵያዉያን እና የጀርመናዉያን ስለነበር ከኢትዮጵያዉያን ጋር ብዙ ለመገናኘትና ለመተዋወቅ በቅቻለሁ። ኢትዮጵያዉያኑን በቅርበት እያወኩዋቸዉ ስሄድ ስለሃገሪቱና ስለህዝቧ የማወቅ ጉጉት እያደረብኝ መጣ ደሞ ከዝያ ሌላ ኢትዮጵያዉያን በጥሩነታቸዉ ከዓለም አንደኛ ናቸዉ።»

Yenatfenta Abate Vorbereitung der eignen Arbeit zur Ausstellung im Goethe Institute Addis Künstlerin aus Äthiopien
ምስል Azeb Tadesse Hahn

በአካባቢዉ ላይ በርካታ ኢትዮጵያዉያን እና ኤርታራዉያን እንደሚኖሩ የገለፁልን ሞኒካ ኤበርቶቭስኪ በተለይ በከተማዋ በሚገኘዉ የስደተኞች መኖርያ ዉስጥ የሚኖሩ ኤርትራዉያን እና ኢትዮጵያዉያን ያዘጋጁት ባህላዊዉ ምግብ እንጀራና ወጥ በሽያጭ መልክ ቀርቦአል። ገቢዉም የስደተኞች ጣብያዉ ወጭ የሚዉል መሆኑ ተመልልክቶአል። ሞኒካ ስለዓዉደ ርዕዩ በመቀጠል።

«ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ማኅበራት ጋር ሰርቻለሁ ለምሳሌ ሊስትሮ የተባለዉን ድርጅት የማዉቀዉ ከምስረታዉ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት ጀምሮ ነዉ። ይህን የእግዚቢሽን ማዕከል በመሪነት ማገልገል ስጀምር ስለኢትዮጵያ ማቅረብ እንደምችል ለኔ ግልፅ ነበር። በዚህም በኢትዮጵያ የሚገኙ ሥነ-ጥበባትና የኪነ-ጥበብ ሰዎችና ሥራቸዉን እንዲሁም በጀርመን የሚኖሩ ሰዓልያንና ሥራቸዉን በጋራ እቅድ ይዤ ይኸዉ ለእይታ በቅቶአል። ይህን የስዕል አዉደ ርዕይ ያየ ብዙ ይጠይቃል፤ ብዙ ያዉቃል፤ ይተዋወቃል እጅግ ጥሩ ነገር ነዉ። በኢትዮጵያ ያሉ ሰዓሊዎች እዚህ ካሉት ኢትዮጵያዉያን ሥራዎች ጋር ሌላ አይነት ዘዴና አያያዝ እንዳላቸዉ መረዳት ይቻላል።»

ሠዓልያኑ በቀለማቸዉ ኢትዮጵያን በተለያየ መልክዋ ባለ ክራሩ ስለሺ ደምሴ እንዲህ በክራሩ በአማርኛ እያዜመ በእንጊሊዘኛ እየተረጎመ የተሰበሰበዉን ሕዝብ አጀብ ሲያሰን ማየቱ አይደለም ኢትዮጵያዉያኑን ብቻ ይህ አዉደርእይ እንዲዘጋጅ የፈቀዱትን እንደፈንዲሻ ሲያስፈነድቅ ማየቱ በጣም ያስደስታል።

Kunstausstellung Kunststation Kleinsassen 05.06.2016
ምስል DW/A. Tadesse

ከያኒ ስለሺ ደምሴ 19 ሰዓልያን የሥዕል ሥራዎቻቸዉን ባቀረቡት አዉደ ርዕይ መክፈቻ ላይ ባቀረበዉ ሦስት እና አራት ሙዚቃ ብቻ የሙዚቃ ድግሱ አላበቃም። የክላይን ዛስን ከተማ ሕዝብ አርብ ለቅዳሜ አጥብያ በስለሺ ደምሴና በአንድ ክራሩ ጥበባዊ ችሎታዉ ሲዝናና በሳቅ ሲፈርስ ነዉ ያመሸዉ። በአዉደ ርዕዩ መክፈቻ እለት ወደ ሦስት መቶ የሚጠጋ የከተማ ነዋሪና በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ነበር የተገኙት ። ተቀማጭነቱን በበርሊን ያደረገዉ የበርሊኑ የሊስትሮ ድርጅት የዚህ አዉደ ርዕይ ተባባሪ አዘጋጅም ነበር። የድርጅቱ መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሻንቆ፤ የሊስትሮ ሳጥን አዉደርዕይ ዘርግተዉ ሳለ ከዛሬ አስራ ሦስት ዓመት በፊት የተዋወቅዋት የኢግዚቢሽኑ ዋና ተጠሪ የኢትዮጵያዉያን ሥነጥበብን ለማሳየት በመፈለጋቸዉ፤ ሊስትሮ ድርጅት ሠዓልያኑን በማሰባሰብ መርዳታቸዉን ነግረዉናል። በዓዉደርዕዩ ላይ የተለያዩ የሊስትሮ ሳጥኖች፤ የሊስትሮን ማንነት በመግለፅ የተመልካቹን ቀልብ ስበዉ ነበር። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ