1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ወጣቶች ያለ ሥራና ተስፋ

ዓርብ፣ ነሐሴ 23 2006

ሰሞንን የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያመላክተው አውሮፓ ውስጥ የወጣት ሥራ አጡ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር በ30 000 ከፍ ብሎ 7,5 ሚሊዮን ደርሷል።

https://p.dw.com/p/1D3YN
Arbeitslosigkeit Frankreich - Arbeitsamt
ምስል picture-alliance/dpa

ሲውዘርላንድ ስምንት ሚሊዮን ገደማ የሚሆን ነዋሪ አላት። ወይ ስራ ወይም ደግሞ የሙያ ስልጠና ሳያገኙ አውሮፓ ውስጥ የተቀመጡ ወጣቶች ቁጥር የዚህን ህዝብ ቁጥር ሊያክል ምን ቀረው። ይህንን ነው የሮበርት ቦሽ ተቋም ጥናት ሰሞኑን ያረጋገጠው። እንደ ጥናቱ አሁንም በስፓኝ እና ግሪክ ያለ ከሁለት አንዱ ወጣት ስራ የለውም። የሮበርት ቦሽ ተቋም ስራ አስኪያጅ ኢንግሪት ሀም እንደሚሉት ይህ አሃዝ እጅግ አሳሳቢ ነው።« ተስፋ ቢስ ትውልድ ነው በዚህ አጋጣሚ እየተፈጠረ ያለው። ይህ ወደ ስራ ዓለም በመግቢያ ጊዜ ጠባሳ ሆኖ እንደሚቀር እና ገና ዘላቂነት ያለው እንደሆነ ጠበብቶች ያውቃሉ። በርካታ በወጣትነት ጊዜያቸው ስራ ያላገኙ ሰዎች እድሜ ልካቸውን ራሳቸውን ሳይችሉ የቀሩ አሉ። ከገቡበት ሊወጡበት የማይችሉ የማህበራዊ ቀውስ ነው ያለው።»

እንደ ኢጣሊያ፣ ግሪክ፣ ስፓኝ እና ፖርቹጋል ያሉ ሀገራት በተደጋጋሚ ስራ አጥነት እንደአጠቃቸው ሰሞኑን የወጣው አዲስ ጥናት አመላክቷል። ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ የሚያቋርጡ ወጣቶች በመበራከታቸው ነው። ከዚህም ሌላ በየሀገሪቱ የሥራ ገበያ ላይ ያልተመረኮዘ ሙያዊ የስልጠና አሰጣጥ ፣ በሰራተኛ ማህበራት እና በሰራተኛ ቀጣሪዎች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች እንደ ምክንያት ተጠቅሰዋል። ኢጣሊያን የወሰድን እንደሆነ ለምሳሌ የትምህርት አሰጣጡ ላይ ጉድለት እንዳለው ምሁራን ይገልጿሉ። እኢአ ከ1995 ጀምሮ ለትምህርት አሰጣጥ የተመደበው ባጀት ላይ ጭማሬ አልተደረገም። አዲሱ የስራ አጥ ጥናት እንደሚያሳየው ስፓኝ ውስጥ ከ5 ተማሪ አንዱ ትምህርቱን አያጠናቅቅም። በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርቱን ካጠናቀቁት ውስጥ በሰለጠኑበት ሙያ ወይም ጨርሶ ስራ አያገኙም።

Bettler in Athen
ግሪክ ውስጥ የሚለምን ወጣትምስል picture alliance/ANE

ለስራ አጥነት በርካታ ምክንያቶች አሉ። የባጀት ቀውስ ብቻ ምንክያት አይሆንም ይላሉ በአውሮፓ የኢኮኖሚ ጥናት ተቋም የስራ እድል አጥኒ ሆልገር ቦኒን። እንደ እሳቸው ይህ ከ 10 ዓመት በፊትም የነበረ የመዋቅር ችግር ነው። « እነዚህ የትምህርት አሰጣጦች ከስራው ዓለም የራቁ ናቸው። ለመስሪያ ቤቶች ከሚያስፈልጓቸው በላይ ሰዎች ሲሰለጥኑ ችግር መሆን ይጀምራል። ምሩቃን ሲያፈሩ ነገር ግን ለምሩቃን የሚሆን ስራ ከሌለ በርገጠኝነት ስራ አጥነት ይፈጥራል። ይህ ካልሆነ እና የስራ እድል ከተገኘ ደግሞ ከእውቀታቸው በታች የሆነ ስራ ያገኛሉ።ነገር ግን አንድ ምሩቅ ለረዥም ጊዜ ታክሲ ለመንዳት ሲገደድ ዘላቂነት ያለው መዘዝ ይኖረዋል።»

ይህንን የቦኒን ሀሳብ በርካታ ስራ ያጡ ወጣቶች ይጋራሉ። ሌይ እዚህ ጀርመን ሀገር በንግድ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ስራ ግን እስካሁን በማፈላለግ ላይ ነው።«በትክክል ከአንድ አመት በፊት ነሀሴ 2013 ነበር የተመረቁሁት። ስለዚህ ስራ ስፈልግ አንድ ዓመት ሆነኝ ማለት ነው። በመካከል የተወሰኑ የስራ ልምምዶች አግኝቼ ለአጭር ጊዜ ሰርቼያለሁ። ቋሚ ስራ ግን አላገኘሁም።»

Spanien Protest Demonstration Puerta del Sol Madrid
ስራ አጥነትን የምትቃወም ስፓኛዊምስል picture alliance/Fabian Stratenschulte

የዓለም አቀፍ የንግድ አስተዳደርን ዋና ምርጫው አድርጎ ያጠናው ሌይ ምኞቴ ከፍ ያለ ስለነበር ይሆናል ምናልባት ያልተሳካው ይላል አንድ እውቅና ያለው መስሪያ ቤት ለመቀጠር በመፈለጉ። « እንደገና ከማመልከቴ በፊት የተለያዩ የሚያስፈልጉ ስልጠናዎችን እወስዳለሁ ብዬ የተነሳሁት ለዛ ነበር ። ነገር ግን ስራውን ለማግኘት አላበቃኝም። ስለዚህ አሁን እቅዴን ወደታች ቀንሼ ማመልከት ነው ።»

ስራ ማግኘት አንዱ ችግር ሆኖ ሳለ ፤ ስራ ያገኙ ጀማሪዎች ደግሞ ቋሚ እስኪሆኑ የኮንትራት ውላቸው በየጊዜው መራዘም ይኖርበታል ስለሆነም ስራቸው አስተማማኝነት የለውም። ባለፉት አመታት ይልቁንስ ወጣት ምሩቃን የጎደለ ሰራተኛ ማሟያ ሆነው ሲሰሩ ተስተውለዋል።» ይላሉ የዚህ የስራ አጥ ጥናት ፀሀፊዎች ። የጀርምን ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዱኤታ ራይነር ሶንቶቭስኪ እንደሚሉት ጀርመን የአውሮፓ ጎረቤት ሀገሮችን ስራ በማግኘቱ ረገድ ልትተባበር ይገባል። « በኢንተርኔት አገልግሎት ዘመን እየኖርን በአውሮፓስራ የሚያገናኝ የኦንላይን ገበያ የለንም። ስራ አጥተው ስፓኝ የተቀመጡ ወጣቶች ለምሳሌ ጀርመን የት ስራ እንዳለ ማፈላለጉን የሚያቃልልላቸው።»

ሶንቶቭስኪ ይሁንና ፖለቲካዊ አካሄድ ከሚፈቅደው የዘለለ መሆን እንደሌለበት በሌላ በኩል ይመክራሉ። የመኪና መለዋወጫ አምራች የሆነው ቦሽ በዚህ በአውሮፕያኑ አመት መጨረሻ ድረስ ለ100 ወጣቶች የስራ እድል ሲሰጥ ከዚህም 50 ቦታዎች ለስፓኛዊያን ነበር የሰጠው። ይሁንና ምንም ጀርመን የሚገኙ ወጣቶች ደቡብ አውሮፓ እንደሚገኙት በስራ አጥነት ባይጨናነቁም ፤ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሌይ እና መሰሎቹ ይናገራሉ። ሌይ ከልጅነቱ ጀምሮ ከቻይናውያን ወላጆቹ ጋር ጀርመን ሀገር ሲኖር የሁለቱንም ሀገር ባህል እና አኗኗር በቅርበት ለማወቅ ችሏል። በሌላ በኩል ቻይና ከሁሉም የአለማችን ሀገራት ጋ ኢኮኖማዊ የንግድ ትስስር አላት። ለአንድ የንግድ አስተዳደር ላጠና ሰውና ፤ ቻይናን በወሬ ብቻ ሳይሆን በአካል ለሚያውቅ ወጣት ስራ ማግኘት ቀላል አይሆንም?« እኔንጃ ብዙውን ጊዜ ሰዎች እንደዛ ይሉኛል። እስካሁን ግን እንደዛ ሆኖ አላገኘሁትም። ወይ ለኔ አልታወቀኝም ወይ ደግሞ ሰዎች እንደሚያሟሙቁት አይደለም። ስለዚህ ለኔ እንደዛ ነው ለማለት አልችልም።»

እንደ ሌይ የንግድ አስተዳደር ተምራ በዚህ አመት የተመረቀችው ካርሎታ ሁለት ዲግሪ አላት፤ ሁለተኛው ዲግሪዋም ከንግድ አስተዳደሩ ጋር የተያያዘ ፤የአለም አቀፍ የንግድ ሽያጭ ሲሆን ይህንን ያጠናቀቀችው ደግሞ ሀገሯ ስፓኝ ነው። በአሁኑ ሰዓት በስራ ማፈላለግ ላይ ትገኛለች። « በመጀመሪያ እዚህ ጀርመን ውስጥ ስራ አፈላልጋለሁ። ከስፓኝ ጋ ሲነፃፀር ጀርመን ውስጥ ብዙ እድል አለን። ስፓኝ አሁን ያለው ሁኔታ ብዙ ጥሩ አይደለም ስለዚህ አንድ ሁለት አመት የስራ ልምምድ አደርግና ወደ ሀገሬ እመለሳለሁ።

Spanien Arbeitslosigkeit Schlange vor Arbeitsamt
አሰሪ እና ሰራተኛን የሚያገናኝ መስሪያ ቤት በስፓኝምስል picture-alliance/dpa

የ24 አመቷ ወጣት ጀርመን ሀገርም ስራ የማግኘት እድሏ ሰፊ ነው። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ዮናይትድ ስቴትስ ነው፤ እዚህ ጀርመን ሀገርም በረዳት አስተዳዳሪነት በአንድ የልብስ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ተቀጥራ የመስራት እድል አግኝታለች። በአሁኑ ሰዓት ለዕረፍት ወደ ሀገሯ ስፓኝ የተጓዘችው ካርሎታ፤ በስፓኝ ያሉ ወጣቶች ያላቸውን ችግር እንዲህ ታብራራለች።« ችግሩ በርካታ ወጣቶች እንግሊዘኛ ወይም ሌላ ቋንቋ አይናገሩም። ይህ አንዱ ችግር ነው ምክንያቱም በርካታ ዓለም አቀፍ መስሪያ ቤቶች ሁለት ወይም ሶስት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን መቅጠር ነው የሚፈልጉት። ሌላው ደግሞ በሁለት የከፍተኛ ተቋም የተመረቁ እዚህ የሚከፈላቸው 1000 በዛ ቢባል 1200 ዮሮ ነው። እኛ ደግሞ ከማስተርስ በኋላ እንድናገኝ የምንፈልገው ይህን አይደለም።»

ተመርቀው ስራ ከሚያፈላልጉት ወጣቶች ጨርሶ ሙያዊ ስልጠና ወደሌላቸው ስናልፍ ደግሞ፤ ጀርመን ውስጥ እድሜያቸው ከ 25 እስከ 35 የሆኑ 1,5 ሚሊዮን ሰዎች የከፍተኛ ተቋምም ይሁን ምንም አይነት ሙያዊ ስልጠና ያላገኙ ወይም ስልጠናቸውን ያላጠናቀቁ ይኖራሉ። በዚህም የተነሳ የተሻለ ስራ የላቸውም። ስለሆነም የጀርመን መንግስት እስከ ጎርጎሬሲያኑ 2015 ድረስ ይህንን ቁጥር በግማሽ ለመቀነስ እቅድ አውጥቷል። በዚህም መሰረት «ለዘግይቶ ጀማሪዎች» በሚል አዲስ ተሳትፎ ተጀምሯል። ባለፈው አመት በተጀመረው ስልጠና 32 000 ጎልማሶች ተካፍለዋል። ኤቫ ኪራይ የትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ ከተቀመጠች አመታት ተቆጥረዋል። የ32 ዓመቷ በርሊናዊ ከሌሎች 22 ተማሪዎች ጋ አንድ ክፍል ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርት ሻጭ ሆና ለመመረቅ ተቀምጣለች። «ዘግይቶ ጀማሪ» መባሉን ግን አትመርጥም።«ዘግይቶ ጀማሪ» ማለት ለኔ እስከዛሬ ድረስ እድሜ ልኩን ምንም ያልሰራ ነው። እኔ ግን እንደዛ አይደለሁም። ለአመታት የቀሰምኩት የሙያ ልምድ አለኝ። በዛ ላይ ከሀገር ውጪም ተሞክሮ አለኝ። የሌለኝ ነገር ቢኖር የትምህርት ማስረጃ ነው።»

Deutschland Frankreich deutsch-französisches Arbeitsamt in Kehl
አሰሪ እና ሰራተኛን የሚያገናኝ መስሪያ ቤት በጀርመንምስል PATRICK HERTZOG/AFP/Getty Images

ይሁንና ጀርመን ሀገር ስራ ለመቀጠር ወይ የከፍተኛ ተቋም ወይም የረዥም ጊዜ ሙያዊ ስልጠና ያገኙበት የምስክር ማስረጃ ወሳኝ ነው። ኤቫ ምንም እንኳን 30ዎቹን ዕድሜ ብትጀምርም አብረዋት አንድ ክፍል የተቀመጡት የ16 አመት ወጣቶች አለመሆናቸው ተስፋ ሰጥቷታል።« በ30 አመት ገና ትምህርት ቤት መሄድ ለሚሉት አንገት መድፋት አያስፈልግም። ይህ አለማወቅ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ራስን ከጎበዞቹ ጋር ማወዳደር አያስፈልግም። ስለዚህ የሆነውን ተቀብሎ ፤ በሌላ በኩል ይህን እና ያንን ሰርቼያለሁ እያሉ ራስን ማበረታታት ነው። በተገኘው ሁለተኛ እድል አዲስ ነገር መማር ይቻላል። »

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ