1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ የብልጽግና ጉዞ ከሮማው ውል እስከ ኤውሮ

ሐሙስ፣ መጋቢት 17 2001

የአውሮፓ የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብ ምሥረታ ውል ሮማ ላይ ከተፈረመ ዛሬ 52 ዓመት ሆነው።

https://p.dw.com/p/HJoD
የማስትሪሽት ጉባዔ
የማስትሪሽት ጉባዔምስል AP

በተከታዩ ዓመት መግቢያ ላይ የጸናውን ስምምነት በመጀመሪያ የተፈራረሙት ስድሥት መንግሥታት፤ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፤ የቤኔሊክስ አካባቢ አገሮች፤ ቤልጂግ፣ ኔዘርላንድና ሉክሰምቡርግ ነበሩ። በዚሁም በአውሮፓ መሃል ላይ የመጀመሪያው የጋራ የኤኮኖሚ አካባቢ ዕውን ይሆናል። እ.ጎ.አ. መጋቢት 25 ቀን. 1957 ዓ.ም. የተፈረመው የሮማ ውል የኋላ ኋላ ለሰፈነው የአውሮፓ ሕብረትም ዋና መሠረቱ ነበር። የአውሮፓ የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብ ምሥረታ ለምጣኔ-ሐብት ዕድገትና ለብልጽግና ጽኑ መሠረት ከመጣሉም ባሻገር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለክፍለ-ዓለሚቱ ሰላም ጽናትም ታላቅ አስተዋጽኦ ነው ያደረገው። የአውሮፓው ሕብረት ዛሬ በዓለም ላይ ጠንካራው የኤኮኖሚ ክልል ሲሆን የጋራው ምንዛሪ የኤውሮ ክስተትም አንዱ የታሪካዊ ዕርምጃው ውጤትና መለያ ነው።

ወቅቱ የኢጣሊያ ርዕሰ-ከተማ ሮማ ለብዙ ቀናት በዝናብ የጨገገችበት ነበር። ሆኖም ዝናብና ብርድ ለአውሮፓውያኑ መሪዎች የሚደረገውን ታሪካዊ መስተንግዶ አላቀዘቀዘውም። ትምሕርት ቤቶች ሲዘጉ ሕጻናት የመንግሥታቱን መሪዎች ለማየት በጉጉት ወደ ከተማ ያመራሉ። በዚህ ሁኔታ ነበር ስድሥቱ አውሮፓውያን መንግሥት በሮማ ከእድም ሁለት ውሎች የተፈራረሙት። ከውሎቹ አንዱ የአውሮፓው የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብ ምሥረታ ሲሆን ሌላው ደግሞ ኤውርአቶም በሚል አሕጽሮት የሚታወቀው የአቶም ሃይል ስምምነት ነበር። የአውሮፓው የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብ ምሥረታ ውል ስድሥት ዓመታት ቀደም ሲል የተደረገውን የሞንታን ሕብረት በመባል የሚታወቅ የማዕድን ከሰልና የብረታ-ብረት የጋራ ስምምነት ተከትሎ ነበር የሰፈነው።

ስድሥቱ የሮማው ውል ተፈራራሚ መንግሥታት ይህንኑ ከሰልና ብረት አምራች ለሆኑ ኢንዱስትሪዎች የጋራ ገበያ ለመፍጠር ሐምሌ 23 ቀን. 1952 ዓ.ም. የተደረገውን ስምምነት ሲያሰፍኑ ለሃምሣ ዓመታት በዘለቀው ውል ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባሩ ከብሄራዊ ወደ ጋራ ባለሥልጣን የተሻገረበትም ነበር። በሞንታኑ ውል በተለይ የጀርመንን ያህል ተጠቃሚ የሆነ አልነበረም። በመሆኑም የመጀመሪያው የጀርመን ቻንስለር ኮንራድ አደንአወር አዳዲሶቹን ውሎች ገሃድ በማድረጉ ረገድ ሚናቸው የጠነከረ ነበር። በስብሰባው ላይ ባሰሙት ንግግርም የማሕበረ-ሕዝቡ መፈጠር በረጅም ጊዜ የሚኖረውን የጋራ ጠቀሜታ ጠለቅ አድርገው ማብራራታቸው አልቀረም።

“እየጠነከረ የሚሄድ የስድሥት አገሮቻችን ትብብር ብቻ ነው ሁላችንም ነጻ ዕድገታችንንና ማሕበራዊ ዕርምጃችንን እንድናረጋግጥ ሊያደርገን የሚችለው። የአውሮፓ ማሕበረ-ሕዝብ ሰላማዊ ግብን ብቻ ነው የሚከተለው። ማንንም አይጻረርም፤ ከየትኛውም መንግሥት ጋር ለመተባበር ዝግጁ ነው። መቀላለል ለሚፈልጉ ለሁሉም የአውሮፓ አገሮች ክፍት ሆኖ ይቀጥላል”

እንዲያ ሲል ምሽት ላይ የተጀመረው ሥነ-ሥርዓት የስድሥቱ መንግሥታት ተጠሪዎች የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብና የአቶም ውል ተፈራርመው በስኬት ይፈጸማል። ከዚያን ወዲህ አንስቶ ነው በአውሮፓ የጋራ ገበያ አካባቢ በመንግሥታት መካከል የቀረጥና የንግድ መሰናክል መወገድ የጀመረው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጥሎት ያለፈው የቁስል አሻራ በክፍለ-ዓለሚቱ ገና ሕያው ሆኖ ሳለ ጦርነቱ ባበቃ በ 12 ዓመቱ ሥር የሰደደው አለመተማመን በጊዜው ይወገዳል ብሎ ማመኑ ቀላል አልነበረም። ሆኖም ለሮማው ውል ተፈራራሚዎች የጋራ የአውሮፓ የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብን ያህል ክፍለ-ዓለሚቱን ከተከታይ ጦርነቶች የሚሰውር መከላከያ አለመኖሩ ግልጽ ነበር። የጊዜው የፈረንሣይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮበርት ሹማን ውሉ በተፈረመበት በዚያ ታሪካዊ ዕለት የወደፊት የአውሮፓ ራዕያቸውን እንዲህ ነበር የገለጹት።

“አውሮፓ ተጻራሪ ሃይሎች ደም የሚፋሰሱባት መተራረጃ ቦታ መሆኗን ማብቃት ይኖርባታል። ከዚህ ከባድ መስዋዕትነትን ከጠየቀ ግንዛቤ ተነስተን አንድ ወደሆነችና ዘላቂ ሰላም ወደሰፈነባት አውሮፓ በሚመራ አዲስ መንገድ መራመድ ነው የምንፈልገው”

በዕውነትም አውሮፓ ምንም እንኳ በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ለአሠርተ-ዓመታት ተከፋፍላ ብትቀጥልም የኤኮኖሚው ትብብር ክፍለ-ዓለሚቱ ከቀድሞው ትውልድ ይልቅ ለረጅም ጊዜ በሰላም እንድትኖር ነው ያደረገው። አውሮፓ በኤኮኖሚ ማሕበረሰቡ መሠረት ላይ በመቆም የአውሮፓን ሕብረት ፈጥራ ወደፊት ስትገሰግስ ዛሬ እስከ ምሥራቅ በመሥፋፋት 27 ዓባል ሃገራትን ለመጠቅለል በቅታ ነው የምትገኘው። መጋቢት 25 ቀን 1957 ዓ.ም. የዚህ ታሪካዊና ተመሳሳይ ያልታየለት ዕርምጃ የልደት ቀን ሲሆን የሮማው ውልም የምሥክር ወረቀቱ፤ መለያው ነው። ዕድገቱን የረጅም ጊዜው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርቺል በጊዜው የተነበዩት ጉዳይ ነበር።

“አውሮፓ በመጀመሪያ በተባበረች ጊዜ ሶሥት ወይም አራት መቶ ሚሊዮን ነዋሪዎቿ ወሰን የለሽ ደስታ፣ ብልጽግና፣ ሃያልነትንና ክብርን ይጎናጸፋሉ”

የአውሮፓው ማሕበረ-ሕዝብ ዕውነትም ብዙዎች አገሮችን እያስተሳሰረና የጋራ ዕርገታቸውን መሠረትም እያሰፋ ይሄዳል። እ.ጎ.አ. በ 1985 ዓ.ም. ሉክሰምቡርግ ውስጥ አምሥት መንግሥታት በተፈራረሙት የሼንገን ውል በጋራ ወሰናቸው ላይ የነበረውን ቁጥጥር ያስወግዳሉ። የሼንገኑ ውል ዛሬ እየተስፋፋ መጥቶ በ 28የአውሮፓ አገሮች የሚሰራበት ደምብ ነው። እርግጥ በአውሮፓው የትስስር ሂደት ውስጥ የአውሮፓ ሕብረት ሕያው የሆነበት የማስትሪሽት ውል ደግሞ ይበልጥ ታላቅ ቦታን ይይዛል።
በኔዘርላንድ ከተማ በማስትሪሽት የጊዜው የአውሮፓ ማሕበረ-ሕዝብ 12 ዓባል መንግሥታት መሪዎች የፈረሙት ውል ከሕብረቱ ባሻገር ለጋራው ምንዛሪ ለኤውሮም ጥርጊያን የከፈተ ነበር። በማስትሪሽቱ ውል አሮጌው ማሕበረ-ሕዝብ ከመሠረቱ ሲጠገን ለውጡ ለአውሮፓ ፓርላማ የበለጠ ሥልጣን ከመስጠት ሌላ የጋራ የውጭና የጸጥታ ፖሊሲ፤ እንዲሁም ለአውሮፓ የውስጥ ገበያና የጋራ ኤኮኖሚ ሕብረትም መንገድ ያመቻቻል። ይህም ኤውሮን ከ 2002 ዓ.ም. አንስቶ የጋራ መገልገያ ምንዛሪ በማድረግ የተሟላ ሂደት ነው።

እርግጥ ምንዛሪው ገና በመላው የሕብረቱ ዓባል ሃገራት የሕዝብ መገልገያ ባይሆንም የኤውሮው አካባቢ በዓለም ላይ ታላቁ የምንዛሪ አካባቢ ለመሆን በቅቷል። የጋራ ምንዛሪው በሰፈነበት ዕለት የቀድሞው የጀርመን የፊናንስ ሚኒስትር ሃንስ አይሽል እንዳሉት ድርጊቱ በአውሮፓ የአንድነት ሂደት ውስጥ ፍጹም ታሪካዊ ነበር።

“ዕለቱን ታሪካዊ የሚያደርገው እያንዳንዱ ሰው የአውሮፓ አንድነት ምን ማለት እንደሆነ በቅርብ እንዲዳስስ፤ እንዲሁም ለኛ ለአውሮፓውያን ታላቁ የብልጽግናና የሰላም ፕሮዤ መሆኑን ማሣየቱ ነው”

በሌላ በኩል ኤውሮ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የኑሮ ውድነት መለያ ሆኖ በብዙዎች ቢታይም በወቅቱ በዓለም ላይ የተረጋጋው ምንዛሪ ሊሆን በቅቶ ነው የሚገኘው። ሌሎች አገሮች ተቀማጭ ገንዘባቸውን በኤውሮ እያደረጉ ሲሄዱ ዛሬ ከፊሉ የነዳጅ ዘይት ንግድ የሚካሄደውም በዚሁ ምንዛሪ ነው። በወቅቱ 16 የሕብረቱ ዓባል ሃገራት የሚገለገሉበት የአውሮፓው ምንዛሪ ከአሜሪካ ዶላር አንጻርም የዋጋ ዕድገት አሳይቷል።

በአጠቃላይ ታሪካዊው የአውሮፓ የአንድነት ሂደት ለማሕበራዊ ዕድገትና ለጋራ ብልጽግና ታላቅ አርአያነት አለው። በእሢያ የኤኮኖሚው ማሕበር አዜያን የሕብረቱን ፈለግ ተከትሎ ለማደግ በያዘው ጥረት ጠቃሚ ዕርምጃ አድርጓል። የአፍሪቃ ሕብረትም ሕልም ቢቀር በፍላጎት ደረጃ በዚሁ አቅጣጫ መራመድ ነው። ይሁንና በተለይ አፍሪቃን በተመለከተ ለዚሁ ዕርምጃ አስፈላጊ የሆኑት መሠረታዊ ሁኔታዎች በጣሙን ይጎላሉ። ለአውሮፓው ሕብረት የግማሽ ምዕተ-ዓመት ታሪካዊ ዕርምጃ ወሣኙ ነገር የዴሞክራሲ ስርዓት መኖሩ፤ ለማሕበረ-ሕዝቡ የኤኮኖሚ ዕርምጃም መዋቅራዊው ይዞታ መመቻቸቱ ነበር።

አፍሪቃ በአንጻሩ ዛሬ የምትገኝበት ሁኔታ እነዚህ መሠረታዊ ሁኔታዎች አሉ ማለቱ ቀርቶ ሂደቱ እንኳ ወደዚያ መሆኑን ለመናገር እጅግ የሚያዳግት ነው። የአውሮፓን ፈለግ ተከትሎ የሕብረት ዕድገት ለማድረግ ከተፈለገ በጎ አስተዳደርና ፍትሃዊ ስርዓት ግድ ይሆናል። ቢሮክራሲ መወገዱ፣ ፍቱን የገበያ ኤኮኖሚ ስርዓት መኖሩና ነጻው የኤኮኖሚ ዘርፍ መስፋፋቱ፤ እንዲሁም ከመሰናክሎች ነጻ የሆነ የአካባቢ ገበዮች እንቅስቃሴ ገሃድ መሆን ይጠበቅበታል። ከሁሉም በላይ ጠቃሚው ደግሞ እንዳለፈው አንድ አሠርተ-ዓመት በብዙዎች አገሮች ታየ የተባለው ተከታታይ የኤኮኖሚ ዕድገት የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ በሚያሻሽል ማሕበራዊ ዕድገት መከሰት መቻሉ ነው።

ሕዝብ ከረሃብ አፋፍ ላይ ቆሞና ፍትሃዊ ስርዓት ጎሎ ዕድገትም ሕብረትም አይሆንም። ብልጽግና ሰላምን፣ በጎ አስተዳደርንና አርቆ አስተዋይነትን ይጠይቃል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውድመት በኋላ በአውሮፓ የታየው የኤኮኖሚ ትብብርና የሕብረት ዕርምጃ ትርጉሙ፤ ትምሕርቱም እዚህ ላይ ነው። አውሮፓ ከጦርነቱ ወዲህ ረጅሙን የሰላም ዘመን በብልጽግና ለማሳለፍ ችላለች።

መሥፍን መኮንን, DW