1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ኪስማዮ ገባ

ዓርብ፣ መስከረም 18 2005

ኬንያ መራሹ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ሥልታዊቷን የወደብ ከተማ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በምድር፥ ባየርና በባሕር ሲያጠቃ ነበር። ዉጊያዉ ዛሬም ከተማይቱ ዉስጥ አይሎ ዉሏል።

https://p.dw.com/p/16HI0
In this photo taken Monday, April 30, 2012 and released by the African Union-United Nations Information Support Team Tuesday, May 1, 2012, Ugandan soldiers of 341 Battalion serving with the African Union Mission in Somalia (AMISOM) man the frontline near the main road on the northern edge of Maslah Town, the northern city limit of the Somali capital Mogadishu, in Somalia. (Foto:AU-UN IST, Stuart Price/AP/dapd).
ምስል AP

ሶማሊያ የሠፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረት (አሚሶም) ጦር የአሸባብን የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታ ኪስማዮን በከፊል መቆጣጠሩን አስታወቀ። ኬንያ መራሹ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ሥልታዊቷን የወደብ ከተማ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በምድር፥ ባየርና በባሕር ሲያጠቃ ነበር። ዉጊያዉ ዛሬም ከተማይቱ ዉስጥ አይሎ ዉሏል። የኬንያ ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ሳይረስ ኦጉና ዛሬ ጠዋት ጦራቸዉ ከተማይቱን ከአሸባብ አስለቅቆ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል ብለዉ ነበር። ዛሬዉኑ ቀትር ላይ ግን ጦሩ የያዘዉ የከተማይቱን ገሚስ ብቻ መሆኑን አስታዉቀዋል።

«ከተማይቱ ዉስጥ ወታደሮች አሉን።ይሕ ለአሸባብ ከፍተኛ ዉድቀት ነዉ።ምክንያቱም ጥቃት የተከፈተባቸዉ ድንገት ነዉ።አካባቢን በተመለከተ ከተማይቱ ትልቅ ናት።በዚሕም ምክንያቱ ሁሉንም የከተማይቱን ክፍል አልያዝንም።ይሁንና አሸባብ ይቆጣጠራቸዉ የነበሩ ሥልታዊ አካባቢዎችን ይዘናል።»

ከተማይቱን ለመያዝና ላለማስያዝ በተደረገዉ ዉጊያ ሥለደረሰዉ ጉዳት እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ኬንያ መራሹ ጦር ከተመይቱን ለመያዝ ጥቃት ከከፈተ ጀምሮ ከስድስት ሺሕ የሚበልጥ የከተማይቱ ነዋሪ ሸሽቷል።

ነጋሽ መሐመድ

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ