1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ እድገትና የምግብ ዋስትና

ረቡዕ፣ ግንቦት 8 2004

የአፍሪቃ አገሮችን ፈጣን እድገት ረሃብና የምግብ እጥረት እንዳያደናቅፈዉ ሲል የተመ የልማት መርሃግብር UNDP ስጋቱን ገለጸ። የድርጅቱ አስተዳደር ኃላፊ ሄለን ክላርክ እንዳመለከቱት ረሃብን ማጥፋት ካልተቻለ በቅርቡ አፍሪቃ ዉስጥ በአንዳንድ

https://p.dw.com/p/14wWJ
ምስል DW

ሐገሮች የታየዉ የኤኮኖሚ እድገት ዘላቂነት ሊኖረዉ አይችልም። የኤኮኖሚ እድገቱም ሆነ እምቅ ጥሬ ሃብት እያላትም አፍሪቃ ከዓለም የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠባት አህጉር መሆኗን UNDP አስታዉቋል። አፍሪቃ እየተደጋገመ በሚጎበኛት ረሃብ ምክንያት የምግብ ዋስትና መታጣቷን የተመድ የልማት መርሃግብር UNDP ትናንት ናይሮቢ ኬንያ ይፋ ባደረገዉ የአፍሪቃ የልማት ዘገባ አመልክቷል። ድርጅቱ በጥናቱ ወደ218 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪቃዉያን በቂ ምግብ እንደማያገኙ፤ 55 ሚሊዮን ህፃናት ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ እንደማይመገቡ፤ ይህ ቁጥርም እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይሄድ ያለዉን ስጋት አሳይቷል።

Burkina Faso Ländliche Entwicklung Kinderarbeit
ምስል DW

UNDP አክሎም አፍሪቃ ዉስጥ የምግብ ዋትናን የግብርናዉን ዘርፍ ምርታማነት በማሻሻል፤ እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ስልቶችን በመቀየስ ማረጋገጥ እንደሚቻልም እምነቱን ገልጿል። እንደUNDP ዘገባ ከሆነም አፍሪቃ ዉስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች አሁን እየታ እንደሆነ የሚነገርለት እድገት በተቃራኒዉ ክፍለ ዓለሚቱ የምትታወቅበትን ተደጋጋሚ ረሃብ፤ ብሎም የምግብ ተመፅዋችነቷን ለመቀየር በሚያስችል መልኩ ሥራ ላይ አልዋለም። ከሰሐራ በስተደቡብ አንዳንድ አገሮች ያስመዘገቡት የኤኮኖሚ እድገት ያለባቸዉን የምግብ ዋስትና ችግር ሊፈታ አለመቻሉም የሚቃረን እዉነታ መሆኑን የድርጅቱ ረዳት ዋና ፀሐፊና የአፍሪቃ ዳይሬክተር ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ ገልጸዋል፤

«ተቃርኖዉ ይህ እድገት አፍሪቃ ዉስጥ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ህዝቦች ያመጣዉ የምግብ ዋስትና የለም። እድገቱ ለአፍሪቃ ህዝቦች እኩልነት አላመጣም። በሌሎች እንደብራዚል ህንድና ቻይና በመሳሰሉት ሐገሮች ሚሊዮኖች ከድህነት ኑሮ መላቀቅ ሲችሉ እዚህ የድህነት ደረጃዉንም ከ51 ወደ48 በመቶ ነዉ ዝቅ ያደረገዉ።»

አፍሪቃ ዉስጥ ሥርዓቶቹ የሀገራቸዉን ሀብት ማዋል ለሚገባቸዉ ነገር ከመጠቀም ይልቅ የስልጣን መዋቅራቸዉን ማጠናከሪያ ማድረጋቸዉ፤ ያም የክፍለ ዓለሚቱን እምቅ ሀብት ለብክነት መዳረጉን ዶክተር ተገኘወርቅ አመልክተዋል። ለራሳቸዉ የቆሙ ያሏቸዉ ልሂቃን በህዝቡና በመሪዎች መካከል ሆነዉ የመንግስትን ገቢ እንደሚቆጣጠሩ የገለፁት ባለሙያ፤ በአንድ ወገን የተያዘዉ የመንግስት ገቢ የሥራ እድል ለመፍጠርም ሆነ ለገጠሩ ኢንዱስትሪ ለማቆም እንዳላስቻለም አስረድተዋል።

Reisanbau in Mali neu
Reisanbau in Mali neuምስል DW

አፍሪቃ በቂ እዉቀትና እምቅ ሀብት አላት ያሉት ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ የጦር መሳሪያን መጠቀምና መግዛት የማይገዳቸዉ አፍሪቃዉያን የተሻሻለ የግብርና ቴክኒዎሎጂዎችን ስለምን ወደየአገሮቻቸዉ አያስገቡም ሲሉም ጠይቀዋል፤

«አፍሪቃዉያን የተራቀቁ የአየር መንገድ ጀቶችን ማብረር ከቻሉ፤ ታንኮችና የረቀቁ ወታደራዊ የጦር መሳሪያዎችንም መቆጣጠር ከቻሉ፤ የተራቀቁ መሳሪዎችን በማምጣት የቴክኒዎሎጂ ሽግግር የማይደረግበት፤ እና በቂ የተሻሻሉ የእርሻ ምርቶችን በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ቁርጠኝነት የማይኖርበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።»

የእሳቸዉን ሃሳብ ያጠናከሩት የUNDP የበላይ ኃላፊ ሄለን ክለርክ በበኩላቸዉ አፍሪቃ ህዝቦቿን ከረሃብ ሊያላቅቅ የሚችል በቂ የእርሻ መሬት እና ተስማሚ አየር አላት ብለዋል፤

«አፍሪቃ ዉስጥ ለእርሻ በቂ መሬት አለ፤ በቂ የዉሃ ክምችት አለ፤ ከዚህም ሌላ ለምግብ የሚሆነዉን ምርት ለማሳደግ የሚያስችል ተስማሚ የአየር ንብረትን አላት።»

Bäuerin in Uganda
ምስል DW

አፍሪቃዉያን መራብ እጣ ፈንታቸዉ እንዳልሆነ ያስገነዘቡት የUNDP የአፍሪቃ ዳይሬክተር ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ፤ መንግስታት ተገቢ መመሪያዎችና ያንን የሚደግፉ ሁኔታዎችን ካመቻቹ ችግሩ በተወሰነ ጊዜ ዉስጥ ሊፈታ የሚችል እንደሆነ አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት አፍሪቃ ዉስጥ ቻድ፤ ማሊ፤ ኒዠር፤ ሞሪታኒያ እና ቡርኪናፋሶ፤ እንዲሁም ሰሜን ሴኔጋልና ሰሜን ናይጀርያ እና ካሜሮን ዉስጥ በጥቅሉ ወደ15 ሚሊዮን ህዝብ ለረሃብ አደጋ መጋለጡ ተገልጿል። ባለፈዉ ዓመት በምስራቅ አፍሪቃ የተከሰተዉ ረሃብ ሶማሊያ፤ ኬንያ፤ ኢትዮጵያ፤ ዑጋንዳና ጅቡቲ ዉስጥ ከሃምሳ እስከ አንድ መቶ ሺህ ሰዎችን ፈጅቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ