1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአይቨሪ ኮስት ጋዜጠኞች የሰላም ጥረት

ዓርብ፣ ጥር 21 1996
https://p.dw.com/p/E0lA
የአይቨሪ ኮስትን ውዝግብ ያበቃው የሰላም ውል ከተፈረመ ከአንድ ዓመት በኋላ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ሎውሮን ግባግቦ የውሉን ተግባራዊነት እንደሚያፋጥኑ ከጥቂት ቀናት በፊት ያስታወቁበት ድርጊት በሀገሪቱ የኃይሉ ተግባር በጉልህ እንዲቀንስ አድርጎዋል። የሰላሙ ውል በተግባር የሚተረጎምበት ድርጊት እንዲፋጠን፡ በርስ በርሱ ውጊያ የተመሰቃቀለችው ሀገር ሕዝብም አንድ እንዲሆን እና ሰላም እንዲሠፍን የግል ድርጅቶችም የበኩላቸውን ጥረት አነቃቅተዋል። በዚሁ ዕርቀ ሰላም በማውረዱ ጥረት መደዳም አንድ የወጣት ጋዜጠኞች ማኅበር ቀዳሚውን ቦታ ይዞዋል። ምክንያቱም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ውዝግቡ ለተባባሰበት ድርጊት የተጫወቱት ሚና በቀላሉ የሚታይ አልነበረምና። ማኅበሩ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ይዞት ከተነሣው በጎ ፈቃድና ፅኑ ፍላጎት በስተቀር ጽሕፈት ቤትም ሆነ አስፈላጊው ቁሣቁስ እንኳን የለውም። መገናኛ ብዙኃን በጋዜጦች ባቀረቡዋቸው ዘገባዎቻቸውና በቴሌቪዥን ባሳዩዋቸው ዝግጅቶች የአይቨሪ ኮስትን ውዝግብ እንዳጋጋሉ፡ ውጥረቱ እንዲስፋፋ በማድረግ ቀጥተኛ ሚና መያዛቸውን የቡድኑ አባል የሆነውና 24አወርስ ለተሰኘው ነፃ መጽሔት የሚሠራው ጋዜጠኛው ፓርፌ ኩሳይ አስታውቋል። በመሆኑም ተግባራቸው በሀገሪቱ ላይ ያስከተለውን ጉዳት በመገንዘብ፡ ሰላም እንደገና ሊወርድ ለሚችልበት ሁኔታ የሚጠበቅባቸውን ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አሳስቦዋል። በፓርቲዎች ላይ ጥገኛ የሆኑት ትልቆቹ የሀገሪቱ ራድዮ ጣቢያዎችና የቴሌቪዥን ድርጅቶች ከብዙ ዓመታት ወዲህ በውጭ ሀገር ዜጎች አንፃር ጥላቻውን አስፋፍተዋል። የሎውሮ ግባግቦ መንግሥትም በውሁዳኑ ቡድናት አንፃር የክትትሉን ርምጃ ባስፋፋበት ተግባርም ሥልጣኑን ለማጠናከር እንደቻለ ጋዜጠኛው ኩሳይ ይናገራል። በሰሜነሀገሪቱ ከፊል የሚኖሩ ሙሥሊሞችና ሥራ ብለው ወደ አይቨሪ ኮስት የሄዱ የውጭ ሀገር ዜጎች በፕሬዚደንቱ ፓርቲ እና በአንዳንድ ጋዜጦች በተበረታቱ ወገኖች ተገድለዋል ወይም ተዘርፈዋል ወይም ብርቱ ክትትል ተደርጎባቸዋል። አሁን ዕርቀ ሰላም ለማስገኘት ቆርጦ የተነሣሣው የጋዜጠኞቹን ቡድን የመሳሰሉ ድርጅቶች ጋዜጠኞች ያለባችውን ኃላፊነት ከዓይን ሳይርቁ በሚያቀርቡዋቸው ዘገባዎቻቸው አማካይነት በጎሣዎች መካከል ጥላቻ የሚያስፋፉ ፖለቲከኞች ከዚሁ ሀገሪቱን ከሚከፋፍለው ተግባር እንዲቆጠቡና የሰላሙን ድርድር እንዲያነቃቁ ጥሪ የማቅረብ ዓላማ ይዘው ተነሥተዋል። የሰላሙን ውል ከአንድ ዓመት በፊት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የፈረሙት ፕሬዚደንት ግባግቦ ሂደቱን ተግባራዊ ለመድረግ ባመነቱበት ሁኔታ ሰበብ ተቀናቃኝ ዓማፅያኑና ሚሊሺያዎች ገና የጦር መሣሪያ ትጥቃቸውን መፍታት አልጀመሩም። ይህም ጋዜጠኞች ሥራቸውን በነፃ እንዳያከናውኑ አዳጋቹን ሁኔታ እንደፈጠረባቸው ኩሳይ አንድ የፈረንሣይ ራድዮ ቃል አቀባይ ባለፉት የመፀው ወራት በሀገሪቱ ፖሊስ የተገደለበትንና በራሱም ላይ በተደጋጋሚ የሚቀርብበትን የማስፈራሪያ ዛቻ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ አመልክቶዋል።