1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳው ኅብረት በአዲስ ኣባላት መስፋፋት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 21 1996

የአውሮጳው ኅብረት እንደጎርጎራዊው አቆጣጠር በግንቦት አንድ፣ ፪ሺ፬---ማለት በመጭው ቅዳሜ---አሥር አዲስ ኣባላትን ተቀብሎ፣ የጠቅላላ አባላቱን አሃዝ ፳፭ ያደርሰዋል። እነዚሁ አሥሩ በባልቲክ አካባቢ የሚገኙት የቀድሞዎቹ ሶቭየት-ሬፑብሊኮች ኤስቶኒያ፣ ላትቪያና ሊቷንያ፣ እንዲሁም የቀድሞዎቹ የምሥራቅ አውሮጳ ኮሙኒስት ሀገሮች ፖላንድ፣ ስሎቫኪያ፣ ስሎቬኒያ፣ ቸክሬፑብሊክ እና ሁንጋሪያ፣ ሁለቱ የማዕከላይ ባሕር ደሴቶች ማልታና ቆጵሮስ ናቸው።

https://p.dw.com/p/E0fl
የአውሮጳው ኅብረት በአዲስ አባላት መስፋፋት
የአውሮጳው ኅብረት በአዲስ አባላት መስፋፋትምስል APTN


እንግዲህ የአውሮጳው ኅብረት አሁን በአሥር አዲስ ኣባላት ከተስፋፋ በኋላ፣ እነርሱም በበኩላቸው ሙሉ አባልነትን የሚሹት የደቡብምሥራቅ አውሮጳ ሀገሮችስ እንዴት ሊሆኑ ነው? እነዚሁ ሩማንያንና ቡልጋሪን የመሳሰሉት የደቡብምሥራቅ አውሮጳ ሀገሮች ለጊዜው የአባልነቱ በር ባይከፈትላቸውም፣ ወደፊት ዕድሉ እንደማይነሳቸው አሁን ተነግሮአቸዋል።

የአውሮጳው ኅብረት ለመላው የደቡብምሥራቅ አውሮጳ ሀገሮች ነው የአባልነቱን ዕድል የከፈተው። እንዲያውም ከሩማኒያና ከቡልጋሪያ ጋር አሁንም ነው ድርድር በመካሄድ ላይ የሚገኘው። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከክሮአሲያም ጋር ድርድሩ እንደሚከፈት ነው የሚጠበቀው። እነዚሁ የኣባልነቱን ቀን በጉጉት በመጠባባቅ ላይ የሚገኙት የደቡብምሥራቅ አውሮጳ ሀገሮች ይኸው ዓላማቸው ምናልባት እ ጎ አ በ፪ሺ፯ እውን ሊሆን እንደሚበቃ ነው ተሥፋ የሚያደርጉት። ግን እስከዚያው ድረስ ለሙሉ አባልነት የሚጠየቅባቸውን የለውጥ መስፈርት አሟልተው ይገኙ ይሆን? የአውሮጳውም ኅብረት የገባውን ቃል ይጠብቅ ይሆን? ለመሆኑ የአውሮጳው ኅብረት በመጭው ቅዳሜ የአባላቱን አሃዝ ወደ ፳፭ ካመጠቀ በኋላ፣ ራሱን እንደገና በሌሎችም ተጨማሪ አባላት ለማስፋፋት ፍላጎትና ብቃት ይኖረዋልን?

በጀርመን ፈደራዊ ምክርቤት/ቡንደሳታክ ውስጥ የሶሻልዴሞክራቶቹ አንጃ ምክትል ሊቀመንበር ጌርኖት ኤርለር በሚያቀርቡት አስተያየት መሠረት፣ አሁን ፲፭ ኣባልሀገሮች ያሉት የአውሮጳው ኅብረት በ፲ አዲስ አባላት ተስፋፍቶ የጠቅላላ አባላቱን አሃዝ ፳፭ ካደረሰውም በኋላ ለሌሎች ተጨማሪ አባላት በሩን ክፍት እንደሚያደርግ የሚያጠራጥር ሆኖ አይታይም። በዚህ ረገድ አንድ ምሳሌ ሆና የምትጠቀሰው አሁን በመጋቢት የአባልነቱን ማመልከቻ ያቀረበችው፣ የዩጎዝላቪያ ግማድ የነበረችው መቄዶኒያ ናት። ጌርኖት ኤርለር ዶይቸቬለ ራዲዮና የደቡብምሥራቅ አውሮጳ ማኅበር ተባብረው በከፈቱት የመረጃ ጉባኤ ላይ የሰጡት መግለጫ፥”..............በግንቦት አንድ የአሥር ሀገራትን አዲስ አባልነት እናከብረዋለን። ከዚሁ ድርጊት ቀደም ብለን አሁን ይህን የመረጃ ጉባኤ የከፈትነው፣ የአውሮጳው ኅብረት የሚስፋፋበት ሂደት ገና ያላበቃ መሆኑን ለማሳየት ነው። መቄዶኒያ ያካባቢ ማረጋጊያውና የጥምረቱ ሂደት አንድ ከፊል ናት። በእኛ አስተያየት፥ በዚሁ ማረጋጊያና መጣመሪያ ሂደት የሚሳተፉት ሀገሮች የድርድር ማመልከቻ የሚያቀርቡበት መብት አላቸው።

ግን የጀርመን ክርስቲያንዴሞክራቶችን የሚወክሉት ፖለቲከኞች ኅብረቱ እንደገና በተጨማሪ አባላት የሚስፋፋበት ጥያቄ እክልም እንዳለበት ነው የሚያስገነዝቡት። ለምሳሌ የዚሁ ፓርቲ የባየርን ቅርንጫፍ የውጭ ፖለቲካ ቃልአቀባይ ጌርት ሚውለር እንደሚሉት፥ “............በግንቦት አንድ የአውሮጳው ኅብረት በ፲ ሀገሮች አዲስ አባልነት የሚስፋፋበትን ሂደት ማከናወን አለብን፣ ድርጊቱ ትልቅ የደስታ ምልክት ነው፣ ግን ትልቅ ችግርም አለበት። ሂደቱ እስኪስተካከል ድረስ ገና ዓመታት ወይም አሠርተ ዓመታት የሚፈጅ ይሆናል። ቀጥሎ፣ የአውሮጳው ኅብረት እንደገና በሌሎችም አባላት የሚስፋፋበት ጥያቄ ይደቀናል። ወደፊት ሩማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ምናልባትም ክሮአሲያ እና መቄዶኒያ የሚካሄድላቸው የአባልነቱ ድርድር ይቃና ዘንድ የሚጠየቅባቸውን የቤት ሥራ ለማከናወን መጣር ይኖርባቸዋል።”

ለአዲስ አባልነቱ ጥያቄ ወሳኝ መስፈርት የሚሆነው፥ በተሐድሶ ለውጡ ረገድ የሚገኘው እመርታ ነው። አውሮጳ ውስጥ በምዕራባዊው ባልካን በተለይም በአልባኒያና በመቄዶኒያ ነው ገና ብዙ የተሐድሶ ለውጥ መከናወን ያለበት። አውሮጳውያኑ አሁን በተለይ አሳሳቢ ሆኖ የሚያዩት በቦስኒያና ኸርዜጎቪና፣ በሰርቢያና በሞንቴኔግሮ ያለው ፖለቲካዊው ውዥቀት፣ እንዲሁም ገና ተረጋግጦ ያልታወቀለት የኮሶቮ እጣ ነው።

ጊዜ ይፈጃል እንጂ፣ የተቀሩትም አውሮጳውያት ሀገሮች ከኅብረቱ ጋር የሚቀላቀሉበት ርምጃ እውን ሊሆን እንደሚችል እዚህ ጀርመን ውስጥ የመንግሥትና የተቃውሞ ፓርቲዎችም ይስማሙበታል። ግን ቱርክ የአውሮጳው ኅብረት ሙሉ አባል በምትሆንበት ጥያቄ ረገድ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተለያዩ አመለካከቶች ናቸው የሚንፀባረቁባቸው። በተለይም ወግአጥባቂዎቹ ፓርቲዎች ናቸው የቱርክን አባልነት ጥያቄ የሚቃረኑት። የሆነ ሆኖ፣ የአውሮጳው ኅብረት ከቱርክም ጋር ድርድርን ይጀምር እንደሆን የሚታወቀው፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ይሆናል ነው የሚባለው። ግን፣ በተለይ የኤኮኖሚው ሁኔታ ድርድሩን እስከ ፲፪ እና ፲፭ ዓመታት የሚያጓትተው እንደሚሆንም ነው የሚገመተው።

እንግዲህ፣ የአውሮጳው ኅብረት እ ጎ አ በግንቦት አንድ፣ ፪ሺ፬ የአባላቱን ሀገሮች አሃዝ ከ፲፭ ወደ ፳፭ ካወጣጣውም በኋላ በሩን ይዘጋል ማለት አይደለም። ጀርመናዊው ውጭ-ጉዳይ ሚኒስትር ፊሸር እንደሚሉት፥ “..............የአውሮጳው ኅብረት መስፋፋት ለኣባላቱ ሀገሮች የሚያስገኘው ደኅንነት እና የኤኮኖሚ ዕድገት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፤ ርምጃው ለእኛ፣ ለልጆቻችንና ለልጅ-ልጆቻችን ነው ጠቀሜታን የሚያመጣው”።

በመጭው ቅዳሜ የአውሮጳው ኅብረት በአሥር አዲስ አባላት የሚስፋፋበት ድርጊት የአውሮጳን ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ገጽ የሚቀያይረው ይሆናል። በዚህም መሠረት፥ የአውሮጳው ኅብረት ነዋሪዎች አሃዝ ከ፫፻፹ ሚሊዮን ወደ ፬፻፶፭ ሚሊዮን ያድጋል፤ ግን በአዲሶቹ አባላት ወቅታዊ የኤኮኖሚ ድክመት ምክንያት የኅብረቱ ነፍስወከፍ ገቢ በ፲፭ በመቶ ተቀንሶ ወደ ፳፩ሺ፩፻ ኦይሮ የሚወርድ እንደሚሆን ነው የሚገመተው። ከጠቅላላው የዓለም ኤኮኖሚያዊ ውጤት ወደ ፴ በመቶ የሚጠጋው ከፊል በአውሮጳው ኅብረት ውስጥ የሚፈጠር ነው የሚሆነው።

አዲሶቹ የአውሮጳው ኅብረት አባልሀገራት የኅብረቱን ሕግ መቀበል አለባቸው። ግን፣ ድሃው የአውሮጳ ምሥራቅ ከሐብታሙ ምዕራብ ጋር የሚጣመርበት ድርጊት የሚያስከትለውን የማኅበራዊ ኑሮ ሳንካ ለማቃለል ይቻል ዘንድ፣ በብዙ የኑሮ ዘርፎች በኩል የሽግግር ድንጋጌዎች እንዲኖሩ ግዴታ ነው።

የ፲ሩ አዲስ መጭ ሀገሮች አባልነት ከተከናወነም በኋላ በእነርሱና በ፲፭ቱ ነባሮች መካከል ያለው የኬላ ቁጥጥር ለሰዎች ዝውውር ለጊዜው እንደፀና ይቆያል፤ መታወቂያ ካርድም ይጠየቃል። የገበያ ዕቃዎች ቁጥጥር ግን ኬላው ላይ የሚወገድ ይሆናል። እንደ ደንቡ ከሆነ፣ የአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገሮች ዜጎች ከየሀገራቸው እየወጡ በማናቸውም ሌላ አባል-ሀገር ውስጥ ለመኖርና ለመሥራት ቢፈልጉ የተለየ ፈቃድ ኣያሻቸውም፣ ግን ይኸው የሥራ ነፃነት አሁን አባላት ለሚሆኑት ለስምንቱ የምሥራቅ አውሮጳ ሀገሮች ዜጎች እስከ አንድ የተወሰነ ጊዜ ተገድቦ ሊቆይ ይችላል። የሁለቱ አዲስ መጦች ቆጵሮስና ማልታ ዜጎች ግን አሁኑኑ ሙሉ የዝውውር ነፃነት ነው ያላቸው። ጀርመንና ብዙዎቹ ሌሎች የአውሮጳው ኅብረት አባላት በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ለስምንቱ የምሥራቅ አውሮጳ ነዋሪዎች የሥራው ፈቃድ እንደተገደበ ይቆያል። እንዲያውም ይኸው የሥራ ግደባ እ ጎ አ እስከ ፪ሺ፲፩ የሚዘልቅ እንደሚሆንም ነው የሚታሰበው።

አዲሶቹ የአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገሮች የሸርፉ ኅብረት ተጣማሪዎች ባይሆኑም ቅሉ፣ የኅብረቱን የበጀት ሕግጋት ማክበር አለባቸው። በበጀቱ ጉድለት ረገድ እስከተወሰነ ጊዜ ከነባሮቹ አባላት የሚጠየቀውን እንዲፈጽሙ ባይገደዱም፣ ጥብቅ ቁጥጥር ነው የሚደረግባቸው። በቄራ አያያዝና በመባልእት አደረጃጀት ረገድ አዲሶቹ አባላት እጅግ ኋላቀር ሆነው ነው የሚታዩት። ስለዚህ የአውሮጳውን ኅብረት የንጽሕና ጥበቃ ደረጃ በማያሟሉት በአዲሶቹ አባል-ሀሮች ውስጥ ያሉ ኣያሌ የምግብ ማደራጃ ተቋማት እንዲዘጉ መደረጋቸው አይቀርም።

አዲሶቹ የአውሮጳው ኅብረት አባላት በተጨማሪ፥ ኅብረቱ በዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ ያለውን የጋራ ንግድ-መርሕ እንዲከተሉም ነው የሚጠየቁት፤ እስካሁን የደረሷቸውን ሁለትዮሽ ውሎች ማፍረስ አለባቸው። የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን የፊናንስ ድጋፍ የሚሰጠው፣ ከአዲሶቹ አባላት መካከል የኅብረቱን መላ ሕግጋት ለሚያከብሩት ብቻ መሆኑን አስታውቋል። ይኸው ግዴታ ነው የውህደቱን ሂደት የሚያፋጥነው ሆኖ የሚታየው።