1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«አይ ኤስ» ቡድን የገንዘብ ምንጭ

ሐሙስ፣ ኅዳር 9 2008

ራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ፅንፈኛ ቡድን በቅርቡ ፓሪስ ላይ ያደረሰዉ ጥቃት ብዙ ትኩረት ስቧል። ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርገዉን እንቅስቃሴ የሚመለከቱ ምርመራዎች የሚያሳዩት የፅንፈኛዉ ቡድን የግንኙነት ሰንሰለት እየሰፋ መሄዱን ነዉ። ይህ ፅንፈኛ ቡድን የሽብር ተግባራቱን ለማከናወን የሚያዉለዉን ገንዘብ ከየት ያገኛል?

https://p.dw.com/p/1H98H
Dschihad-Kämpfer im Irak
ምስል picture-alliance/AP Photo

[No title]

ራሱን« እስላማዊ መንግሥት» እያለ የሚጠራዉ በእንግሊዝኛዉ ምህፃር IS የተሰኘዉ ፅንፈኛ ቡድን የገንዘብ ስጋት የለበትም። በተቃራኒዉ በሰሜን ኢራቅ እና ሶርያ ፅንፈኛዉ ቡድን በተቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች፤ መንግሥታቱ ገቢ ያገኙባቸዉ የነበሩ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸዉን መሠረተ ልማቶች በእጁ አስገብቷል። በዚህም ከሚገኙ የነዳጅ ጉድጓድ እና የሞሱል አካባቢ ኗሪዎች ርዳታ የገንዘብ ካዝናዉን ይሞላል። እናም «እስላማዊ መንግሥት» ነኝ የሚለዉ ቡድን በአሁኑ ጊዜ በርካታ የገንዘብ ምንጮች አሉት። የነዳጅ ሽያጭ፣ እገታ እና በዚያ ገንዘብ መጠየቅ፤ ማስገደድ/ማስፈራራት፤ ቀረጥ፤ እና ቅጣት ዋነኛ የቡድኑ ገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዶች ናቸዉ። የሚሰደዱ ሰዎች መኪናቸዉን፤ ጥሬ ገንዘባቸዉ እና ቤቶቻቸዉን ይዘረፋሉ። በዚያም ላይ እንደሳዉድ አረቢያ ያሉ የባህረ ሰላጤዉ አረብ ሃገራት አልቃይዳንና የሶርያዉን አምባገነን ፕሬዝደንት በሽር አል አሰድን በመቃወም ለIS የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በአሁኑ ጊዜ ፅንፈኛዉ አሸባሪ ቡድን እንዲህ ባለዉ መንግሥታዊ የገንዘብ ድጋፍ ላይ የተመረኮዘ እንዳልሆነ በበርን ዩኒቨርሲቲ በእስልምና ላይ ምርምር የሚያካሂዱት ራይንሀርድ ሹልዝ ይናገራሉ።

Symbolbild Geldscheine und Kreditkarten
ምስል picture-alliance/P. Byrne/PA Wire

««እስላማዊ መንግሥት» አለዉ የተባለዉን በጥሬ ገንዘብ 2 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገደማ የደረሰዉን የገንዘብ አቅሙን ስንመለከት፤ ቡድኑ ያካሄደዉን ወረራ እና በዚያ ላይም አሁንም እያደረገ ያለዉን በትክክል ማየት ይቻላል። እነዚያ ቦታዎች የነዳጅ ሀብት እና እርሻ የነበረባቸዉ አካባቢዎች ነበሩ።»

ሌላዉ ዋነኛ ነጥብ ቡድኑ በሚገኝባቸዉ እና በያዛቸዉ አካባቢዎች የኤኮኖሚ እና የገንዘብ መሠረቶችን መገንባት መቻሉ ነዉ። እንደሹልዝ አገላለፅም ይህ IS ከአልቃይዳ የሚለይበት ስልት ነዉ።

«አልቃይዳ በንፅፅር ምንም ዓይነት መሬት ያልተቆጣጠረ፤ ምንዓይነት ግዛት ያልያዘ ራሱን የነጠለ ድርጅት ነበር። ራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ቡድን ግን ሰፊ አካባቢዎችን ይዟል፤ በጣም ትልቅ ግዛትን ተቆጣጥሮ ከአካባቢዉ ገንዘብ እያመነጨ እና ወደግዛቱ ፋይናንስ የሚፈስበትን መንገድ ፈጥሯል፤ አልቃይዳ ይህ አልነበረዉም።»

IS Kolonne Fahrzeuge Toyota
ምስል picture-alliance/AP Photo

እያንዳንዱ የፋይናንስ ምንጭ ጥቅም ላይ ይዉላል፤ ለምሳሌ የተዘረፉና እንዲወድሙ ከተደረጉ ቤተመዘክሮች የተመዘበሩ ባህላዊ ቅርሶች ይሸጣሉ። አነስተኛ እቃዎችም በሕገወጥ መንገድ ወይም በጥቁር ገበያዉ ይቸበቸባሉ። እንደእዉነቱ ከሆነ IS የኢራቋን ሞሱል ከተማ በያዘበት ወቅት የሀገሪቱን ማዕከላዊ ባንክ ዘርፎ በእጁ ካገባዉ 400 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ተጨምሮ፤ ሁለት ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገደማ በጥሬዉ ይዟል። እንዲያም ሆኖ የቡድን ዓይነተኛ የገንዘብ ምንጭ ሕገወጥ ንግዱ ነዉ። በየጊዜዉ ቡድኑ አንድ ሺህ የሚሆኑ የነዳጅ ማጓጓዣ ቦቴዎችን በየጊዜዉ እየሞላ ይነግራል። በምሥራቅ ሶርያ በአልኦማር የነዳጅ ማጣሪያ አካባቢ የቦቴ አሽከርካሪዎች ተራ እስኪደርሳቸዉ ለአንድ ወር ያህል ሊጠብቁ ይችላሉ። ተራ ይዘዉ የሚሰለፉት ተሽከርካሪዎች አንዳንዴ ስድስት ሜትር ርዝመት ይደርሳሉ። ፅንፈኛዉ ቡድን በየወሩ እስከ40 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ከነዳጅ ሽያጩ ይሰበስባል። ሽያጩ የሚከናወነዉ በጥቁር ገበያዉ ነዳጁን ወደሌላ ሀገር አትርፈዉ በመሸጥ ለሚጠቀሙ አቀባባይ ነጋዴዎች ነዉ። ቡድኑ የሚሰበስበዉ ገንዘብ ከቀረጥ ነፃ ነዉ። ቡድኑ ጠላቱ ከሆነዉ የሶርያ ፕሬዝደንት በሽር አል አሳድ መንግሥት ጋር እንደሚደራደር አንድ የBBC ዘጋቢ ፊልም ይፋ አድርጓል። አሳድ ነዳጁን ይፈልጋሉ፤ IS ደግሞ ገንዘብ። አንዳንዴም የነዳጁ ክፍያ የጦር መሣሪያ አቅርቦት ሊሆን ይችላል። ሰሞኑን የተካሄደዉ ቡድን 20 በመባል የሚታወቁት የበለፀጉት 20 ሃገራት ጉባኤ የዚህን ፅንፈኛ ቡድን የገንዘብ ምንጮች ለማድረቅ ወስኗል። ይህ ግን ከድርጊቱ ይልቅ መናገሩ ይቀልል ይሆናል። ቡድኑ ከምንም በላይ በጥሬ ገንዘብ መገበያየትን ይመርጣል። ሊከታተሉት የሚቻል ምንም ዓይነት የገንዘብ ሽግግር ሂደት ባለመኖሩ ስልቱ ገንዘብ በእጁ በቀጥታ እንዲደርስ ያደርግለታል። ራይንሀርድ ሹልዝ፤

Ölraffinerie im Irak
ምስል AP

«በጣም ከተለመደዉ የወጣ የገንዘብ ሽግግር ስልት ነዉ የተመሠረተዉ። አረቦቹ ኃዋላ ከሚሉት አሠራር ጋር የተገናኘ ስልት መሆኑን መገመት ይቻላል። ይህ የፋይናንስ ባለሙያዎች እንኳ ሊረዱት የማይቻል አስቸጋሪ የልዉዉት ሂደት ነዉ። ሌላዉ ቀርቶ ገንዘቡን የሚሰጠዉ አካል ያ ገንዘብ ከየት እንደመጣ እንኳ ሊያዉቅ የማይችልበት አሠራር ነዉ፤ እናም ገንዘቡን የሚቀበለዉ ወገን ከየት እንደመቻ እንኳን አያዉቅም።»

Russland Syrien Militärhilfe
ምስል picture-alliance/dpa/RIA Novosti/D. Vinogradov

ያም ቢሆን ግን ምዕራቡ ዓለም ለዚህ መፍትሄ ያጣል ማለት አይቻልም። IS የሚጠቀምበትን የነዳጅ ቧንቧ መዝጋት፤ ነዳጁ በሚጓጓዝበት ጊዜ ማጥቃት ሁሉ አማራጮች ናቸዉ። ሶርያ ዉስጥ የዩናይትድ ስቴትስ ተዋጊ አዉሮፕላኖች በሰነዘሩት ጥቃት ከ295 የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴዎች 116ቱን አዉድመዋል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም በርካታ ክፍተቶች አሉ። ለምሳሌ የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት ለኢራቅ መንግሥት ያቀረበዉ በቢሊየን የሚገመት ዶላር በፅንፈኛዉ ቡድን እጅ ዉስጥ መግባቱን አረጋግጧል። ይህ እንዴት ሆነ? አሁን አሜሪካ ዶላር በአዉሮፕላን እየጫነች ወደባግዳድ ትልካለት። ያ ገንዘብ ደግሞ የምንዛሪ ጨረታ በሚያካሂዱ ወገኖች እጅ ይገባል። እንዲህ ላለዉ ሁሉ መፍትሄ ካልተገኘ የአሜሪካን ግብር ከፋዮች ገንዘብ በዚህ ፅንፈኛ ቡድን እጅ ብቻ ሳይሆን ማዕቀብ ወደተጣለባቸዉ የኢራን ባንኮችም መግባቱ አይቀርም።

ሀንስ ዩርገን ማዉሩዝ/ ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ