የኡጎ ሻቬዝ ዜና ዕረፍት
ረቡዕ፣ የካቲት 27 2005
06 03 13
የቬኑዙዌላዉ ፕሬዝዳት ኡጎ ሻቬዝ በመሞታቸዉ የተለያዩ ሐገራት መሪዎች እና የድርጅቶች ተጠሪዎች የሐዘን መግለጫ መልዕክት ሲያተላልፉ ነዉ የዋሉት።ከኩባ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ፥ ከኢራን እስከ ሩሲያ የሚገኙ የሻቬዝ ወዳጅና ተቃዋሚ መንግሥታት መግለጫዎችን አስተላልፈዋል። በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉን ደቡብ አሜሪካዊት ሐገር ለአስራ-አራት ዓመታት የመሩት ሻቬዝ ከነቀርሳ (ካንሰር) በሽታ ጋር ለሁለት ዓመታት ያሕል ሲታገሉ ከርመዉ ትናንት ነዉ ያረፉት።የግራ ፖለቲካ የሚያቀነቅኑት ሻቬዝ በአብዛኛዉ የሐገራቸዉ ደሐ ሕዝብ ና የግራ መርሕ በሚከተሉ መንግሥታት ዘንድ ሲበዛ ተወዳጅ፥ ሐብታሙ ዜጋቸዉና ምዕራቡ ዓለም አጥብቆ የሚጠላቸዉ መሪ ነበሩ።
እንደ ወታደር የተዋጉ፥ እንደ ጦር መኮን መፈንቀለ መንግሥት የሞከሩበት፥ እንደ መሪ መፈንቅለ መንግሥት ያከሸፉበት፥ድሆችን የረዱ፥ ሶሻሊስቶችን ያስተባበሩ፥ ኢምፔሪያሊትን ያወገዙበት ፈርጣማ ጉልበታቸዉን ነቀረሳ ገነደሰዉ።«ሞተ»የአሥራ-አራት ዘመኑ መሪ፥ ኡጎ ራፋኤል ሻቬዝ ፍሪያስ።በቃ፥ አለቀ፥ ደቀቀ፥ ተፈጠመ።«ዛሬ መጋቢት አምስት አስራ-ስድስት ሰዓት፥ ከሃያ አምስት ደቂቃ ላይ ፕሬዝዳት፥ ጠቅላይ አዛዥ ኡጎ ሻቬዝ አረፉ።ለሁለት ዓመታት ያክል ከበሽታቸዉ ጋር በፅናት ታግለዋል። ኡጎ ሻቬዝ ለዘላለም ይኑር።»
ምክትል ፕሬዝዳት ኒኮላስ ማዱሮ።የተደሰቱ አልጠፉም።አብዛኛዋ ቬኑዙዌላ ግን አዘነች፥ አረገደችም። እሳቸዉ ለዝንተ-ዓለም ሲያንቀለፉ አፍቃሪ፥ ተከታይ፥ አድናቂዎቻቸዉ እንባ እንደተራጩ ያለዕንቅልፍ አደሩ።
በ1975 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከካራካሱ የጦር አካዳሚ በተመረቀ ማግሥት ባሪናስ በተባለችዉ ግዛት ሸምቀዉ የነበሩትን የማርክሲስት ሌኒኒስት ደፈጣ ተዋጊዎችን የሚያጠቃዉ ጦር የመገናኛ ክፍል አዛዥ ሆኖ ዘመተ።ባሪናስ ሲደርስ ደፈጣ ተዋጊዎቹ ተዳክመዉ፥ ዉጊያዉም ቀዝቅዞ ሥለ ነበር፥ ለሚወደዉ ስፖርት፥ ለንባብና ፅሁፍ በቂ ጊዜ አገኘ።
የግዛቲቱ የቤዝቦል ቡድን እዉቅ ተጨዋች፥ የጋዜጣ ቋሚ አምደኛ፥ አንባቢም ሆኑ።የዚያን ቀን-ቃኚዉን ጦር የመምራቱ ሐላፊነት የእሱ ነበር።ከጦር ሠፈራቸዉ ጥቂት እንደተጓዙ ጥይት የቦዳደሳት፥ የዛገች መኪና አዩ።ብዙዎቹ መኪናዋን ብዙ ጊዜ ሥላዩት አለፏት።እሱ ግን ተጠጋት። መፅሐፍት፥ ወረቆቶች፥በራሪ ፅሑፎችና ሰነዶች ተከምረዉበታል።አማፂያኑ ጥለዉት የሸሿት መሆን አለባት።
ጓደኞቹን ችላ ብሎ አዋራ የጠገቡትን መፅሐፍት በማሲኖዳዉ ያጭቅ ገባ።የማርክስ፥ የሌኒን፥ የማኦ መፅሐፍት፥ የቼ ጎቬራ እና የሌሎችም አብዮታዉያን ታሪኮች ነበሩ።ወጣቱ ወታደር ይመገምጋቸዉ ያዘ።ሁሉንም ወዷቸዋል።«የእስኩዌል ዛሞራ ዘመን» በሚል ርዕሥ በ19ኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን ሥመ-ጥር ፌደራሊስት ሥለ ነበሩት ጄኔራል የሚተርከዉን ያክል ግን ልቡን የነካዉ አልነበረም።የድኽነትን ክፋት ካራካስ እያለ አይቶቷል።ሙስናን በቅርብ ተመልክቶታል።ከነዚያ መፅሐፍት ደግሞ መፍትሔዉን አገኘ።ወይም ያገኘ መሠለዉ።
«ግራ የሆንኩት ገና በሃያ-አንድ ወይም በሃያ-ሁለት አመቴ ነዉ» ብለዉ ነበር በኋለኛ ዘመናቸዉ። ድሆችን የመርዳት፥ ሙስናን የማጥፋት፥ የግራ ፍልስፍናቸዉን ገቢር ለማድረግ በመፈንቅለ መንግሥት ሞከሩት።1992 ።ግን ከሸፈባቸዉ።ዘብጥያ ተወረወሩ።ከሁለት ዓመት በሕዋላ ከወሕኒ ሲወጡ አዲስ ፓርቲ መሥርተዉ አዲስ ትግል ጀመሩ።በ1998ቱ ምርጫ አሸነፉ።
በሁለት ሺሕ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ተወገዱ።በሁለተኛዉ ቀን ግን ተመለሰዉ ሥልጣን ያዙ።በሙስና የላሻቁ ባለሥልጣናትን አስወግደዉ፥ በምዕራቦች በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ የሚታገዙ ኩባንያዮችን ገፍታትረዉ ከሐገሪቱ የነዳጅ ዘይት የሚገኘዉን ሐብት የድሆችን ኑሮ ያሻሽሉበት ያዙ።
«አንዳድ የሐብታሞች ቢደሰቱም፥ ሕዝቡ በጣም አዝኗል።ምንያሕል ሰብአዊ ሐዘን እንደሆነ አይገባቸዉም።ግን በጣም አናሳ ናቸዉ።ጠቅላይ አዛዡ ባይኖርም አብዮቱ ይቀጥላል።ምንጌዝም ከኛ ጋር ነዉ።»
አሉ ሰዉዬዉ።ሻቬዝ ለአንጋፋዉ የኩባ መሪ ለፊደል ካስትሮ «ፅንዑ አብዮታዊ ልጅ» ነበሩ።ለሩሲያዉ ፕሬዝዳት ለቭላድሚር ፑቲን ደግሞ «አቻ የማይገኝላቸዉ ጠንካራ፥ እና አርቆ አሳቢ።» የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ግን የሻቬዝ ሞት ከቬኑዙዌላ መንግሥት ጋር ገንቢ ግንኙነት ለመስረት ጥሩ አጋጣሚ ነዉ» ብለዉታል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን «ከልቤ አዝኛለሁ» ሲሉ የብራዚሏ ፕሬዝዳት ዲልማ ሮዉሴፍ ሻቬዝን ታላቅ ደቡብ አሜሪካዊ ብለዋቸዋል።
«ዛሬ ከታላቅ ሐዘን ጋር ታላቅ ደቡብ አሜሪካዊ ሞቱ ማለት አለብኝ።ፕሬዝዳት ኡጎ ሻቬዝ።የብራዚል መንግሥት ከፕሬዝዳት ኡጎ ሻቬዝ ጋር ብዙ ጊዜ አይስማማም።ዛሬ ግን ሁሌም እንደምንለዉ ታላቅ መሪነቱን መቀበል አለበን።የማይተካ ሰዉ፥ ከሁሉም በላይ የብራዚልንና የብራዚላዉያንን ወዳጅ አጣን።»
ኡጎ ሻቬዝ አዲዮስ።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ