የአፍሪቃ አብያተ ክርስቲያንና ግብረሰዶማዊነት
ዓርብ፣ ኅዳር 21 2005
በብዙዎቹ የአፍሪቃ ሃገሮች የግብረ ሰዶማውያን መብት እንዲጠበቅ የሚቀርበው ጥሪ በአብያተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ። የአብያተ ክርስቲያን ተጠሪዎችና ህብረተሰቡ ግብረሰዶማዊነት ከባህላችንና ልምዳችን ውጭ በመሆኑ መቼም ቢሆን አንደግፈውም ይላሉ ። ይህ ጠንካራ አቋምም በፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ተፅእኖ እያደረገ ነው ። በዚህ ረገድ ማላዊ እንደ አንድ ምሳሌ ልትወሰድ ትችላለች ።
« የግብረ ሰዶማውያንን መብት በመቃወም ስብሰባ አድርገናል ። የናይጀሪያ ካቶሊካውያን ማህበረሰብ እንዲሁም የተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ግብረሰዶማዊነት የሚቃወሙ መፈክሮችን አሳይተዋል ። »
ቄስ ራፋኤል አደባዮ የሌጎስ ናይጀሪያው የቅዱስ አግነስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን ናቸው ። በናይጀሪያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ግብረ ሰዶማዊነት በፅኑ ይቃወማሉ ። ቄስ አደባዮ ምክንያቱን ያስረዳሉ ።
« እግዜዘብሔር የሚቃወመውን ቤተክርስቲያን መደገፍ አትችልም ። ፀያፍ ነው »
በናይጀሪያ ክርስትና እስልምናም ሆነ ልምዳዊ እምነቶች የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን እንደሚቃወሙ የናይጀሪያ የፓርላማ አባል የሆኑት ጃጋባ አደምስ ጃጋባ ይናገራሉ ።
« ልምዳዊ እምነቶቻችን ይቃወሙታል ፤ ክርስትና አይቀበለውም ፤ እስልምናም ይቃወመዋል ። በባህላችን ፀያፍ ነው ። ለዚህም ነው እንደ ፓርላማ ባህላችንንና ልምዶቻችንን ለማስጠበቅ ህጉን ያሳለፍነው ። »
ናይጀሪያ ባህልና ልምድዋን ለማስጠበቅ ህግ አውጥታለች ። ናይጀሪያ ውስጥ ግብረ ሰዶማዊ ተጓዳኝነት ወይም ለግብረሰዶማውያን መብቶች ዘመቻ የሚያካሂዱ እስከ 10 አመት የሚደርስ እሥራት ሊጠብቃቸው ይችላል ። ይህ ህግ ሥራ ላይ እንዲውል የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ጉድ ላክ ጆናታን ማፅደቅ አለባቸው ። አብያተ ክርስቲያን ግብረ ሰዶማዊነት መቃወማቸው በ ጀርመን Recklinghausen ለግብረ ሰዶማውያንንና አብያተ ክርስቲያን የጋራ የምክክር ቡድን መሪ Markus Gutfleisch አያስገርምም ።
« የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሁሌም ጣልቃ ትገባለች ፤ ለምሳሌ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ መንግሥት ለግበረሰዶማውያን የበለጠ መብት የሚሰጥ አንድ ረቂቅ ህግ ሲያቀርብ ይቃወማሉ ። »
ጉትፍላይሽ አብያተ ክርስቲያን በማህበራዊ ጉዳዮች የራሷን ሃሳብ ማንፀባረቋ በመሰረቱ ተገቢ ነው ። ሆኖም በርሳቸው አመለካከት በወግ አጥባቂ አመለካከት ሳቢያ ግን የሰው ልጅ መብት መጣስ የለበትም ። ይህ የማሊን መንግሥት አስቸጋሪ ምርጫ ውስጥ ከቶታል ።
አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን የሃገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር የግብረሰዶማውያንን እንቅስቃሴ የሚያግደው ህግ እንደሚነሳ መናገራቸውን ዘግበዋል ። ይህ ጉዳይም በሃገሪቱ ፓርላማ ክርክር እየተካሄደበት ነው ። አስተያየቱ ከማላዊ አብያተ ክርስቲያን ምክር ቤት በኩል አሉታዊ ምላሽ አስከትሏል ። ማላዊ ያሉ አንዳንድ ግብረ ሰዶማውያን ምክር ቤቱ እንደ ሰው እንደማያቆጥራቸውና በነፃነት መንቀሳቀስ ሊፈቀድላቸው አይገባም እንደሚልም ይናገራሉ ። አብያተ ክርስቲያን ስለ ሰብአዊ መብት መናገር እየወደዱ የነርሱን መብት አለመጠበቃቸው ከምድረ ገፅ ይጥፉም ማለታቸውን እአይቀበሉም ። ቄስ አዴባዮ ግን ይሄ ከእምነታችን ጋር የሚሄድ አይደለም ነው የሚሉት ።
«ቤተክርስቲያን ሰብአዊ መብትን ልታከብር ትችላለች ። ሰብአዊ መብት የእግዜአብሔርን ትዕዛዛት ሲጥስ ግን እስከ ወዲያኛው አንደግፈውም »
በማላዊ አብያተ ክርስቲያን ተቃውሞ በኋላ መንግሥት በመጀመሪያው አቋሙ ከመፅናት ወደ ኋላ እያለ ነው ። የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው ከአፍሪቃ የግብረ ሰዶማውያን መብት በህገ መንግሥት ያሰፈረችውና እና የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ የፈቀደችው ደቡብ አፍሪቃ ብቻ ናት ። በተቀሩት ሃገራት በሙሉ ማለት ይቻላል ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በእሥራት ያስቀጣል ። በካሜሩን ከ 6 ወር እስከ 5 አመት በሚደርስ እሥራት እንዲሁም 350 ዩሮ ያስቀጣል ። ናይጀሪያ ና ኡጋንዳ የግብረ ሰዶማዊነት የሚቃወም ህግ ለማውጣት በዝግጅት ላይ ናቸው ። ግብረሰዶማዊነትን የሚቃወም ህግ ከሌላቸው ጥቂት የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ ማሊ ቡርኪናፋሶና አይቮሪ ኮስት ይገኙበታል ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ