1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአድዋ ድልን የሚዘክር ዩንቨርሲቲ

ዓርብ፣ የካቲት 10 2009

የአድ ዋ ድልን ለመዘከር የሚያስችል የአድዋ ፓን አፍሪካን ዩንቨርሲቲ ሊገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር አስታወቀ። ዩንቨርስቲዉ የአድዋ ጦርነትንና የተገነዉን ድል የሚመለከቱ ጥናትና ምርምሮች የሚካሄድበት ነዉ ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2XmhA
Äthiopien Addis Abeba Gedenken Adwa Mitglieder der Veteranen-Vereinigung
ምስል DW/Getachew Tedla

Adwa Victory memorial university will built. - MP3-Stereo

 

ኢትዮጵያ ከ 121 አመት በፊት በአድዋ ተራሮች ላይ የተጎናጸፈችዉን ድል ለመዘከርና ለትዉልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የሚያስችል የፓን  አፍሪካ ዩንቨርሲቲ ፤በአድዋ  ሊገነባ  መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል።የአድዋ ድል የመላዉ ኢትዮጵያዉያንና የአፍሪካዉያን ብሎም የጥቁር ህዝቦች ድል በመሆኑ፤ይህንን ድል ለመዘከር እስካሁን ከተሰሩ ስራወች በተጨማሪ ዩንቨርሲቲ ለመገንባት  እቅድ መያዙን ለዶቼ ቬለ የገለጹት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና የአለም አቀፍና  ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ  አባተ ናቸዉ።

እንደ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ፤የአድዋ  ፓን  አፍሪካ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ያካተተ በጠቅላይ ሚኒስቴር  ፅህፈት ቤት የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሟል በዩንቨርሲቲዉ የአድዋ ጦርነትንና የተገዉን ድል እንዲሁም በጦርነቱ የተሳተፉ ኢትዮጵያዉያን ታሪክ ላይ ምርምርና ጥናት የሚደረግበት ነዉ።ግንባታዉ መቼ እና በምን ሁኔታ ይከናወናል የሚለዉን ግን ጥናቱ ሲጠናቀቅና ወደ ስራ ሲገባ በባለሙያወችና በኮሚቴዉ የሚገለጽ መሆኑን አቶ ገዛኸኝ ገልጸዋል።         

ጦርነቱ ከተካሄደባቸዉና ድል ከተገኘባቸዉ የአድዋ ተራሮች  ባሻገር ከአድዋ ድል ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ ታሪኮችና ቦታዎችን ለማስታወስ  የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ይሰራሉ ተብሏል።ከነዚህም ዉስጥ ለጦርነቱ መነሻ የሆነዉን የዉጫሌ ዉል የተፈረመበትን ቦታ  ለመዘከር  መታሰቡን አቶ ገዛኸኝ ተናግረዋል።

                  

120. Jahrestag der Schlacht von Adwa
ምስል Yared Sumete

የአድዋ ድል ሲታሰብ  ቦታዎቹንና ታሪኮችን ከመዘከር ባለፈ ድሉን ያስገኙ ጀግኖችን በማክበርና እዉቅና በመስጠት እንዲሁም ለትዉልድ በማስተላለፍ  ረገድስ ምን እየተሰራ ነዉ? ብለን 

ላነሳንላቸዉ ጥያቄ ፤እስካሁን የተሰራዉ በቂ አለመሆኑን ገልጸዉ ወደፊት ግን ዩንቨርሲቲዉን ጨምሮ ሌሎች በሚሰሩ የመታሰቢያ ስራወች እንደየ ታሪክ ድርሻቸዉ ቦታ የሚሰጣቸዉ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በመጭዉ የካቲት 23 ለ121ና ጊዜ  ይከበራል። በአሉ በዋናነት በአድዋ ተራሮች የሚከበር ሲሆን በመላዉ ኢትዮጵያም በተለያዩ ዝግጅቶች  ታስቦ ይዉላል ሲል  የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ገለፃ ያመለክታል።

 

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ