የኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ጩኸት
ሐሙስ፣ ኅዳር 5 2006
የሳዑዲ አረቢያ ፀጥታ አስከባሪዎችና ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ይተባበራሉ የሚባሉት የሐገሬዉ ወጣቶች በሕገ-ወጥ የዉጪ ሐገር ነዋሪዎች በተለይ በኢትዮጵያዉያን ላይ የሚፈፅሙት በደል በየሐገሩ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ለተቃዉሞ ሠልፍ እያሳደመ ነዉ።የኢትዮጵያዉያን ትኩረት ሳዑዲ አረቢያ ላይ ባነጣጠረበት ባሁኑ ወቅት በሌሎች ሐገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች እየተበደልን ነዉ ይሉ ይዘዋል።ስደተኞቹ እንደሚሉት የየሐገሩ ባለሥልጣናት ያስሯቸዋል፥ ያንገላቷቸዋል፥ ያስፈራሯቸዋል፥ ቀለል ሲል ደግሞ ጉቦ ይጠይቋቸዋል።በየሥፍራዉ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ለዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች በየጊዜዉ አቤት ቢሉም እስካሁን የረዳቸዉ የለም።
ኢትዮዮጵያዊዉ ወጣት ይሰደዳል።የሌሎች ስደተኞች ስቃይን እየሰማም፥ ባገኘዉ አጋጣሚ፥ በቀለለዉ አቅጣጫ በገፍ ይሰደዳል።አቅጣቸዉ ወደ አዉሮጳ ከሆነ የሳሕራ በረሐን ለማቋረጥ ሲሞክር በዉሐ-ጥም ይሰቃያል፣ የጠናበት ይሞታል።በአጋቾች ይታፈናል፥ ይደፈራል፥ ይገረፋል፥ አካሉ እየተተለተለ ይቸበቸባል።በረሐዉን ማቋረጥ የቻለዉ፥በባሕር ወሐ-መበላት ይጠብቀዋል።
እሱና ብጤዎቹ ምናልባት አዉሮጳን እያለሙ ወደ ሜድትራኒያን ባሕር አንጋጠዉ ይሆን-ይሆናል።መከራዉ ግን የሳሕራ-በረሐን እስኪረግጥ አልጠበቀዉም።ወደ ሱዳን ቀረበበት።
በየመን-አሳብሮ በነዳጅ ሐብት ከበለፀጉት የአረብ ሐገራት ለመድረስ ያለመዉ የአቀባባይ ደላሎችን ዱላ፥የአጋቾችን አፈና ካለፉ ከባሕር-ማዕበል፥ ከየመን በረሐና በረሐኞች ጋር መጋፈጥ ግዱ ነዉቁልቁል-ደቡብ አፍሪቃ ለመድረስ የሚሹ የኬንያን ጠረፍ ከረገጡበት ጊዜ ጀምሮ፥ የደላሎች፥ የወረበሎች፥ የድንበር ተቆጣጣሪዎች ዘረፋ፥ ዱላ፥ እስራትን፥ በብረት ሰንዱቅ ታፍኖ አለያም፥ሐይቅ ዉስጥ ተደፍቆ መሞትን ለመጋፈጥ መቁረጥ አለባቸዉ።እሱ ብዙዉን መከራ አልፎ፥ ሞትን አምልጦ ደቡብ አፍሪቃ ሲገባ-እፎይ የሚል መስሎት ነበር። ግን ሌላ ፍዳ-ጠበቀዉ። ሌላዉ ከደቡብ አፍሪቃ ተመሳሳይ አቤቱታ ያሰማል፤ ገና ከኬንያ ያለለፉትም-ችግር አልራቃቸዉም።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ