1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ህብረትና ስደተኞች

ማክሰኞ፣ መስከረም 4 2008

የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ አውሮፓ የገቡ ስደተኞችን ተከፋፍሎ ለመውሰድ በቀረበላቸው ሃሳብ ላይ ለመስማማት ትናንት ብራሰል ቤልጅየም ውስጥ ያካሄዱት ስብሰባ ያለ ውጤት ተበትኗል ።ሚኒስትሮቹ እልባት ባላገኘው በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት በመጪው ጥቅምት ለመነጋገር ሌላ ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

https://p.dw.com/p/1GWzO
Thomas de Maiziere / Bernard Cazeneuve / Innenminister / Brüssel
ምስል picture-alliance/AP Photo

የአውሮፓ ህብረትና ስደተኞች

ከአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች አንዳንዶቹ ወደ ትናንቱ የብራሰልሱ ስብሰባ ከመግባታቸው በፊት በሰጡት አስተያየት ስደተኞችን ተከፋፍሎ በመውሰዱ ሃሳብ ላይ ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል ተስፋ ነበራቸው ። በዙር የሚደርሰው የወቅቱ የህብረቱ ፕሬዝዳንት የሉክስምበርግ የኢሚግሬሽንና የተገን ጠያቂዎች ጉዳይ ሚኒስትር ፣ የን አሰልቦርን ተሰብሳቢዎቹ ተጨባጭ እርምጃዎችን የመውሰድ ሥልጣኑ ኃይሉና ፍላጎቱ አላቸው ሲሉ ከስብሰባው በፊት ቢናገሩም ከ8 ሰዓታት በኋላ በሰጡት መግለጫ ግን ተጨባጭ እርምጃ ብለው የተናገሩት አልነበረም ። ከዚያ ይልቅ ሚኒስትሩ ሃሳቡ የብዙሃኑን ድጋፍ አግኝቷል ሲሉ ማለፋቸውን የዶቼቬለዋ አንድሪያ ሮንስበርግ የዘገበችው ። ስብሰባው ከመጀመሩ ከ2 ሰዓት አስቀድሞ የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደሚዜር እና የፈረንሳዩ አቻቸው ቤርናርድ ካዜነቭ በሰጡት መግለጫም እንደተናገሩት ቢያንስ በአንዳንድ አነስተኛ ሊባሉ በሚችሉ እርምጃዎች ላይ ይስማማሉ የሚል ግምት ወስደው ነበር ። ሆኖም ስብሰባው የታሰበለትን ግብ ሳይመታ ነው ያበቃው ።ሚኒስትሮቹ ትናንት ብራሰልስ ቤልጅየም ውስጥ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ግሪክ ኢጣልያና ሃንጋሪ የሚገኙ 160 ሺህ ስደተኞችን በአስቸኳይ እንዲከፋፈሉ ባቀረበው ጥያቄ ላይ ተነጋግሮ አግባቢ ውሳኔ ለማሳለፍ ነበር ።የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር ባለፈው ረቡዕ ባስተላለፉት በዚህ ጥሪ ኮሚሽኑ እቅዱን ያወጣው ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተመሳሳይ ችግሮችን ለመቋቋም ጭምር መሆኑን ሽታራስቡርግ ፈረንሳይ ለተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት አስረድተው ነበር ። «ስደተኞችን በሚመለከተው መርሃችን ይበልጥ አንድ መሆን ያስፈልገናል ።እውነተኛው የአውሮፓ የስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች መርህ ፣በፖሊሲያችንና በደንቦቻችን ላይ በቋሚነት ትብብርን የሚያጠቃልል ሊሆን ይገባል ። ኮሚሽኑ ዛሬ ያቀረበው ሃሳብም ስደተኞችን በቋሚነት ወደ ሌላ ቦታ ማስፈር ነው ። ይህ አሰራር ወደፊት የሚያጋጥሙ ቀውሶችን በቀላሉ ለመቋቋም ያስችለናል ።»

Symbolbild Ungarn Grenze Zaun
ምስል picture alliance/CITYPRESS 24/Hay

ዩንከር አውሮፓ አሁን የገጠመውን የስደተኞች ማዕበል ለመቋቋም ይረዳል ሲሉ ባለፈው ሳምንት ያቀረቡት አዲስ እቅድ 22 ቱ የህብረቱ አባል ሃገራት፣ ግሪክ ፣ኢጣልያ ና ሃንጋሪ የሚገኙ 120 ሺህ ስደተኞችን ተከፋፍለው እንዲወስዱ የሚጠይቅ ነው ። ህብረቱ አባል ሃገራት ይከፋፈሉ የሚለው በኢጣልያ የሚገኙ 15,600 ፣ግሪክ ያሉ 50,400 እንዲሁም ሃንጋሪ የደረሱ 54 ሺህ ስደተኞችን ነው። የአባል ሃገራትን የህዝብ ብዛት መሠረት ባደረገው በኮሚሽኑ እቅድ ጀርመን 40,206 ፣ፈረንሳይ 30,783 ፣ ስፓኝ 19 ሺህ ፣ኔዘርላንድስ 9261 ስደተኞች እንዲቀበሉ ተጠይቀዋል ።

የህብረቱ ኮሚሽኑ ባለፈው ግንቦትም ኢጣልያ የሚገኙ 24 ሺህ ስደተኞችን ና ግሪክ ያሉ 16 ሺህ ስደተኞችን በአጠቃላይ 40 ሺህ ስደተኞችን አባላቱ ተከፋፍለው እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርቦ ነበር ። ሚኒስትሮቹ ትናንት ከተስማሙባቸው ጉዳዮች አንድ ዓለም ዓቀፍ ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል ለተባሉ ባለፉት 4 ሳምንታት ኢጣልያና ግሪክ የገቡ 40 ሺህ ስደተኞችን መውሰድ ብቻ ነው ። ይህ ትናንት በይፋ ይፅደቅ እንጂ የአውሮፓ ህብረት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ባለፈው ሐምሌ ውሳኔ ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነበር ። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደሚዜር የትናንቱ የአውሮፓ ህብረት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ይጠበቅበት የነበረውን ዋና ውሳኔ ባለማሳለፉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል ።

«ይህ በቂ አይደለም ።በዚህም ምክንያት አንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ተስማምተን ቢሆን ኖሮ ወሳኝ እርምጃ ላይ ደርሰን ነበር ። ሆኖም ከአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ይጠበቅ ከነበረው ከዚህ ውሳኔ ርቀናል።»

DW Euromaxx Wir-Gefühl EINSCHRÄNKUNG
ምስል DW

አንዳንድ ሃገራት ተባብረው ለመሥራት ሃላፊነት ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አውሮፓን ችግር ላይ እንደጣሉትም ደሜዜር ሳያነሱ አላለፉም l።ከዚህ ሌላ ሚኒስትሮቹ በትናንቱ ስብሰባቸው ለህይወት የማያሰጉ የሚባሉ ሃገራት ስም ዝርዝር ለማፅደቅም ተስማምተዋል ።ሆኖም ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት በመጪው ጥቅምት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ነው ።ደሚዜር እንዳሉት ደግሞ ሚኒስትሮቹ የስደተኞች መተላለፊያ ያሏቸውን ሃገራትም ለይተዋል ።

«ስደተኞቹ የሚተላለፉባቸው ሃገሮች የትኛዎቹ እንደሆኑ ተግባብተናል ። እነዚህ በቱርክ ቀጥሎ ያሉት የባልካን ሃገራት ናቸው ።»

ደሚዜር በትናንቱ ስብሰባ ግሪክም የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት መስማማቷን እንዳሳወቀችም አስረድተዋል ።

«ዛሬ ግሪክ ብዙ የአስቸኳይ ጊዜ የስደተኞች ጊዜያዊ መቀበያ ጣቢያ ለመክፈት ተስማምታለች ።ግሪክ ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም እንደምታደርገው ሁሉ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር ይበልጥ ተባብራ ለመሥራትም ፈቃደኝነቷን ገልጻለች ።»

የአውሮፓ ህብረት የምሥራቅ አውሮፓዎቹ ሃገራት ፖላንድ 11,946 ቼክ ሪፐብሊክ 40,306 ስሎቫክያ 2,287 ፣ስሎቬንያ 1,126 ፣ ሃንጋሪ 827 ስደተኞች እንዲቀበሉ ጠይቋል ። ይሁንና እነዚህ ሃገራት ህብረቱ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል ። ። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ሃገራቱን ለማግባባት ባለፈው ሳምንት ቼክ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ፕራግ ጎራ ብለው ነበር ። ይሁንና የቼክ ሪፐብሊክ፣ የሃንጋሪ፣ የፖላንድና የስሎቫክያ አቻዎቻቸው የአውሮፓ ህብረት ያወጣውን ስደተኞችን የመከፋፈል እቅድ እንዲቀበሉ ማሳመን አልቻሉም ። ስደተኞች ወደ ኦስትሪያና ወደ ጀርመን መተላለፊያ የሚያደርጓት ሃንጋሪ ስደተኞች ከመቀበል ይልቅ በደቡባዊ ድንበሯ 4 ሜትር ርዝመት ያለው አጭር ግንባታ እያጠናቀቀች ነው ።የቀኝ ክንፉ የሃንጋሪ መንግሥት አሁን የስደተኞች ዋነና መሸጋገሪያ የሆነውን ዋና መንገድ ዛሬ ዘግቷል ። ከሰርቢያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ተገን ለመጠየቅ የሚመጣውንም ስደተኛ እንደምትመልስ ሃንጋሪ አስታውቃለች ።በስውር ለመግባት የሚሞክር ማንኛውም ስደተኛ እስር ይጠብቀዋል ስትልም እያስፈራራች ነው ። የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን መንግሥታቸው በባልካን ሃገራት በኩል አድርገው ወደ ጀርመንና ስዊድን የሚሄዱ ሙስሊሞች የሚሸጋገሩበትን መንድ የሚዘጋው የአውሮፓን የክርስትና እሴቶች ለማስጠበቅ ነው ይላሉ ።ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ በተባለው በአሁኑ የስደተኞች ጎርፍ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሃንጋሪ በኩል ወደ ሰሜንና ምዕራብ አውሮፓ መግባታቸው ቀጥሏል ።

Ungarn baut den Grenzzaun zu Serbien mit Hilfe von Gefängnisinsassen zu Ende
ምስል Reuters/D. Balogh

ትናንት ስደተኞች ተከፋፍለው ለመውሰድ መስማማት ያቃታቸው የአውሮፓ ህብረት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች በመጪው ጥቅምት ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ቀጠሮ ይዘዋል ። የጥቅምቱ ስብሰባ አግባቢ ውሳኔ ላይ የሚደርሱበት ይሁን አይሁን ወደፊት ይታያል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ