የአፍሪቃ ሠላምና ሠላም አስከባሪ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2005
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እንደዛቱት ጦራቸዉን ከሶማሊያ ካስወጡ ሶማሊያ ዉስጥ የፈነጠቀዉ ሠላም ባይዳፈን-እንደሚጋረድ የፖለቲካ አዋቂዎች፣በሚያስጠነቅቁበት መሐል በድብቅ የሞቃዲሾ ኤምባሲያቸዉን የከፈቱት የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በሶማሊያ አስተማማኝነት ሠላም የሚሰፍንበት ጊዜ መቃረቡን መሠከሩ።የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርን መግለጫን የዓለም መገናኛ ዘዴዎች ሲቀባበሉት፤ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የማሊን ሠላም የሚያስከበር ሠራዊት ለማዝመት ወሰነ።ሐሙስ።በማግሥቱ፣ የአፍሪቃ እና የአዉሮጳ ሕብረቶች መሪዎች አፍሪቃ ዉስጥ ሠላም ለማስፈን ያደረጉት ጥረት ጥሩ ዉጤት ማግኘቱን አወደሱ።አዲስ አበባ፥ ሞቃዲሾ እና ኒዮርክ የተባለና የተወሰነዉን አስታከን የአፍሪቃን እዉነት ከሰላም ብያኔ እንዴትነት ጋር አጣቅሰን ባጭሩ እንቃኛለን።አብራችሁኝ ቆዩ።
የኢትዮጵያ መሪዎች የሶማሊያ ተቀናቃኝ ሐይላትን ለመሸምገል ከመጣር፣ መልፋት፣ መባተላቸዉ እኩል ሁለቱን ሱዳኖች ለማስታረቅ መዉጣት መዉረዳቸዉ እርግጥ ነዉ።ሶማሊያ ዉስጥ የወጣት ወታደሮቻቸዉን አካል፣ ደም፣ ሕይወትን ከመሰዋታቸዉ እኩል ከአብዬ እስከ ላይቤሪያ ሠላም አስከባሪ ወታደር ማዝመታቸዉ ሐቅ ነዉ።
የአዲስ አበባ መሪዎች በተደጋጋሚ እንዳሉት ሶማሊ እና ሥለ ሶማሊያ፣ ሁለቱ ሱዳኖች እና ሥለ ሁለቱ ሱዳኖች ያሉ ያደረጉትን ሁሉ የማለት ማድረጋቸዉ ምክንያት የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር፣ የጎረቤት ሐገራት ሕዝቦችን ለመርዳት ሊሆን ይችላል።
ወይም ተቃዋሚዎቻቸዉ እንደሚሉት በተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ በነፃ ጋዜጠኞች፣ በመብት ተሟጋቾች፣ በጥቅሉም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚፈፅሙትን አፈና እና ረገጣ ለመሸፈን ሊሆን ይችላል።ወይም ደግሞ ገለልተኛ ተንታኞች እንደሚሉት የአስመራ ጠላቶቻቸዉን በተዘዋዋሪ ጦርነት፣ ዲፕሎማሲ ለመምታት፣ የአፍሪቃ ቀንድ ልዕለ ሐይልነታቸዉን ለማስመስከር፣ አካባቢዉን ከዓረቦች በተለይም ከግብፆች ተፅዕኖ ለማላቀቅ ሊሆንም ይችላል።ഊ
ወይም ሌላ።አንድ ነገር ግን ሐቅ ነዉ።ያደረጉትን ሁሉ በማድረጋቸዉ የምዕራብ መንግሥታትን ሁለንተናዊ ድጋፍ ሸምተዉበታል።ዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ኬንያ ጦራቸዉን ካዘመቱ ወዲሕ ግን አዲስ አበባና አዲስ አበባ ላይ ብቻ አተኩሮ የነበረዉ የዋሽግተን-ብራስልስ መሪዎች ቀልብ ወደ ካምፓላና ናይሮቢ መሳቡ አልቀረም።
ናይሮቢዎች ጦራቸዉን ሶማሊያ ባዘመቱ ማግሥት አዲስ አበቦች ጦራቸዉን ዳግም ማዝመታቸዉ በምዕራባዉያኑ ዘንድ እንደ ቀድሞዉ ብቸኛ ተፈላጊ ባያደርጋቸዉ እንኳ ከናይሮቢና ከካምፓላዎች አለማነሳቸዉን አስመስክሮላቸዋል።
ይሁንና አክራሪ፣ አሸባሪዉን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብን ሞቃዲሾና ኪስማዩን ከመሳሰሉት ትላልቅ ሥልታዊ ከተሞችን የማስወጣቱን ዉለታ ከአዲስ አበባ ይልቅ ከአዲስ አበባ መሪዎች ብዙ ዘግይተዉ ጦር ያዘመቱት የካምፓላና የናይሮቢ መሪዎች መዉሰዳቸዉ አዲስ አበቦች ተፈላጊነታቸዉን ለማሳየት ሌላ እርምጃ እንዲያሰላስሉ ሳያስገድዳቸዉ አልቀረም።ጦራቸዉ ከሁዱር ማስወጣታቸዉ በግልፅ ከታዩት እርምጃዎች አንዱ ነዉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ሽትራስ ቡርግ፣ ብራስልስና ፓሪስን በጎበኙ በሁለተኛዉ ሳምንት ምክር ቤት አባላት ፊት እንደዛቱት ሶማሊያ የሠፈረዉን ጦር ማሳወጣታቸዉ ብዙ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት በብዙ ምክንያት አጠራጣሪ ነዉ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ያሉትን ማለታቸዉ ግን ከአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች ጋር ባደረጉት ዉይይት የሚፈልጉትን አለማግኘታቸዉን ጠቋሚ፣ ወይም ተፈላጊነታቸዉን ለማሳየት ሌላ የተጠቀሙበት ሌላ ዘዴን አመልካች ነዉ።የኢትዮጵያ መሪዎች ሙከራ ከሽፎ፥ ወይም ወጪዉ አስገድዷቸዉ ጦራቸዉን ካስወጡ ግን በብራስልስ፥ ዋሽንግተኞች እንደታቀፉ ለመቆየት የሚቀራቸዉ ትልቅ ካርድ አንድ ብቻ ነዉ።ሱዳን።እንደዲፕሎማሲዉ ወግ ኢትዮጵያ ተባባሪ ወዳጅ ለሚባሉት ግን ደግሞ ተፈላጊነትን ለማትረፍ ኢትዮጵያን ለሚሻሙት ኬንያና ዩጋንዳን ለመሳሰሉት ሐገራት ረጨማሪ ሸከም ነዉ-የሚሆነዉ።ከሁሉም በላይ የምትከስረዉ ግን ለሃያ-ዘመናት ሠላም የማታዉቀዉ ለሶማሊያ ናት።
የፀጥታ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ አንድሩስ አሳሞሐ።የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ በድብቅ ሶማሊያ ገብተዉ፥ በሞቃዲሾ የሐገራቸዉን ኤምባሲ የከፈቱት፥ ኢትዮጵያ ጦሯን ለማስወጣት የመዛቷን ሰበብ ምክንያትን፥ ዛቻዉ እዉን ከሆነ የሚያስከትለዉን መጥፎ ዉጤት እነ አሳሞሐ፥በሚተነትኑበት መሐል ነዉ።
ሔግ ሥለ ሶማሊያ የወደፊት ጉዞ የሚመክረዉን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለንደን ላይ ከማስተናገዳቸዉ ካንድ ሳምንት በፊት ለሃያ-ሁለት ዓመታት ተዘግቶ የነበረዉን የሞቃዲሾ ኤምባሲያቸዉን የከፈቱት መንግሥታቸዉና ተሻራኪዎቹ ለሶማሊያ ሠላም ተቆርቋሪ መስለዉ ለመታየት፥ ወይም ተቆርቋሪ መሆናቸዉን ከልብ ለማሳየት ሊሆን ይችላል።
ወይም ደግሞ ብዙዎች እንደሚያምኑት ከምዕራቡ ዓለም ጋር የምትወዛገበዉ ኢራን፥ በተዘዋዋሪ መንገድ የምትሻኮተዉ ቱርክ ሞቃዲሾ ዉስጥ ኤምባሲ በመክፈታቸዉ አዉሮጳ አሜሪካኖች ከሶማሊያ የሚፈልጉትን ጥቅም ላለመነጠቅ አልመዉ ሊሆን ይችላል።አላማ ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኤምባሲያቸዉን ሲከፍቱ ሥለ ሶማሊያ ሠላም ያሉት ግን የፖለቲካ ተንታኞቹ ካሉና ከሚሉት፥ ከሶማሊያም ተጨባጭ እዉነት የራቀ ነዉ።
«የቀድሞዉ ኤምባሲያችን ከተዘጋና ባንዲራዉ ከወረደ ከሃያ-ሁለት ዓመታት በሕዋላ ኤምባሲያችንን ሥንከፍት የመጀመሪያዉ ምዕራባዊ ሐገራት ነን።ይሕ እርምጃ ሶማሊያ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እየታገዘች ችግሮቿን ማስወገድ እንደምትችል ለመተማመናችን አብነት ነዉ።ገቢራዊ ትብብራችንንም ያሳያል።»
ኤምባሲዉ ባንዲራ ከሚዉለበለብበት በስተቀር ዲፕሎማቶች የሉበት።ሥራ የሚጀምረዉ ሐምሌ ነዉ።ሐምሌም ሥራ ሲጀምር በደርሶ መልስ የሚሠራ እንጂ ሞቃዲሾ ዉስጥ በቋሚነት የሚሠራ አምባሳደር ወይም ዲፕሎማት አይመደብም።ሔግ በብረት ሰንዱቅ (ኮንተይነር) የተሠራ ባዶ ቤት ቁልፍ መክፈታቸዉ እንኳ የተነገረዉ ሞቃዲሾን ለቀዉ ከወጡ በኋላ ነዉ።
ይችን ሶማሌ ነዉ፥ የቀድሞዋ ሶማሊ ላንድ ቅኝ ገዢ፥ የአዉሮጳዋ ትልቅ ሐገር ትልቅ ዲፕሎማት ችግሯን ለማስወገድ እንደምትችል የሚተማመኑባት።የሔግ ድርጊት-ከቃላቸዉ፥ ቃላቸዉ ከሶማሊያ እዉነት መቃረኑ ምሥራቅ አፍሪቃ ላይ ሲያነጋግር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የማሊን ሠላም የሚጠብቅ ሠራዊት እንዲሠፍር ወሰነ።
ዉሳኔዉ ሠሜናዊ ማሊን ይቆጣጠሩ የነበሩትን የሙስሊም እና የቱአሬግ አማፂያንን እስካሁን ከሚወጋዉ የፈረንሳይ ጦር አባላት የተወሰነዉን፥ የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ኤኮዋስ) አባል ሐገራትን፥ እና የቻድ ወታደሮችን ሰማያዊ መለዮ ከማልበስ፥ የዕዝ መዋቅሩን ና ወጪን ከመለወጥ ባለፍ አዲስ ብዙም አዲስ ጦር አይዘምትበትም።ተልዕኮዉ ግን እንደተናጋሪ፥ ተመልካቹ ለየቅል አንዳዴም ግራ አጋቢ ነዉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ሐላፊ ሔርቨ ላድሶዉ እንዳሉት ተልዕኮዉ ሠላም ማስከበር ብቻ ነዉ።
«የሠላም አስከባሪዉ ሐይል ተልዕኮ ፍፁም ግልፅ ነዉ።ፀረ-ሽብር ተልዕኮ አይደለም።የማረጋጋት ተልዕኮ እንጂ።በተልዕኮዉ የመጀሪያ ምዕራፍ የመጓጓዢያ ተሽከርካሪዎች፥ ድንኳኖች፥ የሐይል ማመንጫ (ጄኔሬተሮች) እና ሌሎች ለሲቢል አገልግሎት የሚዉሉ መሳሪያዎች ወደ ማሊ እንልካለን።»
የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ባሳለፈዉ ዉሳኔዉ እንዳስታወቀዉ ግን የሚዘምተዉ ወይም የዘመተዉ ሠራዊት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከፈረንሳይ ወታደሮች ጋር ሆኖ የማሊ አማፂያንን ይወጋል።የሠራዊቱ ተልዕኮ ሠላም ማስከብር ከሆነ ማሊ ዉስጥ የሚከበር ሠላም አለ ማለት ነዉ።አማፂያኑን የሚወጋ ከሆነ ደግሞ ሠላም የለም ማለት ነዉ።
የማሊዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቲመን ኮዉሊባሊ እንደሚሉት ደግሞ የሠራዊቱ ተልዕኮ ከተባለዉና ከሚባለዉ ሁሉ የላቀ ፈርጀ ብዙ ነዉ።
«ይሕ የማረጋጋቱ ሥራ አንድ ገፅታ ነዉ።ዋና አላማዎቹም የሠላማዊዉን ሕዝብ ደሕንነት መጠበቅ፥ የሰሜናዊ ማሊን አስተዳደር ዳግም ማደራጀት፥ አስቸኳይ ሠብአዊ ድጋፎችን ማድረግ፥ ምርጫን ማደራጀት፥ ሥደተኞችን ወደቀያቸዉ እንዲመለሱ ማድረግ እና ሰማናዊ ማሊ ዉስጥ የዕለት ከዕለት ሠላማዊ ኑሮን ማስፈን ናቸዉ።»
ተልዕኮዉ ሠላም ማስከበር፥ ዉጊያ ይሁን እርዳታ ማቀበል MINUSMA በሚል ምሕፃረ-ቃል ይጠራል።አስራ-ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ወታደሮች እና አንድ ሺሕ አራት መቶ ፖሊሶችን ያስተናብራል።እስካሁን አፍሪቃ መራሽ ዓለም አቀፍ የማሊ ደጋፊ ተልዕኮ (AFISMA በምሕፃሩ) የሚባለዉን የአፍሪቃ ሕብረት ተልዕኮን ከመጪዉ ሐምሌ ጀምሮ ይተካል።
የማሊ ጦር ሐይል መኮንኖች የሐገሪቱን መሪ አስወግደዉ ሥልጣን በመያዛቸዉ ምክንያት የተፈጠረዉን ፖለቲካዊ ቀዉስ ለማስወገድ ቀዳሚዉ የአፍሪቃ ሕብረት ነበር።የማሊ አክራሪና የቱዓሬግ አማፂያን ወደ ርዕሠ-ከተማ ባማኮ መገስገሳቸዉን ለማስቆም ቀድመዉ የተንቀሳቀሱት ጦር ያዘመቱትም አፍሪቃዉያን ናቸዉ።
አፍሪቃዉያን የራሳቸዉን ችግር እራሳቸዉ መፍታት አለባቸዉ በማለት ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ የነበሩት ምዕራባዉያን ሐገራት የወትሮ አቋማቸዉን ሽረዉ የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ዘላ ገባች።ተሻራኪዎችዋም ሙሉ ድጋፍ ሰጧት።የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳት ወይዘሮ ድላሚኒ ዙማ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ፈረንሳይ ያረቀቀችዉን የዉሳኔ ሐሳብ ሲያፀድቅም የአፍሪቃዉያን የእስካሁንና የወደፊት አስተዋፅኦ ከቁብ አልቆጠረዉም።
«ዉሳኔዉን እንቀበለዋለን ልበል።ግን በሒደቱ ሙሉ በሙሉ ተሳትፈን ቢሆን ኖሮ እኛ በተለየ መንገድ የምንመለከታቸዉ ጉዳዮች ይኖሩ ነበር።ምክንያቱም የዉሳኔዉ አብዛኛ ክፍል የአፍሪቃ ሕብረትን ሐሳቦችና እርምጃዎችን አድበስብሶ ሁሉንም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይሰጣል።በመሠረቱ ግን የማሊ ሁኔታ የጋራ ተልዕኮ ነዉ።እንዲያዉም በአንዳድ መስኮች የተወሰዱትን እርምጃዎች የመራዉ የአፍሪቃ ሕብረት ነዉ።»
የሞሮኮ ማዕከላዊ መንግሥት እና ፖሊሳሪዮ የተሰኘዉ የምዕራብ ሳሕራዊ ግዛት ነፃአዉጪ ድርጅት በ1991 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ባደረጉት የሠላም ሥምምነት መሠረት የአወዛጋቢዋ ግዛት ፖለቲካዊ አስተዳደር በግዛቲቱ ሕዝብ ድምፅ መወሰን ነበረበት።ሁለቱን ወገኖች የሸመገለዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥምምነቱን ገቢራዊነትና ሕዝበ-ዉሳኔዉን የሚከታተሉ ከሁለት መቶ ሐምሳ በላይ ዓለም አቀፍ ወታደሮችን አስፍሯል።ሠራዊቱ አሁንም እዚያዉ ነዉ። ሕዝበ-ዉሳኔዉ ግን አልተደረገም።ሃያ-ሁለት ዓመቱ።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አረጋጊ ተልዕኮ (MONUC) የተሰየኘዉ ከአስራ-ስምንት ሺሕ በላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ኮንጎ ከሠፈረ ዘንድሮ አስራ-ሰወስት ዓመቱ።ኮንጎ ዛሬም ሠላም የለም።ዳርፉር ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ሠፍሯል።ሠላም አለ ማለት ግን ያስዋሻል። የአፍሪቃ ሕብረት ሶማሊያ ያሠፈረዉ ሠራዊት ተልዕኮ በርግጥ አሸባብን መዉጋት እንጂ ሠላም ማስከበር ነዉ ማለት ሐሰት ነዉ።አሸባብ ግን ዛሬም ሞቃዲሾን ያሸብራል።
የቀድሞዎቹ የኮትዲቯር አማፂያንና የሐገሪቱ መንግሥት ያደረጉትን የሠላም ዉል ለማስከበር የዘመተዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ከፈረንሳይ ጦር ጋር ተባባሮ የቀድሞዉን የሐገሪቱን ፕሬዝዳት ሎራ ባግቦን ታማኞችን በመዉጋትና ፕሬዝዳንቱን በመማረክ እዉነተኛ ተልዕኮዉን አስመስክሯል።
ተልዕኮዉ በትክክል ሠላም ማስከበር፥ የማይፈለግ ሐይልን መዉጋት፥ ወይም የላኪዎችን ጥቅም ማስከበር ማሊን ጨምሮ ባሁኑ ወቅት በዘጠኝ በአፍሪቃ ሐገራት የዉጪ ሠራዊት ሠፍሯል።በየዓመቱ በትንሽ ግምት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ይወጣል።ታዲያ አፍሪቃ ነፃ እና ሠላምስ ናት? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሠ