1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ

ሰኞ፣ ሰኔ 28 1996

የአፍሪቃ ሀገሮች መሪዎች በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ሦስተኛውን ዓመታዊ የአፍሪቃ ኅብረት ጉባዔ ያካሂዳሉ። እአአ በ 2002 ዓም የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን የተካው የአፍሪቃ ኅብረት አባል ሀገሮች መሪዎች የአህጉሩን ችግሮችና በርካታ ውዝግቦች በማስወገዱና ሰላም በማስገኘቱ፡ እንዲሁም፡ ልማት በማነቃቃቱ ጥረት ላይ መሪ ሚና ለመያዝ ቆርጠው ተነሥተዋል።

https://p.dw.com/p/E0kv
የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ
የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባምስል AP

በዚሁ የአፍሪቃውያኑ መሪዎች ጥረት መደዳም፡ ኅብረቱ ባለፉት የፀደይ ወራት አንድ የሰላምና የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አቋቁሞዋል። ምክር ቤቱ ወደፊት በአንድ ሀገር ውስት የጦር ወንጀል፡ የጎሣ ጭፍጨፋ እና በስብዕና አንፃር ወንጀል በሚፈፀምበት ጊዜ ጣልቃ ገብቶ ርምጃ ሊወስድና የአፍሪቃ ኅብረት ዓቢይ ጉባዔም ውዝግብ ወደተከሰተበት አባል ሀገር የጦር ኃይል እንዲልክ ሀሳብ ሊያቀርብ ይችላል። በዚሁ ሚናው መሠረትም ታዛቢዎች በወቅቱ ከዳርፉር እስከ ኮንጎ ድረስ ተሠማርተዋል፤ እአአ እስከ 2010 ዓም ደግሞ አሥራ አምስት ሺህ ወታደሮች የሚኖሩትና በሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮዎች የሚሠማራ አንድ አጥቂ ኃይል ይቋቋማል። ይህ የኅብረቱ ዕቅድ የሚሳካበት ድርጊት በተለይ በሁለት ጉዳዮች ላይ፡ ማለትም በሥልጠናው እና የገንዘብ አቅርቦቱ በሚሟላበት ጥያቄ ላይ ጥገኛ ይሆናል። አፍሪቃውያን ወታደሮች በሥርዓት አልባነት፡ ሕፃናትን በውትድርና በመልመል፡ የዝርፊያ እና የክብረ ንፅሕና መድፈር ተግባር በሚያካሂዱበት ሰበብ መልካም ስም የላቸውም የሚሉት ብሪታንያዊው አሠልጣኝ ኮሎኔል ሮብ አንድሩ የዕቅዱን መሳካት አብዝተው መጠራጠራቸውን አስታውቀዋል። አፍሪቃውያን ጦር ኃይላት መፍትሔ በማስገኘት ፈንታ ችግር ይፈጥራሉ የተባለበት አነጋገር ግን ሙሉ ለሙሉ ትክክል አይደለም፤ ምክንያቱም ውዝግብ በሚካሄድባቸው አፍሪቃውያን አካባቢዎች ከአውሮጳና ከአሜሪካ የሄዱ ጠንካሮቹ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ እሪቃውያኑ አቻዎቻቸውም ተሠማርተዋልና። ከሀያ ስድስት አፍሪቃውያት ሀገሮች የተውጣጡ አሥራ ስምንት ሺህ ወታደሮች የተ መ ድ በወቅቱ በዓለም በሚያካሂዳቸው የሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮዎች ተሠማርተዋል። ይህም በጠቅላላ በዓለም ከተሠማሩት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መካከል አንድ ሦስተኛው መሆኑ ነው። ናይጀሪያ ወይም ጋናን የመሳሰሉ ሀገሮች ለተ መ ድ ሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮዎች የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን፡ ኔቶ ሀገሮች ካሠማሩዋቸው ወታደሮች የሚበልጡ ወታደሮችን አሰልፈዋል። በሲየራ ልዮን በኬንያ እዝ ሥር የተሠማራው ጠንካራ የተ መ ድ ሰላም አስከባሪ ጓድ በሀገሪቱ መረጋጋትና ፀጥታ አረጋግጦዋል። ናይጀሪያ፡ ጋና፡ ኬንያ፡ ግብፅና ደቡብ አፍሪቃ ወደፊት ይቋቋማል ለሚባለው የአፍሪቃውያኑ ሰላም አስከባሪ ጓድ ብዙውን ወታደር ያበረክታሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
የአፍሪቃ ኅብረት ለሰላም ማስከበሪያው ተልዕኮው ወደ አምስት ሚልዮን ዩሮ በጀት ሲኖረው፡ ከዚሁ መካከል ሁለት ሦስተኛውን የሚያቀርቡት የአውሮጳ ኅብረትና ዩኤስ አሜሪካ ናቸው። ለማነፃፀር ያህል፡ በአፍሪቃ ለሚታዩት ስድስቱ የተ መ ድ የሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮዎች ባያመቱ ሁለት ሚልያርድ ዩሮ ይወጣሉ። የበጀቱ ጉዳይ የደቀነው አጣብቂኝ ሁኔታ ለምሳሌ የርስበርሱ ጦርነት ባዳቀቃት ቡሩንዲ ይታያል። በዚችው ሀገር ውስጥ የመጀመሪያው የአፍሪቃውያን ሰላም አስከባሪ ጓድ፡ ማለትም፡ ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ከኢትዮጵያ፡ ከሞዛምቢክ እና ከደቡብ አፍሪቃ የተውጣጡ ወታደሮች ያሠለፈ ኃይል ተሠማርቶ ተቀናቃኞቹን ፓርቲዎች ለመለያየት በቅቶዋል። ይሁንና፡ ካለፈው አንድ ወር ወዲህ አፍሪቃውያኑ ገንዘብ ስለጎደላቸው በቡሩንዲ በወቅቱ የሰላም አስከባሪውን ጓድ እዝ የ ተ መ ድ ተረክቦታል።