1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራን እስላማዊ አብዮትና አለም አቀፉ ማሕበረስብ

ሰኞ፣ የካቲት 2 2001

---ኢራናዉያን በሙሉ ተመሳሳይ መልስ ይሰጡኛል።»አለ።«ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ነበረን አሜሪካ አፈረሰችብን እንጂ» የሚል

https://p.dw.com/p/GqKk
የንጉስ ፓሕሌቪ ሐዉልት ተገደስምስል Iranische Quelle ohne internationales Copyright

ካርተር እየዛቱባት፥እያስቀጧት፥ ተደራድረዋት-ተዋርደዉባት በምርጫ ተሸነፉባት።ሬጋን የማሸነፈቸዉ መሰረት አድርገዋት፤ ሊያጠፏት-እያወገዟት፤ በኢራቅ እያስወጓት የጦር መሳሪያ ሸጠዉላልት-ቀለሉባት።ቀዳማዊ ቡሽ እያወገዟት፣ የጎረቤት ጠላቷን አዳከሙላት።ክሊንተን እየወነጀሏት ለድርድር ከጀሏት።ኢራን እስላማዊት ሪፐብሊክ።ለቡሽ ዳግማዊ የሰይጣን ዛቢያ ናት።ለድፍን አሜሪካ አሸባሪ፣ ለድፍን ምዕራ ፀረ-ዲሞክራሲ፤ ለእስራኤል ቀንደኛ ጠላት፣ ለአረቦች ክፉ ባላጋራ፣ ለኒኩሌር ቦምብ የምታሴር አደገኛ ሐገር ናት።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።ሳምንት የጀመርነዉን የኢራንን የእስላማዊ አብዮት ምክንያት፤ ሂደት ዉጤት ቅኝታችንን እንቀጥላለን።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ድምፅ

የጆርጂያዉ አገረገዢ ጀምስ አርል ወይም ጂሚ ካርተር ትንሹ በ1976 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዋይት ሐዉስ ሲገቡ፣ ቴሕራን ላይ ብልጭ ድርግም የሚለዉን ሕዝባዊ አመፅ ሒደት ዉጤት በጥሞና ለመከታተል ጊዜ አልነበራቸዉም።

ካርተር ሥልጣን ከመያዛቸዉ ከአምስት ወር በፊት የሞቱትን የኮሚስታዊት ቻይና መስራች ማኦ ዜዱንግን ለመተካት የማኦ ባለቤት ቺያንግ ቺንግ በሚመሯቸዉ አክራሪዎችና ሑአ ኩኦ-ፌንግ የሚመሩት የለዘብተኞች ጎራ የገጡሙት ግብግብ የጠንካራይቱን ሐገር የወደፊት ጉዞ አሳክሮታል።

በቤጂንግና በሞስኮ የሚደገፉት የቬትናም ኮሚንስቶች በዩናይትድ ስቴትስ ላይ የተቀዳጁት ድል የልብ ልብ የሰጣቸዉ ሐይላት ከአዲስ አበባ እስከ ሉዋንዳ የሚገኙ አብያተ መንግሥታትን በቆጣጠሩበት በዚያ ወቅት የቤጂንግ መሪ ማንነት፣ የአመራሩ እንዴትነት አለመታወቁ ከቶኪዮ-እስከ ሶል ለሚገኙ የዋሽንግተን ወዳጆችና ጥቅሟ በርግጥ አደገኛ ነዉ።

እስራኤልና ግብፅ ተኩስ አቁም ቢያዉጁም ወታደሮቻቸዉ ጠመንጃቸዉን እንደወደሩ ነዉ።ሊባኖስ በርስበርስ ጦርነት መንፈር ይዛለች።የሕንድና የፓኪስታን ፍጥጫ ሕንድ አዉቶሚክ ቦምብ ሰራች በመባሉ ሰበብ ንሯል።በ1973 ካቡል ላይ በተደረገዉ መፈንቅለ መንግሥት ሰበብ የተቀሰቀሰዉ የአፍቃኒስታን ትርምስ ሶቬቶችን ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እየጋበዘ ነዉ።

በርግጥም አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ከቤጂንግ-እስከ ሞስኮ፣ ከሐኖይ እስከ ካቡል፥ ከቴል አቪቭ እስከ ካይሮ በነበረዉ ምሥቅልቅል መሐል ለቴሕራን ፖለቲካዊ ቀዉስ ልዩ ትኩረት የሚሰጡበት ምክንያት አልነበረም።ፕሬዝዳት ካርተር በ1978 ከኢራኑ ሻሕ ጋር ዋንጫቸዉን እያጋጩ ንጉሱ እያንቆለጳጳሱ በሐገራቸዉ ሕዝብ እንደሚፈቀሩ ሲገልጡ በቴሌቪዥን የተመለከተዉ የኢራን ሕዝብ እንደ ንቀት እንጂ ዋሽንግተኖች ሥለ ቴሕራን ሁኔታ በቅጡ ያለማወቃቸዉ ምልክት አድርጎ አልትረጎመዉም ነበር።

ንጉሠ-ነገስት መሐመድ ሬዛ ፓሕሌቭ በ1970ዎቹ፥ እና በ1940ዎቹ ወይም ሐምሳዎቹ መካካል የነበረዉን ልዩነት እንዳያጤኑት ከካርተር የተንቆረቆረቆረላቸዉ ሙገሳ-አድናቆት ሳይጋርዳቸዉ አልቀረም።በሕዝቤና በኔ መሐል ንፋስ አይገባም አይነት አሉ።

ድምፅ ፩

«በኔና በሕዝቤ መሐል ያለዉ ልዩ ግንኙነት እስከቀጠለ ድረስ ይሕን ወዳጅነት ለማበላሸት በመሐላችን የቆመ ሰዉ የት እንዳለ እና ማን እንደሆነ አላዉቅም።»

ሻሁ ከፈጠጠዉ እዉነታ ይልቅ በ1941 ካነገሱ፥ በ1953 ከተወገዱበት ዙፋን መልሰዉ ካወጧቸዉ ከለንደን-ሞስኮ-ዋሽንግተን ወዳጆቻቸዉ ያንዳቸዉን ድጋፍ ሲያማትሩ፥ ብሬዥኔቭ እንደ ካርተር ሁሉ ሶልት ሁለት የሚባለዉን የጦር መሳሪያ ቅነሳ ዉል ለመፈረም ቀን እያሰሉ፥ አፍቃኒስታን ለመዉረር ያደባሉ።ሊንገሐን በታቸር እንዳይሸነፉ ያሴሩ ነበር።ሑኦ ኩአ ፌንግ የቤጂንግን ቤተ-መንግሥትን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል።

ሳዳትና ቤገን የሚፈርሙትን የሰላም ዉል ያስረቅቃሉ።ሌላዉ አለም የዋሽንግተን-ሞስኮ፥ የካይሮ-ቴል አቪቭ፥ የቤጂንግ-ለንደንን ሁነት ሂደት ሲከታተል ሻሁ የማያዉቁትን ያወቁ መሰሉ።ደከመኝ አሉ።

ድምፅ

«ከጥቂት ጊዚያት ወዲሕ መሰላቸትና ድካም ይሰማኛል።እና እረፍት እፈልጋለሁ።ከዚሕ ቀደም እንዳልኩት መንግስቱ ከተረጋጋ ወደ ዉጪ እጓዛለሁ።»

ተጓዙም። እስከ መጨረሻዉ።ጥር 16 1979።አረፉም።እስከ ወዲያኛዉ።አስደጁ፣ አስፈሪዉ ንጉስ መሰደጃ ፍለጋ ከግብፅ፣ ሞሮኮ፤ ከዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ አሜሪካ ሲባትሉ፣ ተሰዳጁ አያቶላሕ ሆሚኒ ከቱርክ ኢራቅ፤ ከኢራቅ ፈረንሳይ አስራ-አምስት አመታት ያንከራተታቸዉን ስደት ጨርሰዉ ቴሕራን ገቡ።የካቲት ፪ 1979።

ድምፅ

በዘጠነኛ ቀኑ ሆሚኒ የመሩት አብዮት-እስላማዊ አብዮት።ከነገ-በስቲያ ሮብ ሰላሳኛ አመቱ።

ድምፅ

የእስራኤልና ምዕራባዉያን ሐገራት በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ድርጅት ሐማስ በቅርቡ የገጠሙት ዉጊያ ጋዛን ሲያወድም ሐማስን የምታስታጥቀዉ ኢራን እንደሆነች የእስራኤል ባለሥልጣናት ያልተናገሩበት ወቅት አልነበረም።

ድምፅ

«የጦር መሳሪያ በድብቅ መግባቱ ሊቆም ይገባዋል።ሐሳቡ (ለሐማስ የሚደርሰዉን) የጦር መሳሪያ ከኢራን ወደ ግብፅ በሥዉር ለማስገባት የሚደረገዉን ሙከራ ለማስቆም ከግብፅ ጋር ተባብሮ ለመስራት ነዉ።»

ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዚፒ ሊቭኒ።በ2006 እስራኤልና ሌላዉ አሸባሪ የሚባለዉ የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕ ሊባኖስን ያደቀቀዉን ጦርነት ሲገጥሙ የቴላአቪቭና የዋሽንግተን መሪዎች ኢራን ሒዝቡላሕን ታደራጃለች፥ ታስታጥቃለችም በማለት ወንጅለዋት ነበር።የኢራቅ ደፈጣ ተዋጊዎች ኢራቅ የሰፈረዉን የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ግራ ቀኝ ሲያካልቡት የፕሬዝዳት ጆርጅ ቡሽ መስተዳድር ባለሥልጣናት ኢራን በተደጋጋሚ ሲወነጅሉ ነበር።

ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ከኢራቅ ወረራ፥ ከእስራኤል-ሒቡላሕ፥ ሐማስ ዉጊያ በፊት ገና በሁለት ሺሕ-ሁለት ኢራንን በስይጣን ዛቢያነት የወነጀሉት ኢራን አሸባሪዎችን ትደግፋለች፥ የኒኩሌር ቦምብ ለመስራት ታደባለች፥ዲሞክራሲያዊዉን ሥርዓት ትጻረራለች በሚል ነበር።

ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ሥለደረገችዉ መፈንቅለ መንግሥትና አሸባሪነት በመካከለኛዉ ምሥራቅ ሥላቆጠቆጠበት ሁኔታ የሚያትተዉን All the Shas Men የተስኘዉን መፅሐፍ ያሳተመዉ አሜሪካዊዉ ጋዜጠኛ ስቴቫን ኪንዘር «ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለምን አትመሰርቱም እያልኩ የጠየኳቸዉ ኢራናዉያን በሙሉ ተመሳሳይ መልስ ይሰጡኛል።»አለ።«ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ነበረን አሜሪካ አፈረሰችብን እንጂ»

ዩናይትድ ስቴስና ብሪታንያ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን የጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሙሳዴቅን መንግሥት በሐይል አስወግደዉ ሮም-የተሰደዱትን ሻሕ ከዙፋን ማዉጣቸዉን ለመግለፅ ነዉ።የኢራን ገዢዎች በርግጥ ፀረ-ዲሞክራቲክ ናቸዉ።ለዚያ ያበቃቸዉ ማንነት ግን ጋዜጠኛዉ እንደሚለዉ ግልፅ ነዉ።

ኢራን በድብቅ የኒክሌር ቦምብ ለመስራት እየሞከረች መሆኑ ብዙ አያጠያይቅም።አክራሪዉ ያሁኑ ፕሬዝዳት አሕመዲ ኒጃድም ባንፃራዊ መመዘኛ ለዘብተኛ የሚባሉት የቀድሞ ፕሬዝዳት አክበር ሐሺሚ ራፍሳንጃኒም ለሰላማዊ የሐል ምንጭ እናዉለዋለን የሚሉትን መርሐ-ግብር ለማስቆም የሚደረግባቸዉን ቅጣትና ጫና አንቀበልም ባይ ናቸዉ።

ድምፅ

«ለእናንተ ለምዕራቦች በግልፅ የምነግራችሁ ከማዕቀብ ዉሳኔዉ ምንም ማትረፍ እንደማትችሉ ነዉ።ከዚያ የምታገኙት እናንተን እራሳችሁን፥ መላዉ አለምን በተለይ ደግሞ የኛን አካባቢ ከችግር መዶል ብቻ ነዉ።ተገቢዉ መንገድ ይሕን ትርጉም አልባ አርቲቡርቲ ማቆም ነዉ።»

የኢራን ገገዢዎች ዛሬ ቦምብ ያመርቱበታል ተብለዉ የሚጠረጠሩ፥ የሚወነጀሉበት የአዉቶሚክ መርሐ ግብር የተጀመረዉ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ በ1953 መሐመድ ሙሳዴቅን አስወግደዉ ሼሁን መልሰዉ ከዙፋን በሰቀሉ ማግስት፥ በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍና ርዳታ ነበር።

ኢራን ከሐማስ እስከ ሒዝቡላሕ በአሸባሪነት የሚወነጀሉ ሐይላትን መደግፏ ግልፅ ነዉ።ከድፍን አረብ ሶሪያ ስትቀነስ ባንድ አብረዉ፥ ኢራቅን አስቀድመዉ፥በዩናይትድ ስቴትስ እየተደገፉ ኢራንን ሲወጉ የቴሕራን ሙላሆች የሳዳምን ጠላቶች፥ በአረብ-ምዕራቦች የተጠሉትን አሸባሪዎች ድጋፍ ማደራጀቱን ነዉ-የመረጡት።

ዩናይትድ ስቴትስ ሐገሯ የገቡትን ሻሕ ለኢራን እንድታስረክብ በመጠየቅ ሕዳር 1979 የኢራን ተማሪዎች ቴሕራን የሚገኙ ሀምሳ-ሁለት የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ሲያግቱ «The Athlantic Jouronal -Constitution የተሰኘዉ ጋዜጣ «የፋርሶች አረመኔነት» በማለት ኢራንን ካበሻቀጠ ወዲሕ ከአሸባሪነት፥ እስከ ኑክሌር አምራችነት የዘለቀዉ፥የቴሕራን ምዕራቦች ዉዝግብ እንደቀጠለ ነዉ።

ለዘብተኛ የሚባሉት መሐመድ ሐታሚ የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን በያዙበት ወቅት ከፕሬዝዳት ክሊንተን መስተዳድር ጋር የፈጠሩት የተለሳሰለ ግንኙነት ጥሩ ተስፋ ነበር። ወዲያዉ ግን ቡሽ ዋይት ሐዉስን፥ አሕመዲን ኒጃድ የቴሕራን ቤተ-መንግሥትን መቆጣጠራቸዉ ያልጠናዉን ተስፋ ባጭር ቀጭቶታል። አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ያሉና የሚሉት የሰላ-አመቱን ዉጥረት ለማርገብ በርግጥ አዲስ ተስፋ ነዉ።

ድምፅ

«ከኢራን ጋር ላለን ግንኙነት፥ ዲፕሎማሲን ጨምሮ ዩናይትድ ስቴትስ ያላትን አቅም በሙሉ መጠቀም መቻላችንን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነዉ።በበአለ-ሲመት ንግግሬ እንዳልኩት ኢራንን የመሳሰሉ ሐገራት በጡንቻ መታበያቸዉን ካቆሙ ከኛ በረጅሙ የተዘረጋ እጅ ያገኛሉ።»

የፊታችን ሐምሌ ኢራን በሚደረገዉ ፕሬዝዳትነታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ያስታወቁት መሐመድ ሐታሚ እድል ከቀናቸዉ ኦባማ የተሻለ ተደራዳሪ ያገኙ ይሆናል።ለአለም ደግሞ ሌላ ተስፋ።

ድምፅ

በ1979 አፍቃኒስታንን የወረረዉ የሶቬት ሕብረት ጦር መሸነፉ-ኮሚንዝምን ለማንኮታኮት ጥሩ መደላድል ሆኗል።የእነ-ቢላዳንን የአሸባሪነት መርሕ የተጠነሰሰዉ ግን ያኔ ነዉ።በዚያዉ አመት ግብፅ እና እስራኤ የሰላም ዉል ተፈርሟል።ሐማስም-ሒዚቡላሕም የበቀሉት ግን ከፊርማዉ በሕዋላ ነዉ።ሆሚኒ፥ ሳዳምም የሉም።የካምፕ ዴቪዱ ስምምነት፥እስራኤል ላይ የወረደዉ ሮኬት፥ ሊባኖስ-ጋዛ፥ ኢራቅን ያነፈረዉ ቦምብ-ሚሳዬል፥ በቴሕራን ላይ የሚዥጎደጎደዉ ዛቻ፥ እስላማዊ አብዮቱም ያመጣዉ ሰላም በርግጥ የለም።ሰላሳ-አመት።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Quellen,ZPR, Chronicle of the centurey,Wikipedia,Agenturen

NM/SL