1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

በኢትዮጵያ ለስልኩ ድብልቅ ስሜት ይታያል

ረቡዕ፣ ጥር 3 2009

የ“አይፎን” ዘመናዊ ስልኮች አምራች የሆነው አፕል ኩባንያ መስራች ስቲቭ ጆብስ በመለያ መታወቂያዎቹ ይታወሳል፡፡ ቢሮም ይሁን፣ ስብሰባም ይምራ፣ የኩባንያውን አዳዲስ ምርቶችም ይፋ ያድርግ “ቢትልስ” ሹራብ፣ ጂንስ ሱሪና የስፖርት ጫማ አጥልቆ ነው፡፡ ሲለው በባዶ እግሩ ይዘዋወርም ነበር፡፡

https://p.dw.com/p/2VeFw
USA Apple Phil Schiller präsentiert das iPhone 7 Lightning connection
ምስል Reuters/B. Diefenbach

አይ ፎን አስረኛ ዓመት

ቀለል ያለ የሕይወት ፍልስፍናን ይከተል የነበረው ጆብስ በአንድ ነገር ግን ቀልድ አያውቅም-በጥራት ላይ፡፡ ኩባንያው የሚያመርታቸው ምርቶች እንከን የለሽ እና ጥንቅቅ ያሉ እንዲሆኑ መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት የሚከፍል ነበር፡፡

ወደ ፍጽምና የተጠጋ አካሄድ የስራ መርኹ የነበረው ጆብስ ለምርቶቹ ጥራት አብዝቶ እንደሚጨነቀው ሁሉ ሰው ልብ እንዲገቡ አሉ የተባሉ የማሻሻጥ ጥበቦችን የሚጠቀም ነበር፡፡ ለአጠቃቀም ቀላል እንዲሆኑ ከማድረግ አንስቶ ለዕይታ ሳቢ እንዲሆኑ እስከማድረግ ድረስ ያለውን ሂደት በራሱ ተቆጣጣሪነት ያስፈጽማል፡፡ የሰውየው የጥራት መለኪያ እስከ ምርጥ የምርት ማሸጊያ ድረስ የተለጠጠ ነበር፡፡   

እንዲህ ለተጠቃሚዎች ለመድረስ የተዘጋጁ ምርቶች ታዲያ በተለመደው መልኩ መተዋወቅ የለባቸውም ብሎ ያምናል፡፡ ኩባንያው በየጊዜው ለገበያ የሚያወጣቸውን አዳዲስ ምርቶች ይፋ የሚያደርገው በጥር ወር መጀመሪያ በሚያደርገው ዓመታዊ ዐውደ-ርዕይ እና ስብሰባ ላይ ነበር፡፡ በዚህም የጆብስ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር፡፡ መጀመሪያ የቁልፍ ተነጋሪነቱን ቦታ ለራሱ ይሰጣል፡፡ ኩባንያው በዓመቱ ውስጥ ያከናወናቸውን አዳዲስ ነገሮች ሲያስተዋውቅ ይቆይና “በስተመጨረሻ አንድ ነገር አለ” ይላል፡፡ 

ይህቺ የተለመደች አባባሉ ኩባንያው የሚኮራበትንና የቴክኖሎጂ እመርታ ያሳየ ምርቱን ለማስተዋወቅ የሚጠቅመበት እንደሆነ ስለሚታወቅ ሁሉም ሰፍ ይላል፡፡ ይሄኔ ጆብስ ለሳምንታት ልምምድ ሲደረግ የተቆየበትን የምርት ይፋ ማድረጊያ ስነ-ስርዓት እንደቀላል ነገር ያስኬደዋል፡፡ ብዙ ሺህ ዶላሮች ፈስሶበት፣ ታዋቂ የፕሮግራም አሰናጆች ተቀጥረውለትና በዘመኑ ቴክኖሎጂ ታግዞ የሚከናወነው ስነ-ስርዓት ታዲያ የብዙዎችን ቀልብ መቆጣጠሩ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ 

Steve Jobs mit Apple iPhone
ምስል picture alliance/dpa/J. G. Mabanglo

ጆብስ እንደሌሎቹ የአፕል ምርቶች ሁሉ ልክ የዛሬ 10 ዓመት “አይፎን”ን ይዞ ሲመጣ ተመሳሳይ አካሄዶችን ተጠቅሞ ነው፡፡ ምርቱ የአገሬው ከፍ ሲልም የዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂ ወዳዶች መነጋገሪያ ለመሆን አፍታም አልፈጀበት፡፡ ጋዜጠኞች ስለዘመናዊው ስልክ ልዩ ልዩ ባህርያት ተናግረው አልጠግብ አሉ፡፡ እንዲህ የጀመረው “አይፎን” አንድ ሁለት እያለ አስር የተሻሻሉ ሞዴሎችን ለተጠቃሚ አቅርቦ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ 

የ“አይፎን”ን 10ኛ ዓመት ልደት በማስመልከት የተንቃሳቃሽ ስልኩን ትሩፋቶች እንፈትሻለን፡፡ ንጉሱ ሰለሞን ወጣት የኮምፒውተር እና ኤሌክትሮኒክስ ኢንጂኒየር ነው፡፡ “አይፎን” ለእጅ ስልክ ቴክኖሎጂ “ታላላቅ ነገሮችን” አበርክቷል ይላል፡፡   

“ትክክለኛ ዘመናዊ (smart) ሊባል የሚችል ስልክ ገበያ ላይ ያዋለው አይፎን ነው፡፡ በመጀመሪያ በስልክ ደረጃ የአክስለሮሜትር ቴክኖሎጂን [አግልግሎት] ላይ ያዋለው አይፎን ነው፡፡ የአክስለሮሜትር ቴክኖሎጂ ስልካችን ወደ ጎን ስንገለብጠው አውቆ በራሱ የሚገለበጠውን ማለት ነው፡፡ ሌላው ሙሉ በሙሉ ያለመጠቆሚያ መሳሪያ በጣት ንኪኪ ብቻ እንዲሰራ ተደርጎ [በጎርጎርሳዊው] 2007 በገበያ ላይ በቀረበበት ጊዜ እጅግ በጣም ድንቅ እና አስገራሚ ቴክኖሎጂ ነበር፡፡  ብዙ ዘፈኖችን በአንድ ጊዜ ጭኖ ማጫወት ይችል ነበር፡፡ ኢንተርኔትን ለመጠቀም በጣም እጅግ ቀላል ተደርጎ ነበር የተሰራው፡፡ በተቻለ መጠን ብዙ ነገሮችን ይዞ ነበር የወጣውና በወቅቱ በጣም አስደናቂ ቴክኖሎጂ ነበር፡፡ አሁን ያው ቴክኖሎጂውም እየተዳረሰ መጣ፡፡ አንድ ትንሽ ስልክ ብለን የምንጠቅሰው ነገር አሁን ማሰብ ከምንችለው በላይ ብዙ ዕቃዎችን ይዟል፡፡ ያው ሁሉ የተጀመረው እንግዲህ በአፕል ነው፡፡ እና ለዚህ ደግሞ ትልቅ ውለታ ውለዋል” ይላል የስልኩን ፋና ዋጊ ባህርያት ሲያብራራ፡፡ 

በእርግጥም አይፎን የእጅ ስልክ ከመነጋገሪያነቱ እና የአጭር መልዕክት መለዋወጫነቱ ተራምዶ በርካታ ቁሶቁሶች ሊሰሩ የሚችሏቸውን ነገሮች በአንድ መሳሪያ ጠቅልሎ ማስቀመጥ እንደሚቻል ያመላከተ ነው፡፡ “አይፎን” ሙዚቃ ማድመጫ፣ ድምጽ መቅጃ፣ ጌም መጨዋቻ፣ ካሜራ፣ ኮምፓስ፣ ሰዓት ቆጣሪ እና እንቅልፍ መንቂያን የመሳሰሉ ለየብቻ ይገዙ የነበሩ መሳሪያዎችን በአንድ ሸክፎ በመያዝ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ የስክሪኑ ስፋት፣ ለአያያዝ እና ለአጠቃቀም ቀላል መሆኑ ከዚያ በኋላ የተሰሩ ስልኮች ሁሉ የእርሱን ፈለግ እንዲከተሉ አድርጓል፡፡ 

“አይፎን” በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ቢያስተዋወቅም ባለፉት 10 ዓመታት ያልቀረፋቸው ችግሮች እንዳሉበት ንጉሱ ያምናል፡፡ ስልኮቹ ዲዛይን የተደረጉት እና አጠቃቀማቸውም የተቃኘው ለተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲስማመሙ ተደርጎ እንደሆነ ይከራከራል፡፡ ስልኩ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገራት የሚኖሩ ህዝቦችና አፍሪካውያንን ታሳቢ ያደረገ አይደለም ባይ ነው፡፡ 

“ስልኮቹ ለተጠቃሚ ነጻነት አይሰጡም፡፡ ማለትም እኛ በአፍሪካ ወይም በኢትዮጵያ ደረጃ የምንፈልጋቸው ጥቅሞች አሉ፡፡ ለምሳሌ ፋይሎችን በብሉቱዝም ሆነ በሌላ ገመድ አልባ ቴክኖሎጂ መላላክ እንፈልጋለን፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የትም አካባቢ ሆነን ከስልካችን ወደ ኮምፒውተራችን ፋይል ማስተላለፍ፤ ከኮምፒውተራችንም ወደ ስልካችን ማንኛውንም ፋይሎችን፣ ሙዚቃዎችን፣ ስዕሎችን፣ የፈለግነውን ማስተላለፍ አይነት ጥቅምችን እንፈልጋቸዋልን፡፡ ምክንያቱም በተለመደው አካሄድ ተጨማሪ ምርት መግዛት አንችልም፡፡ አንድ ሰው ስልክ ከገዛ ተጨማሪ ኮምፒውተር ወይም አብሮ አይፓድ መግዛት የለበትምም ወይም ደግሞ አቅሙ የለውም፡፡”

USA Apple Phil Schiller präsentiert das iPhone 7 AirPods
ምስል Reuters/B. Diefenbach

“ተጨማሪ ሜሞሪ ስልኮቻችን ላይ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም [የመረጃ ማስቀመጫ አገልግሎት] cloud service መጠቀም ስለማንችል ወይም ደግሞ ክፍያውም ሊከብደን ስለሚችል ብዙ ነገሮች ስልኮቻችን ለረጅም ጊዜ እንዲቀመጡ እንፈልጋለን፡፡ ያለው ውስን ሜሞሪ ግን ያንን ለማድረግ አይመቸንም” ሲል ችግር ያላቸውን ይዘርዝራል፡፡

እነዚህን አገልግሎቶች የሚሹ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎችም አፍሪካውያን ከ“አይፎን” ይልቅ የ“አንድሮይድ” ዘመናዊ ስልኮችን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ ጉግል የተሰኘውን የመረጃ መፈለጊያ ድረ-ገጽ በሚያስተዳድረው ተቋም አማካኝነት የተሰራውን የ“አንድሮይድ” የማስተናበሪያና ማንቀሳቀሻ ስርዓት (operating system) የሚጠቀሙ በርካታ የተንቀሳቃሽ ስልክ አይነቶች አሉ፡፡ ከእነርሱ መካከል ተጠቃሽ የሆኑት የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ፣ የቻይናው ሁዋዌ እና የታይዋኑ ኤችቲሲ ናቸው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘመናዊ ስልክ ግብይት ከፍተኛውን ድርሻ የተቆጣጠረው ሳምሰንግ ሲሆን አይፎን በሁለተኛነት ይከተላል፡፡ ሁዋዌ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ በኢትዮጵያም ግን “አይፎን” በሽያጭ ሶስተኛ ወደ ሶስተኛ ወይም አራተኛ ደረጃ እንደሚንሸራተት በተንቀሳቃሽ ስልክ ግብይት ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ “ድሪም ሞባይል” የተሰኘ የተንቃሳቃሽ ስልክ መሸጫ ባለቤት የሆነው ዮናታን ቢኒያምም ይህንኑ ያጠናክራል፡፡ 

“እንደእኔ ግምገማ ሳምሰንግ ጥሩ ገበያ አለው፡፡ አንደኛ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሁለተኛ ላይ ሁዋዌ እና ቴክኖ ከተማ ላይ ካሉት ጥሩ [እየተሸጡ ] ያሉ ምርቶች ናቸው፡፡  አይፎን የተወሰነ የገበያ ድርሻ አለው፡፡ ግን እንደነዚያ የበላይ አይደለም፡፡ እኛ ጋር አሁን ገዢዎች ብዙ የሚመርጡት ሳምሰንግና እና አንድሮይድ የሚጠቀሙትን [ተንቀሳቃሽ ስልኮችን] ነው፡፡ ግን አይፎንም በደንብ ገበያ አለ፡፡ ሰፈር ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ ወደ መርካቶ ብዙ ጊዜ አነስ ያሉ፣ ዋጋቸው ቀነስ ያለ ሆነው በብዛት የሚሸጡ ሞባይሎች ብዙ አሉ፡፡ ወደ ቦሌ አካባቢ ደግሞ ስትመጣ ዋጋቸው ከፍ ብሎ ግን ጥራታቸው  ጥሩ የሆነ ፣ ብዙ ጥቅም ያላቸው፣ ካሜራቸው ፣ ፍጥነታቸው፣ የስክሪን ጥራታቸው ምርጥ የሆኑ ይፈለጋሉ” ይላል ዮናታን ስለ ገበያ ሁኔታ ሲያስረዳ፡፡

“አይፎን” እንደ አንድሮይድ ስልኮች በብዛት የማይሸጥበት ምክንያት የዋጋው መወደድ እንደሆነ ዮናታን ይገልጻል፡፡ በቅርብ ለገበያ የዋሉትን ሞዴሎች ብቻ የሚይዘው ዮናታን የሳምሰንግ ምርቶችን ከ15 እስከ 18 ሺህ ብር ሲሸጥ “አይፎኖች”ን ግን እጥፍ ዋጋ ይጠይቅባቸዋል፡፡ በምዕራቡ ዓለም እምብዛም በገበያ የማይገኙት የድሮ “አይፎኖች” ካገለገሉት እስከ ከእሽጋቸው እንኳ እስካልወጡት ድረስ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ንጉሱ ይናገራል፡፡ እነዚህኞቹ በርካሽ ከ2‚500 እስከ ስምንት ሺህ ብር ሊገኙ እንደሚችሉ የሚገልጸው ንጉሱ አዳዲሶቹ ሞዴሎች ግን ዋጋቸው ከ10ሺህ እስከ 26ሺህ ብር እንደሚደርስ ያስረዳል፡፡

Apple lobt Belohnung für Entdecken von Sicherheitslücken aus
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld

በኢትዮጵያውያን ዘንድ “አይፎኖች” ከዋጋቸው ውድነት ሌላ ኢትዮጵያዊ ይዘትን በብዛት ባለማካተታቸው ገሸሽ ሲደረጉ ይስተዋላል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ተብለው የተሰሩ አፕልኬሽኖች ከአይፎን ይልቅ በአንድሮይድ በቁጥር በርከት ብለው እንደሚገኙ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በ“አይፎኖች” ላይ የሚጫኑ አፕልኬሽኖች ለማነሳቸው አንዱ ምክንያት የአንድሮይድ ባለቤት የሆነው ጉግል ባለሙያዎች የሰሩትን አፕልኬሽን በራሱ መገበያያ ላይ እንዲያቀርቡ በዓመት 25 ዶላር ብቻ የሚጠይቅ መሆኑና የአይፎኑ አፕል ግን 100 ዶላር እንዲከፍሉ የሚያደርግ መሆኑ ነው፡፡ 

አንድ አፕልኬሽን ተቀባይነት አግኝቶ ገበያ ላይ የሚቀርብበት ፍጥነትም በሁለቱ ኩባንያዎች ይለያያል፡፡ ጉግል አንድ ተቀባይነትን ያገኘ አፕልኬሽን በ24 ሰዓት ውስጥ ለተጠቃሚዎች በመሸጫው በኩል እንደሚያቀርብ ንጉሱ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪ ሁለት ምክንያቶችም የአንድሮይድ ስልኮች ከአይፎን ይልቅ የተሻለ ተመራጭ እንደሆኑ ያብራራል፡፡

“ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች ናቸው ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያዊ አፕልኬሽን የሚጽፉት፡፡ እነኚህ ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች ብዙ ስልጠና ያገኙት ወይም ደግሞ በትምህርት ደረጃ የዳበሩበት ጃቫ እና አንድሮይድ ላይ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲ እንኳ የሚሰጠው ለአንድሮይድ መስራት ነው፡፡ አይፎን ግን Objective-C የሚባል ቋንቋ ነበር የሚጠቀሙት፡፡ ይህ ቋንቋ ደግሞ ብዙ ጊዜ በትምህርት ቤት ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥም አይሰጠም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ብዙ አፕልኬሽኖች አይፎን ላይ አይገኙም፡፡” 

“ሶስተኛ ደግሞ ምንድነው ያለው፡፡ አንድ አንድሮይድ ላይ የተጻፈ አፕልኬሽን ለዜድ.ቲ.ኢ፣ ለኤች.ቲ.ሲ፣ ለሳምሰንግ እንዲሁም ማንኛውም የአንድሮይድ ተጠቃሚ ሁሉ ያንን አፕልኬሽን ማግኘት ስለሚችል ከአይፎን ይልቅ የመዳረስ ስፋቱ በጣም ትልቅ ይሆናል” ይላል ንጉሱ፡፡  

በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ዘንድ እምብዛም ተመራጭ ያልሆነው “አይፎን” ለእናት ኩባንያው አፕል ከፍተኛ ትርፍ ማጋበሱን ቀጥሏል፡፡ “አይፎን”ን ለዓለም ያስተዋወቀው ስቲቭ ጆብስ ከአምስት ዓመት በፊት በሞት ቢለይም አፕል ግን ከእጅ ሰዓት እስከ ቴሌቬዥን ያሉ አዳዲስ ምርቶችን ማስተዋወቁን ቀጥሏል፡፡ ቀጣይ መዳረሻው ሹፌር አልባ መኪና አልባ እንደሆነ ውስጥ ውስጡን መወራት ይዟል፡፡ ጊዜ ደጉ የማያሳየው የለ፡፡ መጠበቅ ነው፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ