የአፍሪቃ ትኩረት - የመገናኛ ብዙኃን ሽልማት
ዶቼቬለ ለአፍሪቃውያን ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሚበረከተውን ህዝባዊ ሽልማትም በዚህ ዓመት ለአፍሪቃውያን የፎቶግራፍ ጋዜጠኞች ሰጥቷል ። በአፍሪቃ የሰብዓዊ መብት ይዞታን ከሚያንጸባርቁ የአፍሪቃዊ ጋዜጠኞች ምርጥ ፎቶዎች መካከል ጥቂቱን እናሳይዎ ።
ትምህርት የማግኘት መብት
የአፍሪቃውያን የሰብዓዊ መብት መከበር ህዝባዊ ሽልማት » ካገኙት ፎቶግራፎች አንዱ የማኮኮ ህፃናት ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ያሳያል ። በሌጎስ የውሃ ዳርቻ በርብራብ እንጨት ላይ ነው ሰፈሩ የተገነባው ። ትምህርት ድህነትን ለመዋጋት እንድ ጠንካራ መሳሪያ ተድርጎ ይታያል ። ድህነት የተስፋፋበት የማኮኮ ሰፈር ልጆች ግን ትምህርት የማግኘት እድል የላቸውም ። እነዚህ እድሉን ያገኙት ጥቂቶች ናቸው ።
ጥቃት በፖሊስ
ሌጎስ ውስጥ አንድ የሞተርሳይክል ታክሲ ነጂ በአደባባይ ይቅርታ ይጠይቃል ። እንዳይታሰር በማመፅ አስቀድሞ ርቃኑን ነበር ። እጎአ 2012 ዓም የሌጎስ የከተማ አስተዳድር የሞተርሳይክል ታክሲዎች አውራ ጎዳና ላይ እንዳያሽከረክሩ ከልክሏል ። ።ይህንንም ትዕዛዝ ፖሊስ በኃይል ርምጃ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥር ይታያል ።
የመዘገብ መብት
የሶማሊያ ጋዜጠኞች ባልደረቦቻቸው መታሰራቸውን እና መገደላቸውን በመቃወም ሰልፍ ወጥተዋል። የዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ዋና ምክንያት የአንድ ጋዜጠኛ መታሰር ነበር ። ጋዜጠኛው የታሰረው የመንግስት ወታደሮች ደፈሩኝ ላለች አንዲት ሴት ቃለ መጠይቅ በማድረጉ ነበር ። በ2012 ዓ ም ብቻ በሶማሊያ 18 ጋዜጠኞች ተገድለዋል ። በዚህ የተነሳም ሶማሊያ ከዓለም ለጋዜጠኞች አደገኛ ከሚባሉት አገሮች አንዷ ናት።
የወሲብ ጥቃት
ኒኪዌ ማሳንጎ በ87 አመታቸው ነበር ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው ። በማያውቁት ሰው በተኙበት ለሊት መደፈራቸውን ይናገራሉ ። በጭስ አደንዝዞኝ መሆን አለበት ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶኝ ነበር።» « ማንነቱን እንዳላውቅ አይንሽን ጨፍኚ ይል ነበር» ሲሉ ይገልፃሉ ማሳንጎ ።
ናፍቆት
እኚህ ደቡብ አፍሪቃዊ ከ 20 ዓመታት በላይ ወህኒ ቤት ቆይተዋል ። ፊታቸው ላይ ያለው እያንዳንዱ ንቅሳት የአንድ ቡድን አባል መሆናቸውን እና ያላቸውን ደረጃ የሚያሳይ ነው። ማንም ሰው ምንም ዓይነት የኑሮ ደረጃ ይኑረው ውበት እንዳለው ጉርድ ፎቶዋቸው ያመላክታል ።
ጤናማ ልጅ
ዛይቱኒ በደስታ ጨቅላዋን ታቅፋለች ። ልጁም እናቱም ጤነኛ ናቸው። ዛይቱኒ ሆስፒታል እስክታገኝ ከምትኖርበት ቤት ጥቂት ሜትር ብቻ ነበር መሄድ የነበረባት ። ይህ ትንሽ ሆስፒታል ዲፍ በሚባል መንደር በኬንያ እና ሶማሊያ ድንበር ላይ ይገኛል ። ይህ በከተማው ያለ ብቸኛው የማዋለጃ ጣቢያ ነው።
የህዝብ የቁጣ እርምጃ
አንድ ሰውዬ በደቡብ አፍሪቃ ኬፕታውን በአደባባይ መንገድ ላይ በገመድ ታስሮ ይጎተታል ። ከዛ በፊት የተናደዱ መንገደኞች ደብድበውታል ። የተደበደበውም ተንቀሳቃሽ ስልክ ሰርቀሃል ተብሎ ነው ። ፖሊስ በመጨረሻ ሰውየውን ሆስፒታል ወስዶታል ። ማንም ሰው ግን በቁጥጥር ስር አልዋለም ። በአግባቡ ጥፋተኛን ለፍርድ ማቅረብ እዚህ አልተለመደም።
ማፈናቀል
እኚህ እናት ከ 7 ልጆቻቸው ጋ መንገድ ላይ ያለቅሳሉ ። እሳቸው እና ቤተሰባቸው ከሚኖሩበት የቻድ መዲና ንጃሜና በጉልበት ተባረዋል ። መኖሪያ ቤታቸው የሚገኝበት ቦታ ላይ ዘመናዊ ሆቴል ይሰራል ተብሏል ። ለዚህ ሆቴል ሥራ ሲባል ከ670 ሰዎች በላይ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል ። እኚህን ወይዘሮም ጨምሮ አንዳቸውም ካሳ አልተሰጣቸውም።
የድብደባ ቅጣት
የኬንያ ሰላም አስከባሪዎች ቦኒፌስ ዋንጊ የተባለውን የመብት ተሟጋች ተሸክመው ይወስዳሉ ። ይህ የሆነውም የሰራተኛ ማህበር አባልን « ከሃዲ» ሲል በመሳደቡ ነው ። ዋንጊ በዚህ ሰበብ በፖሊስ ድብደባና መታሰር ገጥሞታል ። በደሉ ሀሳቡን በነፃ የመግለፅ ሰብዓዊ መብቱን ተጠቅሞ በመናገሩ ነው ።
የውሃ ችግር
በሰሜን ጋና የጃቶክሮም መንደር ነዋሪዎች ከተገደበ የውሃ ማጠራቀሚያ ውሃ ለማምጣት በኪሎ ሜትር የሚለካ ርቀት መጓዝ አለባቸው። እርሻቸው አጠገብ የሚገኘው ወንዝ ደርቋል ። ከብቶችም የተጠራቀመውን ውሃን ስለሚጠጡ ለመጠጥ አይሆንም። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጋናውያን እስካሁን ንፁህ የመጠጥ ውሃ አያገኙም።
በቂ ያልሆነ የአደጋ መከላከያ
ኬፕታውን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ አንድ ወጣት ከአንዱ አነስተኛ መፀዳጃ ቤት ወደ ሌላው ይዘላል ። በኬፕታውን ዙሪያ በሚገኙ ጎስቋላ ሰፈሮች የሚኖሩ ሰዎች መፀዳጃ ክፍል ማግኘት ጭራሽ የማይታሰብ ነው ። የከተማው መፀዳጃ ቤቶች በሙሉ ፣ ከመጠን በላይ የሞሉና የቆሸሹ ናቸው ። ሰዎች ባለው ከፍተኛ ወንጀል ሳቢያ ከቤታቸው ወጥተው መፀዳጃ ቤት ከመሄድ ይልቅ ቤታቸው ውስጥ በፖፖ መፀዳዳቱን ይመርጣሉ።