1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራቅ የክዌት ወረራ እና ያስከተለው የተፈጥሮ አካባቢ ብክለት

ሰኞ፣ ሐምሌ 26 2002

ከ 20 ዓመት በፊት፣ በዛሬዋ ዕለት የቀድሞው የኢራቅ አምባገነን መሪ፣ ሳዳም ሁሴን፤ ንዑሷን ጎረቤታቸውን ክዌትን መውረራቸው የሚታወስ ነው።

https://p.dw.com/p/OaIQ
ምስል AP

ያኔ፤ ኢራቅ ጦሯን እንድትስወጣ ለአያሌ ወራት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቢቀርብላትም፣ የተከረው ነገር አልነበረም። በመሆኑም፣ ዩናይትድ እስቴትስ፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፈቃድ በማግኘት፣ እ ጎ አ በጥር ወር 1991 ዓ ም፤ «የበረሃ ማዕበል» የሚል ሥያሜ በተሰጠው ዘመቻ፤ ኢራቅን በመጀመሪያ በአየር ከደበደበች በኋላ አስከትላ፤ እግረኛ ጦር አዘመተች። በየካቲት ወር መጨረሻ ገደማ ላይ ክዌት ሙሉ-በሙሉ ነጻነቷ ተመለሰላት። ነገር ግን የኢራቅ ወታደሮች ሲያፈገፍጉ፣ እኩይ የበቀል ተግባር መፈጸማቸው አልቀረም። የነዳጅ ዘይት ኩሬ፣ እስከዛሬ ድረስ ተፈጥሮን ክፉኛ እንደበከለ ነው። Carsten Kühntopp ከአማን ዮርዳኖስ የላከልንን ዘገባ፤ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

ሬድሃ ኧል ሐሰን፤ በክዌት ካርታ ላይ በቢጫ ቀለም ሁለት ክቦች ያሠምራሉ፤ ምን ለማስረዳት ይሆን?!

«በእነዚህ 2 አካባቢዎች ነው ፤ የክዌት የነዳጅ ዘይት ማውጫ ጣቢያዎች የሚገኙት።»

ሬድሃ ኧል ሐሰን፤ በእነዚህ ቦታዎች ኅሊናን የሚሰቀጥጥ ሁኔታ ይታያል ባይ ናቸው። ኧል ሐሰን የሳይንስ ምሁርና ፣ በአገሪቱ የተፈጥሮ አካባቢ ላይ ፤ ከ 20 ዓመት በፊት የኢራቅ ወራሪ ጦር ያደረሰውን ብክለት ለማጽዳት ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የተቋቋመው የመንግሥት መ/ቤት ዋና ኀላፊ ናቸው።

«የሳዳም ሁሴን ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ያኔ፣ ከክዌት በኃይል እንድንወጣ ከተገደድን ፣ ሁሉንም በእሳት ነው የምንለኩሰው ሲል በግልጽ ነበረ ያስታወቀው። እናም 798 የነዳጅ ዘይት ማውጫ ጉድጓዶችን በአሳት ለኮሱ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንዳንዶቹ የነዳጅ ዘይት ጉድጓዶች፤ ከውስጥ ግፊት ባለመጠንከሩ ነበልባላቸው ቢጠፋም፤ ድፍድፉ ነዳጅ ዘይት እንደ ምንጫ ውሃ ወደ ውጭ መፍሰሱን ቀጠለ። እንዲያም ሆኖ በበረሃው ጎድጓዳ ቦታዎች መጠራቀሙን ቀጠለ። »

ያኔ በመንቀልቀል ላይ የነበሩት ቀሪዎቹ የክዌት ነዳጅ ዘይጫ ማውጫ ጉድጓዶች፤ ነበልባላቸው የጠፋው የኢራቅ ወታደሮች ተጠራርገው ከክዌት ከወጡ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር። እርግጥ ነው እስከዛሬ ድረስ፤ ከከርሠ ምድር እየወጣ የፈሰሰው ደፍድፍ ነዳጅ ዘይት ፤ በረሃ ውስጥ 2,400 ያህል ኩሬዎችን ፈጥሯል። በ 60 ካሬ ኪሎሜትር ቦታ ውስጥ በሚገኙት የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ኩሬዎች፤ አንዳንዶቹ የብዙ ሜትር ጥልቀት አላቸው ። ከዚህም ሌላ፤ ስዑዲ ዐረቢያን በሚያዋስነው ድንበር ከአንድ ሺ ኪሎሜትር በላይ ርዝማኔ ባለው የተቆፈረ ቦይ ፤ ሳዳም ሁሴን፤ባወጡት የጦር አቅድ መሠረት ፣ በመገሥገስ ላይ የነበሩትን ክዌትን ነጻ ለማውጣት የዘመቱትን ተባባሪ ጦር ኃይሎች ለመግታት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ሞልተው እንዲጋይ ማድረጋቸው የሚዘነጋ አይደለም።

«ቁሳዊውና ንጥረ-ነገራዊው የድፍድፍ ነዳጅ ዘይቱ የተፈጥሮ ባህርይ፤ እስካሁን ባለው ጊዜ ሙሉ-በሙሉ ነው የተለወጠው። ቀለል ያለው ተኗል። ከበድ ያለው ደግሞ እንደረጋ ነው የቀረው። በተጨማሪም እሳቱን ለማጥፋት ሲባል የተዛቀ አፈርና ከውቅያኖስ እየተቀዳ የተደፋ ጨው ይገኛል። ወፍራም አረፋማ ጭቃ ነው በረሃማውን ምድር ያለበሰው።»

ከዌት ለደረሰባት የተፈጥሮ አካባቢ ብክለት ፤ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት፤ ወደ 3 ቢሊዮን የሚጠጋ ዶላር ካሣ ሊሰጣት ቃል ገብቶ ነበረ። እርግጥ የሚከፈለው ገንዘብ የሚገኘው ካሣ መክፈል ካለባት ከኢራቅ ነው። ጦርነቱ ከተካሄደ 20 ዓመታት ቢያልፉም፤ እስካሁን የደፍድፍ ነዳጅ ዘይት ኩሬዎቹን ለማጽዳት አለመሞከሩ፤ ብዙዎቹን የክዌት ተወላቾች እያበሳጨ ነው። ሬድሃ ኧል ሐሰን የፈሰሰውንና በረሃ ላይ የተቋረውን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በተለመደው አሠራር ማስወገድ ከቶ እንደማይቻል ነው የሚነገሩት።

«አንድ ሰርሣሪና አፈር ደፊን ማሺን ወይም ቡልዶዘርን እናስብ፤ ከአንድ ቦታ ዝቆ በማውጣት ሌላ ቦት በመከመር አሸዋ ሊያለብስ ይችላል፤ ግን ይህ ሊሆን የሚችለው የሚጠረገው ጥቂት ሲሆን ነው። እኛ የምናወሳው፤ ከ 50 እስከ 60 ሚልዮን ኩብ ሜትር ጭቃ ነው። ሌላ ቦታ ይቀበር ሲባል፤ ያ ቦታ ለዚህ ዓለማ እንጂ ለሌላ ሊውል አይችልም ማለት ነው።»

ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የተንጣለለባቸውን ኩሬ መሰል ቦታዎች ለማጽዳት አስቸጋሪ የሚሆነው፤እጅግ መርዘኛውን የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ጭቃ ለመጥረግ፣ በመጀመሪያ ፣ ከውስጥ ምን እንዳለ ለማየት የሚያስችል ሥነ-ቴክኒክ እስካሁን የተሞከረ አለመሆኑ ነው። ሬድሃ ኧል ሐሰን ፤ እኩዩ የሳዳም የበቀል ቅርስ ከ 20 ዓመታት ወዲህም ቢሆን ከ ክዌታውያን አእምሮ የሚወገድ ያልመሰለበት ሁኔታ መቀጠሉ አይቀርም ሲሉ ሥጋታቸውን

አያይዘው ገልጸዋል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ