1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡናና የአየር ንብረት ለዉጥ ጫና

ማክሰኞ፣ ሰኔ 20 2009

ቡናን ለዓለም ያበረከተችዉ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የቡና ምርቷ ከግማሽ በላይ ሊቀንስ እንደሚችል ከሰሞኑ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት አመልክቷል። ጥናቱ እንደሚለዉ የሙቀት መጠን እየጨመረ መሄድ ከጥቂት አስርት ዓመታት በኋላ ቡናን በማብቀል በሚታወቁ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማስከተሉ አይቀርም።

https://p.dw.com/p/2fUOd
Japan Äthiopien Kaffee Projekt
ምስል James Jeffrey

የአየር ንብረት ለዉጥ ያሰጋዉ የኢትዮጵያ ቡና

ቡና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑ ዛሬም ይነገርለታል። አረቢካ የተባለዉን እና እጅግ ምርጥ እና ተወዳጅ የሆነዉን የቡና ዘር ለዓለም ያበረከተችዉ የዚህች ሀገር 15 ሚሊየን ገደማ የሚሆኑ ዜጎች ቡናን በማምረት ኑሯቸዉን ይደጉማሉ። ቡና አምራች ከሆኑት የአፍሪቃ ሃገራትም አብዛኛዉን ቡና የምታመርተዉ ኢትዮጵያ ናት። እንዲያም ሆኖ የቀጠለዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ያስከተለዉ የሙቀት መጨመር በያዝነዉ ምዕተ ዓመት ማለቂያ በኢትዮጵያ ቡና የሚያመርቱ አካባቢዎች ከ39 እስከ 59 በመቶ ገደማ ሊቀንሱ እንደሚችሉ ነዉ አዲሱ ጥናት የጠቆመዉ። የአየር ጠባይ የተመለከተዉ መረጃ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1950ዎቹ ዓ,ም ወዲህ የዝናብ መጠኑ 40 በመቶ እየቀነሰ መሄዱን ያሳያል። በዚህ ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተደጋገመ የሚከሰተዉ ድርቅ ቡና የሚያበቅሉ አካባቢዎች ላይም የራሱን ተፅዕኖ እያስከተለ እንደሆነም ያስረዳል። ይህ ደግሞ በሂደት ከቀጣይ ጥቂት አስርት ዓመታት በኋላ የሀገሪቱ የቡና ምርት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ አስተዋፅኦ ያደርጋል። በዚህ የአየር ጠባይ ለዉጥ ምክንያት የጫካ ቡናም ሆነ ሌላዉ የቡና ዓይነት ነዉ የምርት ይዘቱ ጉዳት የሚገጥመዉ። ዝቅተኛ አካባቢዎች ደግሞ ዋነኛ ተጋላጭ ናቸዉ። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ባለሙያ እንደሚሉት የአየር ንብረት ለዉጥ ያስከተለዉ የሙቀት መጠን ከፍ ማለት አሁን ባለዉ የኢትዮጵያ የቡና ምርት ላይ ያስከተለዉ ችግር ያን ያህል የሚባል አይደለም። አሳሳቢዉ ደንን መልሶ የመተካቱ እና የቡና ተክሉንም ሙቀት ወዳልጠናባቸዉ ከፍተኛ አካባቢዎች የማላመዱ ርምጃ ካልተወሰደ ከ20 ዓመት በኋላ ሊከሰት የሚችለዉ ነዉ። ጥናቱን ካካሄዱት ምሁራን አንዱ የሆኑት ዶክተር ታደሰ ወልደ ማርያም ቡና የት መብቀል እንደሚችል እና በተለይ የጫካ ቡና የሚገኝበት አካባቢ ምን ይመስላል፤ አብረዉትስ የሚገኙት ተክሎች እንዴት ያሉ ናቸዉ የሚለዉን አጥንተዋል። እሳቸዉ የሚመሩት የአካባቢ ተፈጥሮ እና የቡና ጫና መድረክ በእንግሊዝኛዉ «ኢንቫይሮመንት ኤንድ ኮፊ ፎረስት ፎረም፤» በቡና እና በቡና ደን ላይ ጥናት ያካሂዳል። በጥናቱ ዉጤት ተመርኩዞም ለቡና ገበሬዎች በዘላቂነት ጥራቱን የጠበቀ ቡና ማምረት እንዲችሉ፤ ያመረቱት ቡናም ገበያ እንዲያገኝ እገዛ ያደርጋል።

Kaffee Bauer in Äthiopien
ምስል AP Photo
Äthiopien Kaffee Farmer sortieren Kaffee Bohnen
ምስል AP Photo

ኢትዮጵያ ከዓለማችን ቡና አምራች ሃገራት በአምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከአፍሪቃ ደግሞ ዋነኛዋ ቡና ለዉጪ የምትልክ ሀገር ናት። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015 እና 16 ዓ,ም ብቻ 800 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ያወጣ  180 ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና ልካለች። ከሀገሪቱ ዓመታዊ የዉጭ ንግድ ገቢ ሩቡን የሚሸፍነዉ ይህ የቡና ምርት በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ከዓመታት በኋላ እንዳያሽቆለቁል እጽዋት ላይ የሚያጠኑ በርከት ያሉ ምሁራን የተሳተፉበት ጥናት ከወዲሁ አስጠንቅቋል። ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች ለተከታታይ ዓመታት ያካሄዱትን ጥናት መሠረት በማድረግም ከእንግዲህ እንደወትሮዉ መቀጠል ስለማይቻል ለቡና ተክል ተገቢዉ ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝበዋል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ