1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ሕብረት የባልካን ማረጋጊያ ውል

ሐሙስ፣ ግንቦት 24 1998

የአውሮፓ ሕብረት የባልካንን ሁኔታ ከጦርነቱ በኋላ ለማረጋጋት፤ በረጅም ጊዜም ከራሱ ጋር ለማስተሳሰር የውል ድርድር ከጀመረ ሰባት ዓመታት ገደማ አለፉ። የውሉ ዓላማ ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ለአካባቢው የሚሰጠውን ዕርዳታ በተሻለ ሁኔታ ማቀናጀትና ሃገራቱ በመካከላቸው ያለውን ትብብር እንዲያጠናክሩ ማበረታታት ነበር።

https://p.dw.com/p/E0dj
የሰርቢያ-ሞንቴኔግሮ ሰንደቅ ዓላማ

በዚሁ ተግባር ሃምሣ መንግሥታት በለጋሽነት የሚሳተፉ ሲሆን ዕርዳታው የሚቀናበረው ከአውሮፓው ሕብረት መቀመጫ ከብራስልስ ነው። በአውሮፓው ሕብረት ማረጋጊያ ውል መሠረት ከኮሶቮው ጦርነር በኋላ ወደ ባልካኑ አካባቢ የፈሰሰው ዕርዳታ ከ 30 ሚሊያርድ ዶላር ይበልጣል። በሌላ በኩልም ተቀባዮቹ አገሮች፤ አልባኒያ፣ ቦስና ሄርሴጎቪና፣ ቡልጋሪያ፣ ክሮኤሺያ፣ ማቄዶኒያ፣ ሩሜኒያና ሞልዳቪያና ኮሶቮን ጨምሮ ሰርቢያ ሞንቴኔግሮ በየጊዜው እየተገናኙ በአካባቢ ትብብራቸው ሂደት ላይ ይመክራሉ።
አሁን ከሰባት ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ ማረጋጊያውን ትስስር ወደ አንድ የአካባቢ ትብብር ሸንጎ ለመለወጥ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ዋናው ለውጥ የደቡብ አውሮፓው መንግሥታት ወደፊት የበለጠ ሃላፊነት መቀበላቸውና ሚናቸውም መጠናከሩ ይሆናል። በሣምንቱ መጀመሪያ ሰኞና ማክሰኞ ቤልግሬድ ላይ ተካሂዶ የነበረው የማረጋጊያው ውል ጉባዔም ዋና የንግግር ርዕስ ያደረገው ይህን’ኑ ነበር።

ጉባዔው በደረሰበት ስምምነት መሠረት አዲሱ የአካባቢ ተራድኦ ሸንጎ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የባልካን አገሮች፣ የአውሮፓን ሕብረትና የዓለምአቀፉን ማሕበረሰብ ተጠሪዎች የሚጠቀልል ነው የሚሆነው። ዓላማውም እስካሁን በማረጋጊያው ውል መሠረት ይከናወኑ የነበሩትን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል፤ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ለመቀላቀል የሚደረገውን ጥረትም መደገፍ ይሆናል። ወደ አዲሱ የአካባቢ ተራድኦ ሸንጎ የሚደረገው ሽግግር እስከ 2008 ይጠናቀቃል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

የአውሮፓ ሕብረት የማረጋጋጊያው ጥረት አስተባባሪ ኤርሃርድ ቡሤክ እንደሚሉት ከዚህ ግብ እንደሚደረስና ጥረቱም ከራሱ ከአካባቢው ተጠናክሮ መምጣት እንዳለበት የሁሉም ዕምነት ነው። የአካባቢው የትብብር ሸንጎ የባልካኑን አገሮች የወደፊት የአውሮፓ ሕብረት ዓባልነት የሚተካ አይደለም። ወደ ሕብረቱ በሚደረገው ጉዞ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚጠቅም ፍቱን ትብብርን ለማስፈን የሚረዳ ነው። የሕብረቱ የመስፋፋት ጉዳይ ኮሜሣር ኦሊ ሬህን በተለይ ትናንሾቹ አገሮች የአካባቢውን ትብብር አጥብቀው እንደሚፈልጉ አስረድተዋል።

“የዛሬው ዕለት ለማረጋጊያው ውል እጅግ ጠቃሚ ቀን ነው። ጥረቱን እስከ 2008 መጀመሪያ ወደ ደቡባዊው አውሮፓ ማሸጋሽጉ በግልጽ የተቀመጠ የአካባቢ መዋቅር ሊኖረው ይገባል። አካባቢው መዘውሩን ሊይዝ የሚችለው እንዲህ ሲሆን ነው”ብለዋል።

የቤልግሬዱ የማረጋጊያው ውል ጉባዔ ከኤኮኖሚው ዘርፍ ሌላ በዴሞክራሲና በጸጥታ ጉዳዮችም አተኩሯል። እነዚህ ሁለቱ የኋላኞቹ ነጥቦች ለኤኮኖሚው ዕድገት የግድ አስፈላጊ እንደመሆናቸው መጠን የአውሮፓ ሕብረት ለወደፊቱ ትስስር ዓቢይ ክብደት የሚሰጣችው ናቸው። የሰብዓዊ መብቶች መከበርና ፍትሃዊ የፍርድ ሥርዓት መስፈን፤ በጸጥታው አኳያም አስፈላጊው እርጋታ መስፈኑና የወንጀል ድርጊቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ለወደፊቱ የአውሮፓ ሕብረት ዓባልነት ወሣኝነት ይኖራችዋል።

እስካሁን ከቀድሞይቱ ዩጎዝላቪያ መፍረስ ወዲህ አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት የአውሮፓን ሕብረት በዓባልነት መቀላቀል የቻለችው ስሎቬኒያ ብቻ ናት። ከክሮኤሺያ ጋር የሚካሄደው ድርድር የተፈለገውን ያህል ወደፊት ሊገፋ አልቻለም። ሕብረቱ ከቤልግሬድ ጋር ድርድር ለመጀመር ሰርቢያ የጦር ወንጀለኞችን አሳልፋ መስጠቷን ቅድመ-ግዴታ ሲያደርግ ከደቡባዊው ባልካን አካባቢ ምናልባትም የተሻለ ዕድል ያላት ሰሞኑን በሕዝበ-ውሣኔ ነጻነትን የመረጠችው ሞንቴኔግሮ ናት። በሌላ በኩል ቡልጋሪያና ሩሜኒያ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ሕብረቱን መቀላቀላቸው ከሞላ-ጎደል የተረጋገጠ ነገር ሆኗል።
የቤልግሬዱ ጉባዔ ኤኮኖሚን በተመለከተ በአካባቢው የምጣኔ-ሐብት ዕድገትና የሥራ ገበያ ሁኔታ አተኩሯል። የተገኘው ግንዛቤ የንግድ ደምቦች መለዘብና መዋዕለ-ነዋይን የሚስብ ሁኔታ መፈጠሩ ያስፈልጋል የሚል ነው። ለማንኛውም በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ለትራንስፖርትና ለኤነርጂ ዘርፎች ዕድገት አርባ ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚጠጋ ካፒታል በሥራ ላይ መዋሉ እንደሚያስፈልግ ነው የሚታመነው።

በአጠቃላይ አዲሱ የአካባቢ ትብብር የባልካኑን አገሮች ከአውሮፓው ሕብረት በማስተሳሰሩ በኩል እጅግ ጠቃሚ ሂደት ነው። ኮሜሣር ኦሊ ሬህን በጉባዔው አኳያ ከሰርቢያ ባለሥልጣናት ባካሄዱት ንግግር አጋጣሚውን በመጠቀም ቤልግሬድና ፖድጎሪትሣ ከቅርቡ የሞንቴኔግሮ የነጻነት ሕዝበ-ውሣኔ በኋላ በውይይት እንዲቀጥሉ ጥሪ አድርገዋል።

የዓለም ባንክ የ 2006 ዓመታዊ የዓለምአቀፍ ልማት የፊናንስ ዘገባውን ከትናንት በስቲያ አውጥቷል። ዘገባው እንዳመለከተው ቀደም ባለው 2005 ዓ.ም. ወደ ታዳጊ አገሮች የፈሰሰው የግል መዋዕለ-ነዋይ ወደ 491 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። ከመቶ ቢሊዮን በላይ ነው የጨመረው። የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ የወለድ ማደግና የበጀት ኪሣራ መበራከት ሳይበግረው የፈሰሰው ካፒታል እስካሁን አቻ ያልታየለት መሆኑ ነው። የዓለም ባንክ የግል መዋዕለ-ነዋዩ መጨመር በርከት ባሉ ታዳጊ አገሮች የወደፊት የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ዓመኔታ መኖሩን የሚያንጸባርቅ ነው ብሎታል። የሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ሂደትም ተመሳሳይ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።
ሆኖም በካፒታሉ ማየል የሚጠቀሙ ሁሉም ታዳጊ አገሮች አይደሉም። የዓለም ባንክ እንደዘገበው አብዛኛው ገንዘብ ድሃውን ሕዝብ አላዳረሰም። ታዳጊ አገሮች ዛሬ እየናረ ከሚሄደው የሕዝባቸው ቁጥር አንጻር መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ፈተና ላይ ወድቀው ነው የሚገኙት። በመሆኑም ብዙዎቹ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድሃ ሕዝቦቻችውን መሠረታዊ የኤነርጂና የውሃ ጥም ለመወጣት በግል ኩባንያዎች ላይ ለመተማመን አይችሉም።

የዓለም ባንክ በልማት ጉባዔው ላይ እንዳለው ደግሞ የውሃ፣ የኤነርጂ፣ የትራንስፖርትና የቴሌኮሙኒኬሺን ግልጋሎት መኖርና የሙስና መወገድ የተስፋፋውን ድህነት ለመቀነስ ቁልፍ ግዴታዎች ናቸው። ዛሬ በዓለም ላይ ከሚኖረው 6.3 ቢሊዮን ሕዝብ መካከል 1.6 ቢሊዮኑ መሠረታዊ የአነርጂ አገልግሎት አይደርሰውም። ከዚህ ሕዝብ 500 ሚሊዮን የሚሆነው የሚኖረውም ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል ነው።
የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ፓውል ዎልፎቪትስ እንደገለጹት የውሃና የመጸዳጃ አገልግሎት የማያገኘው የምድራችን ሕዝብ በአጠቃላይ 2.6 ቢሊዮን ይደርሳል። ዓለምአቀፉ መዋቅራዊ ይዞታም የዛሬውን ዘመን ፍላጎት ለማሟላት የሚበቃ ሆኖ አይገኝም። የባንኩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በታዳጊ አገሮች መዋቅራዊ ግንባታ መስክ የግሉ ዘርፍ መዋዕለ ነዋይ ከአሥር ዓመታት በፊት 128 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋ ነበር። ሆኖም በ 2003 በግማሽ ገደማ ወደ 58 ቢሊዮን መቀነሱ አልቀረም።
ይህ የሚያመለክተው የግሉ ዘርፍ ለመዋቅራዊው ግንባታ ፍላጎት ሁሉ ምላሽ ለመስጠት ብቃትና ፍላጎቱ እንደሌለው ነው። ለምሳሌ በዘጠናኛዎቹ ዓመታት የግሉ ዘርፍ በመንገድ ግንባታ፣ በውሃና በኤነርጂ አቅርቦት ሰፊ ሚና በመያዝ ዓለምአቀፉን ድህነት ለመቀነስ ይረዳል የሚል ታላቅ ተሥፋ ነበር የተጣለው። ግን ይህ የተጠበቀው ውጤት ዕውን አልሆነም። ሆኖም በሌላ በኩል የግል ዘርፉ ወደፊትም ጠቃሜታ፤ አስፈላጊነትም ይኖረዋል።

የአፍሪቃ ሕዝብ ቁጥር አንድ ቢሊዮን የሚደርስበት ጊዜ ዛሬ ሩቅ አይደለም። የዓለም ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄዱን እንደቀጠለ ሲሆን የከተማ ነዋሪዎች ብዛት በሚቀጥለው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ከገጠር ነዋሪዎች የበለጠ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው። ታዲያ መንግሥታዊ ዘርፎች ብቻችውን አስፈላጊውን መዋቅር ለመገንባትም ሆነ ዕድገቱን ተከትሎ ለመራመድ በቂ አቅም እንደማይኖራቸው ግልጽ ነው። ስለዚህም መንግሥታቱና አበዳሪ ተቋሞቻቸው የማይችሉትን በግሉ ዘርፍ አቅም ማሟላቱ ግድ ይሆናል።
የዓለም ባንኩ ፕሬዚደንት ፓውል ዎልፎቪትስ ለጉባዔው እንዳስረዱት የከተማውን ነዋሪ መዋቅራዊ ፍላጎት የአካባቢ ተፈጥሮን በመንከባከብ ማሟላቱ ደግሞ ታላቅ ፈተና ነው። መዋቅራዊ ግንባታና ልማት የሚለው የጉባዔው ርዕስ የተሻሉ መንገዶች፣ ትራንስፖርት፣ ኤነርጂና የውሃ አገልግሎቶች በቢሊዮን የሚቆጠር የዓለም ድሃ ሕዝብን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል መጣሩ ዓቢይ ትኩረት እንደሚሰጠው የሚያመለክት ነው።
ዎልፎቪትስ እንዳሉት አፍሪቃውያን ውሃ በመሸከም ብቻ በያመቱ አርባ ቢሊዮን ጠቃሚ የሥራ ሰዓታትን ያባክናሉ። ይህ ጊዜ ለትምሕርት፣ ሠርቶ የኑሮ ገቢ ለማግኘት ወይም አዳዲስ ንግዶች ለመጀመር ሊጠቅም የሚችል ነው። የዓለም ባንክ ሙስና የአያሌ ሕዝብን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት የሚያሰናክል መቅሰፍት ሆኖ እንደቀጠለም አስገንዝቧል።

እርግጥ ሙስና የተለመደው በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ውስጥ ብቻ አይደለም። በተለያየ መልክ በዓለም ዙሪያ ተንሰራፍቶ የሚገኝ ነገር ነው። ግን የአፍሪቃውን የድህነቱ መስፋፋት መጠን የከፋ ያደርገዋል። የሆነው ሆኖ ክፍለ-ዓለሚቱን ከድህነት ለማላቀቅ ከተፈለገ ግን በገዢዎች ዘንድ ተስፋፍቶ የሚገኘው ሙስና መወገዱ ግድ ነው። ዕርዳታውም ሆነ ለልማት የሚሰጠው በጀት ለሕዝብ ሊደርስ፤ ተጠቃሚ ሊያደርገውም ካልቻለ የረባ ትርጉም አይኖረውም። ስለዚህም በአፍሪቃ የሰብዓዊ መብቶች መከበርና በጎ አስተዳደር መስፈኑ ልማትን ለማየት ቅድመ-ግዴታ ይሆናል።