1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ኅብረት የኤቦላ አስቸኳይ ስብሰባ

ሰኞ፣ ጳጉሜን 3 2006

በምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት የኤቦላ ተኅዋሲ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ በመምጣቱ የአፍሪቃ ኅብረት ዛሬ አዲስ አበባ ላይ የአስቸኳይ ስብሰባ ማካሄዱ ታዉቋል።

https://p.dw.com/p/1D8xR
Afrika - Beginn des Gipfels der Afrikanische Union
ምስል Getty Images

የአፍሪቃ ኅብረት በምዕራብ አፍሪቃ በተከሰተው የኤቦላ ወረርሽኝ አንፃር በአህጉር አቀፍ ደረጃ አንድ የትግል ስልት ለማውጣት ስለሚቻልበት ጉዳይ ዛሬ በጠራው አስቸኳይ ጉባዔ መክሮአል። በዚሁ እስከዛሬ ከ2,000 የሚበልጥ ሰው በገደለው ወረርሽኝ እና ከ4,000 ሰው በላይ ባሳመመው ተኀዋሲ አንፃር የሚደረገው ትግል ታማሚዎቹን፣ ማኅበረሰብን እና ሀገራትን በማያገል ሁኔታ መካሄድ እንደሚኖርበት የአፍሪቃ ኅብረት የሰላም እና ፀጥታ ፕሬዚደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ስብሰባውን በከፈቱበት ጊዜ ባሰሙት ንግግር አስታውቀዋል። ዙማ አክለው እንዳስገነዘቡትም፣ በወረርሽኙ አንፃር አንድ አጠቃላይ አፍሪቃዊ ምላሽ ማፈላለግ የግድ ይሆናል። ኅብረቱ የጤና መኮንኖችን ለመላክ ቃል ገብቶዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ ሰዎችን ከኤቦላ መከላከል ያስችላል በሚል አንድ ተስፋ የተጣለበት አዲስ ክትባት ሳይመረት እንዳልቀረ በዛሬው ዕለት ተገልጾዋል። የተባለው ክትባት የተሰጣቸው ዝንጀሮዎች ከበሽታው መፈወሳቸው የተሰማ ሲሆን፣ ክትባቱ ከጥቂት ቀናት በኋላ ለሰዎች እንደሚሰጥ ተነግሮዋል።

ሌላ በኩል የዩኤስ አሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኤቦላ ተኅዋሲ ተሰራጭቶ በዓለም ትልቅ የጤና ቀዉስ እንዳያስከትል፤ ዩኤስ አሜሪካ በምዕራብ አፍሪቃ ተኅዋሲዉን ለመግታት የበለጠ መስራት ይኖርባታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የጀርመን መንግሥት በበኩሉ የጤና ባለሞያዎችን ወደ አፍሪቃ እንደሚልክ አስታዉቋል። የኤቦላ ተኅዋሲ ስርጭትን ለመግታት የአፍሪቃዉ ኅብረት አዲስ አበባ ላይ ዛሬ በጀመረዉ ስብሰባ ላይ የተገኘዉ የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ጌታቸዉ ተድላ ኃይለጊዮርጊስ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።

ጌታቸዉ ተድላ ኃይለጊዮርጊስ

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ